የፕሪምየር ሊግ 16ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፪) – ተጫዋች ትኩረት

የሳምንቱን ዐበይት ጉዳዮች የምንመለከትበት ሁለተኛው ክፍል ትኩረት የሳቡ ተጫዋች ነክ ክስተቶችን ይመለከታል

👉 ከጨዋታ ርቀው የከረሙ ተጫዋቾች በጥሩ ብቃት ዳግም መመለስ

በአጋማሹ የዝውውር መስኮት ከአንድ ዓመት እስከ ግማሽ የውድድር ዓመት ድረስ ያለክለብ የቆዩ እንዲሁም በነበሩባቸው ክለቦች የመሰለፍ እድል ጨርሶውኑ ያላገኙ ተጫዋቾች ወደ ተለያዩ ክለቦች ያመሩባቸውን ዝውውሮችን እየፈፀሙ ይገኛል። ለአብነትም አልሀሰን ካሉሻ፣ ተስፋዬ በቀለ፣ ዮናስ በርታ፣ ዐመለ ሚልኪያስ እና ዮናታን ከበደ ከሰሞኑ አዳዲስ ክለቦችን መቀላቀላቸው ይታወሳል።

በተለይም ክለብ አልባ የነበሩትና ላለፉት ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት በሚጠጉ ጊዜያት ምንም አይነት ይፋዊ የፉክክር ውድድሮች ላይ ተሳትፎን ያላደረጉት ተጫዋቾች ከአዲሱ ቡድኖቻቸው ጋር ላለፉት ጥቂት ቀናት ልምምድ ከሰሩ በኃላ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ባገኟቸው የጨዋታ ደቂቃዎች መልካም የሚባልን እንቅስቃሴ ማሳየት ችለዋል።

ከዚህ ቀደም ሙሉዓለም ረጋሳ ጫማውን ከሰቀለ በኋላ ዳግም ወደ ውድድር ተመልሶ ሀዋሳ ከተማ ከተቀላቀለ ወዲህ ባሳየው ጥሩ እንቅስቃሴ ብዙ ሲያነጋግር ሲከርም አሁንም የእነዚህ ተጫዋቾች የ16ኛ ሳምንት የጨዋታ እንቅስቃሴ ሊጉ የሚገኝበትን ደካማ ደረጃ ያመላከተ ሆኗል። ለወትሮም በተንቀራፈፈ የጨዋታ ሒደት የሚታማው ሊጉ ምንም እንኳን ተጫዋቾቹ ከፉክክር ጨዋታ በራቁባቸው ጊዜያት ራሳቸው በሚፈለገው የዝግጁነት ደረጃ ለማቆየት ያደረጉት ጥረት የሚደነቅ ቢሆንም በውድድር ላይ በቆዩና ከውድድር በራቁ ተጫዋቾች መካከል ይህ ነው የሚባል ልዩነት አለመኖሩ ግን የሚያስተዛዝብ ሁነት ነው።

👉የውድድር ዘመኗ ፈጣን ጎል ባለቤት እና የአሲስት ባለ ሐት-ትሪኩ አዲስ ግደይ

በዘንድሮው የውድድር ዘመን ወላይታ ድቻ በሶዶ ስታዲየም ድሬዳዋ ከተማ ሲረታ የውድድር ዘመኗ ፈጣን ግብ በእዮብ ዓለማየሁ ገና በ48ኛው ሰከንድ መቆጠሩ የሚታወስ ነበር። ነገር ግን በትናንቱ የሲዳማ ቡና እና ወላይታ ድቻ ጨዋታ ላይ አዲስ ፈጣን ጎል ተመዝግቧል።

በሀዋሳው የሰው ሰራሽ ስታዲየም መርሐ ግብር የተያዘለት የሲዳማ ቡና እና ወላይታ ድቻ ጨዋታ በመሀል ዳኝነት የመሩት ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ ገና የጨዋታው የማበሰሪያ ፊሽካቸውን ባሰሙበት ቅፅበት ኳሱን የጀመሩት ሲዳማ ቡናዎች አማካዩ ዳዊት ተፈራ እግሩ ላይ የገባችውን ኳስ በወላይታ ድቻ ተጫዋቾች መዘናጋት ታግዞ በፍጥነት ወደ ወላይታ ድቻ ሳጥን ያሻገረው ኳስ የሲዳማው ቡና አጥቂ አዲስ ግደይ በፍጥነት ደርሶ በጭንቅላቱ በመገጨት የውድድሩን ዘመኗን ፈጣን ግብ በ44ኛው ሰከንድ ለማስቆጠር በቅቷል።

ሌላኛው የዚህች ግብ ታሪካዊ ግጥጥም የቀደመው ክብረወሰንን የየብዞ የነበረው የወላይታ ድቻው እዮብ ዓለማየሁ ደቂቃው ሲሻሻል በሜዳ ላይ የአዲስ ተቃራኒ ሆኖ መመልከቱ ነው።

በዚህ ሳምንት አቡበከር ናስር እና ሀብታሙ ገዛኸኝ ሦስት ጎሎችን አስቆጥረው ሐት-ትሪክ በመስራት የደመቀ ሳምንት አሳልፈዋል። አዲስ ግደይ ደግሞ ለጎል በማመቻቸት ሌላው ባለ ሐት-ትሪክ ነበር። የዓመቱን ፈጣን ጎል ያስቆጠረው አዲስ ሀብታሙ ላስቆጠራቸው ሁለት ጎሎች እና ለዳዊት ተፈራ ጎል በማመቻቸት በእለቱ ከተቆጠሩ አምስት ጎሎች በአራቱ ላይ ተሳትፎ ማድረግ ችሏል።

በዚሁ ጨዋታ ላይ ሁለት ጎል ያስቆጠረውና ለተገኘው የፍፁም ቅጣት ምት መንስኤ የነበረው የወላይታ ድቻው እድሪስ ሰዒድም ድርሻ ከፍተኛ ነበር።

👉ከእድሜው የቀደመው አቡበከር ናስር

በ2008 የውድድር ዘመን አጋማሽ ላይ ነበር ከሐረር ሲቲ ወደ ኢትዮጵያ ቡናተስፋ ቡድን አምርቶ ቀጥሎም ወደ ዋናው ቡድን ያደገው። ድፍረት፣ ታጋይነት፣ ሜዳ ላይ ያለውን ያለ ስስት ለቡድኑ መስጠቱ እና ሌሎች በርካታ ጠንካራ ጎኖችን መዘርዘር ይቻላል።

ገና በከፍተኛ ደረጃ ኳስን መጫወት ከጀመረ ጥቂት ዓመታት ያስቆጠረው ይህ አጥቂ በኢትዮጵያ ቡና ቆይታው በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ራሱን ከተጠባባቂነት ወደ ቡድኑ ወሳኝ ተጫዋችነት በማሸጋገር በደጋፊዎቹ ዘንድ ስሙን በደማቁ እያተመ ይገኛል።

ለተስፈኛ ተጫዋቾች ጤናማ እድገት ያልተመቸ በሆነው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውስጥ እንደ አቡበከር ናስር ባለፉት ጥቂት አመታት ወደ ዋናው ቡድን አድጎ በዚህ ደረጃ ከፍ ያለ ግልጋሎት እየሰጠ የሚገኝ ተጫዋች ለማግኘት ያዳግታል። ገና በለጋ እድሜው ኢትዮጵያ ቡናን በሚያክል ከፍ ያለ የደጋፊዎች ጫና ባለበት ቡድን ውስጥ ከእድሜው በላይ በሆነ ከፍ ያለ ግዳጅ ቢታጭም ራሱን ብቁ በማድረግ ታላላቆቹ ለማድረግ የከበዳቸውን ሁሉ እያደረገ ይገኛል።

የቡድኑ ተቀዳሚ ሁለት አምበሎች አማኑኤል ዮሐንስ እና አህመድ ረሺድ አለመኖራቸውን ተከትሎ ቡድኑን በአምበልነት እየመራ የገባው አቡበከር ናስር ሁለት በጨዋታ እንዲሁም አንድ በፍፁም ቅጣት ምት በማስቆጠር በኢትዮጵያ ቡና መለያው የመጀመርያውን ሐት-ትሪክ መስራት ችሏል።

ገና ከወዲሁ በጉዳት እየተፈተነ እንኳን የኢትዮጵያ ቡና የቁርጥ ቀን ልጅ እየሆነ የመጣው አቡበከር በቀጣይ ራሱን እየቆጠበ በሚጫወትበት እና ስሜታዊነቱን በሚያስወግድበት መንገድ ዙሪያ ከቡድኑ አሰልጣኞች ድጋፍ የሚያገኝ ከሆነ ከክለብ አልፎ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ሀገሩን በቀጣይ ዓመታት መጥቀም የሚችል የእምቅ አቅም ባለቤት ነው።

👉በልደቱ ማግስት ቡድኑን ወሳኝ ነጥብ ያስጨበጠው በዛብህ መለዮ እና የባህር ዳር ስታዲየም

ከቀናት በፊት ልደቱን ያከበረው የፋሲል ከነማው አማካይ በልደቱ ማግስት ቡድኑ ፋሲል ከተማ በቅጣት ምክንያት በባህር ዳር ዓለምአቀፍ ስታዲየም አዳማ ከተማን አስተናግዶ 1-0 በረቱበት ጨዋታ ቡድኑን አሸናፊ ያደረገች ብቸኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል።

በፋሲል ከነማ የአማካይ መስመር ውስጥ ከጥልቀት የሚነሳ አማካይ እንዲሁም ወደ ፊት በተጠጋ የአጥቂ አማካይነት በማይቀዥቅ አቋም ቡድኑን እያገለገለ ይገኛል። አብሮት እንደሚሰለፉት አማካዮች ብዙ ግቦችን ባለማስቆጠሩ በቂ ሙገሳ ባይቸረውም በተለይ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ዘግይቶ በመድረስ አደጋ ለመፍጠር ጥረት የሚያደርግበት መንገድ አስደናቂ ነው።

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ግብ ያስቆጠረው በዛብህ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ቡድኑ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ቅድመ ማጣሪያ የታንዛኒያውን አዛም 1-0 በባህር ዳር ስታዲየም ሲረቱ ከአዳማው ጨዋታ ጋር ተመሳሳይነት ያላትን ግብ ማስቆጠሩ የሚታወስ ነው።

👉ወንድሜነህ ደረጀ እና ፈቱዲን ጀማል ቀጣዩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመሐል ተከላካይ ጥምረት?

ምንም እንኳን በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከኢትዮጵያ ቡና ያነሰ ግብ ያስተናገዱ የመከላከል ጥምረቶች ቢኖሩም በሁለት ኢትዮጵያዊያን የተመሠረተው የእነዚህ ሁለት ተጫዋቾች ጥምረት ግን በጉዳትና ተያያዥ ጉዳዮች አማራጫቸው ለጠበበው የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ የተሻለ የልብ ልብ የሚሰጥ ይመስላል።

የብሔራዊ ቡድኑ ተቀዳሚ ተመራጭ የመሀል ተከላካይ የሆነው አስቻለው ታመነ ጉዳት ላይ ሲገኝ አንተነህ ተስፋዬ እና ያሬድ ባየህ በጉዳት ምክንያት ክለቦቻቸውን በርከት ባሉ ጨዋታዎች ማገልገል አልቻሉም።

በተለይ አሰልጣኙ አይቮሪኮስትን በረቱበት ጨዋታ መጠነኛ ፍንጮች ባሳየው የኳሳ ቁጥጥር አጨዋወት ለመቀጠል የሚሹ ከሆነ ይህን አጨዋወት ለመተግበር ያለውን ሁሉ በሚሰጠው ኢትዮጵያ ቡና ቡድን ውስጥ በቋሚነት እያገለገሉ የሚገኙት ሁለቱን ተጫዋቾች በብሔራዊ ቡድን ስብስብ ውስጥ ማካተቱ ጠቃሚ ይሆናል።

እርጋታቸው፣ ተግባቦታቸውና ከኳስን ለመቀበል ያላቸውን ድፍረት ከጥሩ የአንድ ለአንድ ግንኙነት የማሸነፍ ብቃት ጋር ያጣመሩት ሁለቱ የመሀል ተከላካዮች ዘንድሮ በሊጉ እያሳዮት ካሉት ነገር አንፃር የብሔራዊ ቡድን ጥሪ ቢደርሳቸው የሚያንስ እንጂ የሚበዛ አይሆንም።

*ዛሬ ይፋ በሆነው ምርጫ ፈቱዲን ሲካተት ወንድሜነህ ተዘሏል።

👉ዳዊት እስጢፋኖስ ለሰበታዎች የጭንቅ ቀን ደራሽ ሆኗል

ሰበታ ከተማዎች ከኋላ ተነስተው ከወልዋሎ ጋር ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ዳዊት እስጢፋኖስ ሁለት የቅጣት ምት ግቦች በማስቆጠር ቡድኑን ከጭንቅ ገላግሏል። በጨዋታው ከኳስ ቁጥጥር ብልጫ ባለፈ መፈየድ ላልቻለው ስብስብ ሁለት የቆሙ ኳሶችን ወደ ቁምነገር የለወጠው አማካዩ በተለይም የመጀመርያዋ ቅጣት ምት ያስቆጠረበት መንገድ እጅግ የሚያስደንቅ ነበር።

ወደ ግብ ክልል የተጠጉ እና በቂ ክፍት ቦታ በሌለባቸው ቦታዎች የሚገኙ የቆሙ ኳሶች ወደ ግብነት የመቀየር ትልቅ ክፍተት በሚታየው ሊጋችን እንደ ዳዊት እስጢፋኖስ የመጀመርያ ግሩም ግብ ማየት የተለመደ አይደለም።

👉 ዓብዱልአዚዝ ኬይታ ስህተት እና የደጋፊዎች አፀፋዊ ምላሽ

ባለፈው ዓመት ቡድኑ ተቀላቅሎ የወልዋሎን ግብ በቋሚነት እየጠበቀ የሚገኘው ጊኒያዊው ዓብዱልዓዚዝ ኬታ ካለወትሮው ብቃቱ ወርዶ በግል ስህተት ግቦችን እያስተናገደ ይገኛል። ከሰበታ ጋር በነበረው ጨዋታ ለግቦቹ መቆጠር የቦታ አያያዝ እና የትኩረት መሰረታዊ ችግር የነበረው ግብ ጠባቂው ከስህተቶቹ በላይ በሜዳ ውስጥ ያሳያቸው ለደጋፊውም የተጋጣሚ ቡድንም ያላከበረ አላስፈላጊ ተግባራት ቡድኑ ሊኮንነው ይገባል። በተለይም በሰባ አራተኛው ደቂቃ የሰራው የጊዜ ማጥፋት ተግባር ከአንድ በፕሪምየር ሊግ ደረጃ ከሚጫወት አንጋፋ ግብ ጠባቂ የሚጠበቅ አይደለም።

👉የባዬ ገዛኸኝ ይቅርታ

በተጠባቂው የሲዳማ ቡና እና ወላይታ ድቻ ጨዋታ ጅማሮ በፊት ከዚህ ቀደም ከሲዳማ ቡና ደጋፊዎች ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብቶ የቆየው የወላይታ ድቻው አምበል ባዬ ገዛኸኝ የሲዳማ ደጋፊዎችን በይፋ ይቅርታ ሲጠይቅ ተስተውሏል።

ከሜዳ ውጭ ላሉ የስፖርታዊ ጨዋነት ጥሰት መነሾ ሲሆን የሚስተዋሉ መሰል በተጫዋቾችና በደጋፊዎች መካከል የሚነሱ ውዝግቦችን ለማርገብ ባዬ ገዛኸኝ ያደረገው ጥረት መልካም የሚባል እና የሚበረታታ ሲሆን መሰል ተግባሮች መለመድ ያለባቸው ናቸው።

👉መጥፎ ቀን ያሳለፈው ምንተስኖት አሎ

ኢትዮጵያ ቡና ስሑል ሽረን አስተናግዶ 6-1 በረታበት ጨዋታ የሽረው ግብጠባቂ ምንተስኖት አሎ በከፍተኛ ደረጃ መጫወት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ያሳለፈው መጥፎው ቀን ሳይሆን አይቀርም።

በሊጉ ካሉ ተስፋ ከሚጣልባቸው ግብጠባቂዎች አንዱ የሆነው ምንተስኖት በቅርቡ ወደ አውሮፓ አቅንቶ የሙከራ ጊዜን አሳልፎ ወደ ኢትዮጵያ መመለሱ የሚታወስ ሲሆን በቅዳሜው ጨዋታ ስድስት ግቦችን ከማስተናገዱ በዘለለ ሁለቱ ግቦች የተቆጠሩት የእሱ ስህተት ታክሎባቸው መሆኑ ቀኑን ሌላ ጥሩ ያልሆነ መልክ ይሰጠዋል።

በተለይ የቡድኑን ተነሳሽነት የገደሉት ሁለት ግቦች የተቆጠሩበት መንገድ የተጫዋቹን ወቅታዊ አቋም ጥያቄ ውስጥ የከተቱ ነበሩ። ቢሆንም ተጫዋቹ ከእድሜው ለጋነት አንፃር ስህተቶች እንደመማርያ በመውሰድ ይበልጥ ራሱን ለማሻሻል ሊጠቀምባቸው ይገባል።

👉 ሁለት ግብ ጠባቂዎችን በጨዋታ ዕለት ስብስቡ ያካተተው ድሬዳዋ ከተማ

ድሬዳዋ ከተማ በ16ኛ ሳምንት ሀዋሳ ከተማን አስተናግዶ 3-1 በረታበት ጨዋታ በድሬዳዋ ከተማ የጨዋታ ዕለት የቡድን ስብስብ ውስጥ በተጠባባቂነት ሁለት ግብ ጠባቂዎችን መያዙ አግራሞትን ያጫረ ክስተት ነበር።

በርከት ያሉ ተጫዋቾች ለቀው በምትካቸው እስካሁን ድረስ አምስት ተጫዋቾች በማስረም በንቃት በገበያው እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት ድሬዳዋ ከተማዎች አዳዲስ ተጫዋቾች የወረቀት ስራ በጊዜ ማለቅ ባለመቻሉ ሁለት ግብ ጠባቂዎችን በተጠባባቂነት ከመያዝ ባለፈ ከረጅም ጊዜ ጉዳት መልስ በቅርቡ ወደ ልምምድ የተመለሱ ተጫዋቾችን ጭምር በቡድን ስብስባቸው ውስጥ አካተው ጨዋታውን አድርገዋል።

ከዚህ ቀደም በ2010 የውድድር ዘመን አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ መቐለን በያዙበት ወቅት በተመሳሳይ በጉዳት የሳሳው ቡድናቸውን ይዘው ወደ ሀዋሳ አቅንተው ከሀዋሳ አቻቸው በነበራቸው ጨዋታ በተመሳሳይ ግብ ጠባቂነት በሜዳ ውስጥ ተጫዋቾች በጨዋታ ስብስባቸው ውስጥ አስመዝግበው ጨዋታ ያደረጉበት ጊዜ የሚታወስ ነው።

ድጋፍ የሚያስፈልገው ተስፈኛው ፋሲል ገ/ማርያም

በሊጉ ውስጥ ተስፋ ካላቸው ግብጠባቂዎች አንዱ የሰበታው ፋሲል ገብረማርያም ነው። በትናንትናው ዕለት የመጀመሪያው የፕሪምየር ሊግ የቋሚነት ዕድል ያገኘው ይህ ተስፈኛ ግብ ጠባቂ በጨዋታው ለአንድ ግብ መቆጠር ምክንያት የሆነ ስህተት ቢሰራም በመጀመርያ ጨዋታው ያሳየው ብቃት ግን ተስፋ ሰጪ ነው። ከዳሽን ቢራ ተስፋ ቡድን የተገኘው እና በታዳጊ ብሄራዊ ቡድን ኢትዮጵያን የወከለው ይህ ግብጠባቂ በጨዋታው የነበረው ልበ ሙሉነት እና ድፍረት ለቀጣይ ተስፋ እንዲጣልበት ያደርጋል።


©ሶከር ኢትዮጵያ