በ16ኛ ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ቀን ቅዱስ ጊዮርጊስ በሜዳው በወልቂጤ ከተማ 1-0 ከረታበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።
“ተጫዋቾቼ ያሰበነውን እቅድ ለመተግበር ባሳዩት ጥረት የሚገባንን ውጤት አግኝተናል” ደግአረግ ይግዛው (ወልቂጤ ከተማ)
ስለጨዋታው
” ከሜዳችን ውጭ ያደረግነው እንደመሆኑ ጠንካራ ጨዋታ ነበር። ቅዱስ ጊዮርጊስ ትልቅ ታሪክ ያለውና በጠንካራ ተጫዋቾች የተገነባ ስብስብ ነው። የኛ ቡድን ከጨዋታ ጨዋታ ልጆቻችን ልምድ እያገኙ ሲሄዱ መሻሻሎች በማሳየት ላይ ይገኛሉ። ዛሬም ጨዋታው ሊከብደን እንደሚችል አስበን ነበር። ነገርግን ልጆቻችን ሜዳ ላይ ለመተግበር ያሰበነውን እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ባሳዩት ጥረት የሚገባንን ውጤት አግኝተናል።”
ስለባከኑት የግብ እድሎች
” በተጫዋቻችን ላይ ከፍተኛ ጉጉትና የልምድ ማነስ ይታያል። ነገርግን እኛ እንደቡድን ትኩረት የምናደርገው የነበራቸውን እንቅስቃሴ ለማሸነፍ የነበራቸውን ቁርጠኝነት እኛ ትልቅ ቦታ እንሰጣቸዋለን። ጎል ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎች አሉ። በቀጣይም የሚቀሩትን ነገሮች ለማሻሻል እንሰራለን። አሁን ላይ እየሄድንበት ያለው መንገድ ጤናማ ነው ብዬ አስባለሁ። በቀጣይም ሁለተኛው ዙር ከመጀመርያው የበለጠ በአካልም በአእምሮ ዝግጅት የሚፈልግ ስለሆነ የተሻለ ስራ መስራት ይኖርብናል።”
“ከግቧ መልስ ተጫዋቾቼ ጫና ውስጥ ገብተው ያለእቅድ ነበር ሲጫወቱ የነበሩት” ሰርዳን ዝቪጅኖቨ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)
ስለ ጨዋታው
“ጨዋታው ከባድ እንደሚሆን ገምተን ነበር፤ ምክንያቱም ወልቂጤ በጣም ጠንካራና ጥቅጠቅ ብሎ የሚጫወት ቡድን ነው። በመጀመሪያው 20 ደቂቃ ጨዋታውን ተቆጣጥረን ያቀድነውን ለመተግበር ሞክረናል። ከዛ በኋላ ግን ለምን እንደሆነ ባላውቅው በጀመርንበት መንገድ መጫወት አልቻልንም። በመጀመሪያው አጋማሽ በነበረን ነገር ጎል ለማስቆጠር የሚያስፈልጉትን ወደ ጎል ኳሶችን መምታት ሆነ ወደ ሳጥን ውስጥ ኳሶችን ማሻማት አልቻልንም። በሁለተኛው አጋማሽ እኛ በሰራነው ስህተት እድለኛ ስለነበሩ ጎል ማስቆጠር ቻሉ። ከግቧ መልስ ተጫዋቾቼ ጫና ውስጥ ገብተው ያለእቅድ ነበር ሲጫወቱ የነበሩት። ለእኛ የዛሬ ጨዋታ መጥፎ ጨዋታ ነበር። ነገርግን አሁንም ቢሆን ለዋንጫ የመጫወት እድሉ አለን። ገና ቀሪ 14 ጨዋታዎች አሉን። ከእኛ በላይ ያሉት ቡድኖች በጥቂት ነጥብ ነው የራቁን።
ስለ ደጋፊዎች ጫና
” ቅዱስ ጊዮርጊስ የሀገሪቱ ምርጥ ክለብ እንደመሆኑ ከደጋፊዎች ሆነ ከሌሎች አካላት ሁሌም ጫና ያለበት ቡድን እንደሆነ እረዳለሁ። ነገርግን አንዳንድ ጊዜ የደጋፊዎች ጥያቄ መጥፎም ተጫውተን ስናሸንፍም ደስተኛ አይደሉም። መጥፎ ተጫውተንም ሳናሸንፍ ስንቀር አሁንም ደስተኛ አይደሉም። ደጋፊዎች ሁሌም ስንሸነፍ ደስተኛ አይደሉም። ይህ የተለመደ ነገር ነው። ነገርግን አንዳንዴ ጥሩ ተጫውተህ ትሸነፋለህ። በዛሬው ጨዋታ ቁጥሮች ቢኖሩ ኖሮ ከ60% በላይ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ነበረን። በተጨማሪም 8(9) ተጫዋቾች ከኳስ ጀርባ አድርጎ ከሚጫወት ቡድን ላይ ጎል ማስቆጠር እጅግ ከባድ ነው።
© ሶከር ኢትዮጵያ