ዛሬ በዓዲግራት በተካሄደ ጨዋታ ወልዋሎ እና ሰበታ ሁለት ለሁለት በሆነ አቻ ውጤት ከተጠናቀቀ በኃላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች የሚከተለውን ሀሳብ ሰጥተዋል።
” የፈጠርናቸውን ተደጋጋሚ ዕድሎች ብንጠቀም ተጨማሪ ግቦች ማስቆጠር እንችል ነበር” ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ (ወልዋሎ)
ስለ ጨዋታው
ጨዋታው ጥሩ ጨዋታ ነበር። የመጀመርያ ጨዋታዬ ነው፤ በዛላይ ሁለት ጊዜ ብቻ ልምምድ አሰርቼ ነው ወደ ጨዋታው የገባሁት። እንደ መጀመርያ ጨዋታ ጥሩ ነው። ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎች ፈጥረናል፤ ዕድሎቹን ብንጠቀም ተጨማሪ ግቦች ማስቆጠር እንችል ነበር። ጨዋታው በሁለት የቆሙ ኳሶች ነው የገደሉት። ውጤቱን ይዘን መውጣት ይገባን ነበር።
ከመሀል ሜዳ ነው የገባብን። ምንም እንኳን የግብ ጠባቂ ስህተት ቢሆንም እንደቡድን ስህተት እንወስደዋለን። ከጨዋታዎች በኃላ አሻሽለን የተለየ ቡድን ይዘን እንቀርባለን። በቀጣይ ጨዋታ የተሻለ ነገር ይዘን በመምጣት ደጋፍያችንን የምናስደስትበት ዕድል ለመፍጠር ጥረት እናደርጋለን።
ቡድኑ ያለበትን የመከላከል ችግር ለመፍታት የታሰበው ነገር
በውድድር አጋማሽ ላይ ያለ ክለብ የተቀመጡ ተጫዋቾች ማግኘት ይቸግራል። አብዛኞቹ ደግሞ ብዙ ሳይጫወቱ ያረፉ ናቸው። ስጋት ነበረኝ፤ የመጨረሻ አስራ አምስት ደቂቃ ላይ የአካል ብቃት ችግሮች ይታዩ ነበር። እነዚህን በተደጋጋሚ ልምምድ አሻሽለን በቀጣይ ጨዋታ የተሻለ ቡድን ይዘን ለመቅረብ ጥረት እናደርጋለን።
ስለ ቡድኑ አጨዋወት
በሁለት ቀን ውስጥ የተለየ አጨዋወት ፈጥሬ ቡድኑን ሌላ ውዥንብር ውስጥ መክተት አልፈለግኩም። የተወሰነ ጥገና ለማድረግ ሞክሬያለው እንጂ ቡድኑ በዚህ መንገድ እንዲወጫት አልፈልግም።
“ጠንካራ ጨዋታ ነበር፤ ነጥብ ይዘን መውጣታችንም ትልቅ ነገር ነው” ውበቱ አባተ (ሰበታ ከተማ)
ስለ ጨዋታው
የሜዳ ውጪ ጨዋታ ከባድ ነው። በመጀመርያው ዙር በአንድ ከሜዳ ውጪ ጨዋታ ላይ ብቻ ነበር ነጥብ ይዘን የወጣነው። ከዚህ በፊት ጥሩ ብንቀሳቀስም ነጥብ የመያዝ ችግር ነበረብን። ቅድሚያ ሁለት ጎል ተቆጥሮብን እስከ መጨረሻው ታግለን አቻ መውጣት ችለናል። ጠንካራ ጨዋታ ነበር፤ ነጥብ ይዘን መውጣታችንም ትልቅ ነገር ነው።
ስለ ቡድኑ እንቅስቃሴ
ጥሩ ነው፤ መጫወት በምንፈልገው መንገድ ተጫውተናል። በሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ስንደርስ ችግሮች ነበሩብን። ከዕረፍት በፊት ብዙ ሙከራ ማድረግ አልቻልንም። ከዕረፍት በኋላ ግን በተወሰነ መንገድ ችግራችንን ፈተነዋል። በአጠቃላይ በተጫዋቾቹ የነበረው ጥረት፣ ከሜዳ ውጪ ያደረግነው እንቅስቃሴ እና ከሁለት ግብ መመራት በኃላ ነጥብ ይዘን በመውጣታችም በአጠቃላይ ደስተኛ ነኝ።
ቡድኑ የግብ ዕድሎች መፍጠር ላይ ያለው ክፍተት
አንዱ እዛ መድረስ መቻላችን ጥሩ ነው። ዕድል መፍጠር ላይ እና አጨራረስ ላይ ክፍተቶች አሉብን፤ እነሱ ላይ እየሰራን ነው። የሜዳ ውጪ ጨዋታ ከባድ ነው። ሌላ ደግሞ አፈግፍጎ በብዛት ከሚከላከል ቡድን ጋር ዕድሎች ለመፍጠር በበለጠ በትዕግስት መስራት ያስፈልጋል። ሁለተኛው አጋማሽ ላይ እንቅስቃሴያችንን ለማስተካከል ጥረት ማድረጋችን ይበልጥ ዕድል እንድምፈጥር አድርጎናል።
ስለ ቡድኑ የዝውውር ዕቅድ
በኛ ሀገር ሁኔታ በዚህ ወቅት ተጫዋች ለማዘዋወር ሁኔታው አይፈቅድልህም። ተጫዋች ላምጣ ብትልም ካሉ የተሻሉ ተጫዋቾች ለማግኘት ትቸገራለህ። አንድ ተጫዋች ለማምጣት ዕድል ሊኖረን ይችላል። ከዛ ውጪ ባለን ስብስብ ነው የምንቀጥለው።
©ሶከር ኢትዮጵያ