ሪፖርት| መቐለ ከሜዳው ውጭ ወሳኝ ነጥብ ሲያሳካ ሆሳዕና የመውረድ አደጋ ተጋርጦበታል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛው ዙር የመጀመርያ ጨዋታውን ከቅጣት መልስ በአብዮ ኤርሳሞ መታሰቢያ ስታዲየም መቐለ 70 እንደርታን ያስተናገደው ሀዲያ ሆሳዕና 1-0 ሽንፈት አስተናግዷል።

በዋንጫ ፉክክር ውስጥ የሚገኘው መቐለ እና ላለመውረድ የሚታገለው ሀዲያን ያገናኘው ይህ ሁለት መልክ ያለው ጨዋታ ከሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ይልቅ የጨዋታው ትኩረት የሚስቡ የነበሩ የተለያዩ ክስተቶች ተፈጥረዋል።

በዙ ሳቢ ያልነበረው እና ረጃጅም ኳሶች በበዙበት በዚህ ጨዋታ ከሜዳቸው ውጭ እንደመጫወታቸው ቀጥተኛ ኳስ እና የመስመር አጨዋወቶችን ሲተገብሩ የቆዩት መቐለዎች በ11ኛው ደቂቃ ያሬድ ከበደ የተጣለለትን አየር ላይ ኳሱን አዙሮ የመታውን የሆሳዕናው ግብጠባቂ አቬር ኦቮኖ ወደ ውጭ ያወጣበት የጨዋታው የመጀመርያ ሙከራ ነበር። ተመሳሳይ የሆኑ የረጃጅም ኳሶች እና በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ጥረት የሚያደርጉት ሆሳዕናዎች ባልተለመደ ሁኔታ በጥሩ ኳሱን አደራጅተው ወደ ፊት የሄደን ኳስ ከሳጥን ውጭ ቢስማርክ ኦፖንግ በቀጥታ የመታውን የመቐለዎች ግብጠባቂ ፊሊፕ ኦቮኖ ያዳነበት ለሀዲያዎች መልካም አጋጣሚ ነበር።

አልፎ አልፎ በሚቆራረጥ ኳስ ወደ ጎል ለመድረስ ጥረት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የቀጠለው ጨዋታ 35ኛው ደቂቃ አንድ ክስተት ተፈጥሯል። የሆሳዕናው የመስመር አጥቂ ቢስማርክ ኦፖንግ ከሳጥን ውጭ በድንቅ ሁኔታ የመታውን የግቡ አግዳሚ ሲመልስበት የተመለሰውን ኳስ በድጋሚ አፈወርቅ ሲመታው ሥዩም ተስፋዬ ኳስ በእጅ ነክቷል በሚል ከዕለቱ ዳኛ ብሩክየማነ ብርሀንን በመክበብ ክርክር ውስጥ የገቡት የሀዲያ ተጫዋቾች የማስጠንቀቂያ ካርድ ተመልክተዋል። በዚህም ድርጊት የሆሳዕና ደጋፊዎች የዕለቱን ዳኛ በተለያዩ መንገዶች ተቃውሞቸውን አሰምተዋል።

ጨዋታው ከተወሰኑ ግርግሮች በኃላ ቀጥሎ 45ኛው ደቂቃ ሳይታሰብ በዕለቱ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የተመለከትነው ይሁን እንደሻው ከመሐል ሜዳ መሬት ለመሬት አክሮ የመታው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጭ ወጥቶበታል።

በተደጋጋሚ ወደ ጎል ለመድረስ በሚያደርጉት ጥረት እና 49ኛው ቢስማርክ አፒያ በፈጠረው መልካም የጎል አጋጣሚ በከፍተኛ ተነሳሽነት ሁለተኛ አጋማሽ ጨዋታን የጀመሩት ነብሮቹ ያልጠበቁትን ጎል አስተናግደዋል። የመቐለ ግዙፉ ናይጀርያዊ አጥቂ ኦኪኪ በእንቅስቃሴ ተከላካዮችን በመረበሽ እንጂ የጎል ዕድል መፍጠር ቢቸገርም በ59ኛው ደቂቃ ከአንድ አንድ ያገኘውን አጋጣሚ ወደ ጎልነት ቀይሮታል። ለኳሱ መነሻ የነበረው ቡድኑን ከረጅም ጊዜ ጉዳት መልስ የተቀላቀለው አልሀሰን ካሉሻ ያቀበለውን ኳስ ፍጥነቱ እና ጉልበቱን ተጠቅሞ በአስደናቂ ሁኔታ ሳጥን ውስጥ በመግባት በግብጠባቂው አናት ላይ አሳለፎ ወሳኝ የሆነ ጎል ለመቐለዎች አስቆጥሯል።

አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም በፍጥነት የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ቢያደርጉም ወደፊት የሚጣሉት ያልተሳኩ ረጃጅም ኳሶች ቡድኑን ውጤታማ አላደረጉትም ። ይልቁንም ለመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ተጋላጭ የሆኑት ሀድያዎች በመቐለዎች በኩል አስደንጋጭ የጎል ሙከራ ተደርጎባቸዋል።

አማኑኤል ገ/ሚካኤል የተቀበለውን ኳስ በፍጥነት ከግራ መስመር ወደ ሳጥኑ አጥቦ በመግባት የመታውን ግብጠባቂው አቬር ኦቮኖ ሳይቆጣጠረው ቀርቶ የተፋውን በዛሬው ጨዋታ መልካም እንቅስቃሴ ያደረገው አልሀሰን ካሉሻ ጎል አስቆጠረ ሲባል በድጋሚ ግብጠባቂው ከወደቀበት ተነስቶ አድኖበታል እንጂ ለመቐለዎች ሁለተኛ ጎል መሆን የሚችል ዕድል ነበር።

ከዚህ በኋላ በቀሩት ደቂቃዎች ብዙም የተለየ ነገር ሳንመለከት የጨዋታው መጠናቀቂያ ፊሽካ በሚጠበቅበት ጊዜ ጨዋታውን ለ5 ደቂቃዎች ያህል እንዲቋረጥ ያደረገ ክስተት ተፈጥሯል። ከቅጣት ምት የተሻገረን ኳስ ሀድያዎች በግንባር ገጭተው ጎል አስቆጥረው ደስታቸውን እየገለፁ ባለት ወቅት ረዳት ዳኛው ጎሉ የተቆጠረበት መንገድ ከጨዋታ ውጭ አቋቋም ነው በማለት ጎሉ እንዳይፀድቅ በማድረጋቸው የሀዲያ ደጋፊዎች የተለያዩ ቁሳቁሶች ወደ ሜዳ በመወርወር የዳኛውን ውሳኔ በከፍተኛ ሁኔታ ተቃውመዋል። በዚህም ሁኔታ የመቐለዎች የህክምና ባለሙያ ጭንቅላቱ ላይ ጉዳት አስተናግዶ የህክምና እርዳታ ሲደረግለት ተመልክተናል። የዕለቱ ዳኛ በተለያየ ጊዜ የሀድያ ተጫዋቾች እና አንበሉን ጨምሮ ለማናገር ወደ እርሱ በቀረቡ ቁጥር በርከት ያሉ የማስጠንቀቂያ ካርድ ሲመዙም ተመልክተናል።

በመጨረሻም ጨዋታው የዳኛውን ውሳኔ በመቃወም ከተፈጠረ ተቋውሞ በኋላ ቀጥሎ ውጤቱ በመቐለዎች 1-0 በሆነ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ መቐለዎች የዓምና ድላቸውን ለመድገም በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ሲቀጥሉ በአንፃሩ ሆሳዕናዎች መሸነፋቸውን ተከትሎ የመውረድ ስጋት እንዲጋረጥባቸው አድርጓቸዋል።

©ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ