” በተደጋጋሚ ኳሶች ወደ እኔ በመምጣታቸው የቸገረኝን ግብ ማስቆጠር እንድመልሰው አስችሎኛል” ባለ ሐት-ትሪኩ ሀብታሙ ገዛኸኝ

የሲዳማ ቡናው ሀብታሙ ገዛኸኝ ስለ ሐት-ትሪኩ ይናገራል፡፡ 

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአስራ ስድስተኛው ሳምንት የሁለተኛውን ዙር የመጀመሪያ ጨዋታቸውን በሜዳቸው ያደረጉት ሲዳማ ቡናዎች በግብ ተንበሽብሸው ወላይታ ድቻን 5ለ3 ረተዋል፡፡ በጨዋታው ላይ ለውጤቱ መገኘት ጉልህ ሚና ከነበራቸው ተጫዋቾች መካከል አንዱ የመስመር አጥቂው ሀብታሙ ገዛኸኝ ድርሻ የጎላ ነበር፡፡ በመጀመሪያ ዙር የሊጉ ጨዋታዎች ምንም እንኳን ለሲዳማ ቡና አምስት ግቦችን ያስቆጠረው ወጣቱ ተጫዋች ዛሬ ሲዳማ ቡና በሜዳው ወላይታ ድቻን ሲያሸንፍ ካደረገው ጥሩ እንቅስቃሴ ባሻገር ሦስት ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ሐት-ትሪክ የሰራ ሲሆን ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታን አድርጓል፡፡

የዛሬውን ጨዋታ እንዴት አገኘኸው?

በመጀመሪያ ደስ ብሎኛል። የዛሬው ጨዋታ በጣም ጥሩ ነበር፤ እኛም የተሻልን ሆነን መገኘታችን ለውጤት አብቅቶናል።

በዛሬው ጨዋታ የቡድኑ ጥንካሬ ምን ነበር?

“የቡድናችን ጥንካሬ ካለፈው ዙር ማጥቃቱ ላይ እጅግ ጥሩ ነው፡፡ ትንሽ ግን መከላከሉ ላይ ትንሽ የሰራነው ስህተት ነው ዋጋ ሚያስከፍሉን መሀሉ እና አጥቂው ተጋግዞ ስለሚጫወት ጥንካሬን አምጥቶልናል፡፡

በመጀመሪያው ዙር በመጠኑም ቢሆን ቀዝቀዝ ብለህ ነበር። ዛሬ ደግሞ ደምቀህ ሐት-ትሪክ በመስራት ሁለተኛውን ዙር ጀምረሀል…

እንደ ተጫዋች ይህ ያለ ነው። በመጀመሪያው ዙር ጨዋታችን ኳስ ወደ እኔ ስለማይደርስ ብቃቴን እንዳሳይ አላስቻለኝም ነበር፡፡ በዚህ ጨዋታ ግን በተደጋጋሚ ኳሶችን ወደ እኔ በመምጣታቸው የቸገረኝን ግብ ማስቆጠር እንድመልሰው አስችሎኛል፡፡

በሁለተኛው ዙር ከሀብታሙ ገዛኸኝ ምን ይጠበቃል?

አሁን ካለኝ በተሻለ ሪከርዶችን ማስመዝገብ እፈልጋለሁ። በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ራሴን አብቅቼ መጫወትም እፈልጋለሁ፡፡ ይህን ለማድረግ ከአሁኑ ጠንክሬ እየሰራሁ ነው፡፡ድክመቶች ነበሩብኝ። በክረምቱ ወቅት ወደ ሌላ ክለብ ለመሄድ አስቤ ስለነበር ዝግጅት በደንብ አልሰራሁም፡፡ ይሄ ደግሞ በኔ ላይ ጫና ፈጥሮብኝ ነበር፡፡ አሁን ግን እየሰራሁ እየተስተካከልኩ መጥቻለሁ፡፡ እንደ እቅድ እኔ ዓምና በአንድ ነጥብ ያጣናትን ዋንጫ ማግኘት ነው አላማዬ፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ