የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ተቃውሞ እና የአሰልጣኙ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ

ዓምና ነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ ወደ ፈረሰኞቹ ቤት ብቅ ያሉት አሰልጣኝ ሰርዳን ዝቪጅኖቨ በደጋፊዎች እየደረሰባቸው ያለው ተቋውሞ እና ቀጣይ ዕጣ ፈንታቸው እንዲጠበቅ አድርጎታል።

ከዚህ ቀደም በዩጋንዳው ቪላና በታንዛኒያው ያንጋ አፍሪካ እንዲሁም በዛምቢያው ቢዩልድ ኮን ያሰለጡት ሰርቢያዊው አሰልጣኝ ባለፈው ወር በተከታታይ ድል አስመዝግበው መሪነቱን ከያዙ በኋላ ቡድኑ አስፈሪ መልክ የያዘ ቢመስልም ወደ ጎንደር አቅንተው ከዐፄዎቹ ጋር ነጥብ ተጋርተው ከተመለሱ በኋላ የቡድን ሥራውም ሆነ የውጤት መላው ጠፍቶባቸዋል። በሁለት ጨዋታ ማግኘት ካለባቸው ስድስት ነጥብ አንድ ነጥብ ብቻ በማሳካትም መሪነታቸውን የሚያሰፉበትን አረድል አምክነው ይባሱኑ አስረክበዋል። ይህ ደግሞ ለሁለት ዓመት ከለመዱት ዋንጫ ለራቁት ለቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች አልተዋጠላቸውም። 

በአሰልጣኙ እምነት ያጡት ደጋፊዎቹ በተለያዩ አጋጣሚዎች ከፍተኛ ተቃውሞቸውን እያሰሙ ሲሆን ይልቁንም የክለቡን ባህል፣ ፍላጎት እና የአሸናፊነት መንፈስ የሚያውቁ የቀድሞ ተጫዋቾች ወደ አሰልጣኝነቱ ይመለሱ ማለትም ጀምረዋል።

ይህም ብቻ አይደለም ከአንዳንድ ተጫዋቾችም እየወጡ እንዳሉት መረጃዎች ከሆነ የአሰልጣኙ የአሰለጣጠን መንገድ እና የጨዋታ አቀራረብ እንደልተመቻቸው እየተሰማ ይገኛል። ከሰሞኑም የክለቡ የቦርድ አመራሮች አሰልጣኙን ለማናገር እንዳሰቡ ሰምተናል። ክለቡ ከአሰልጣኙ ጋር የሚያደርገው ውይይት ምን ይዞ ይመጣ ይሆን የሚለውን በቀጣይ ተከታትለን የምናቀርብ ይሆናል።

©ሶከር ኢትዮጵያ