የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከዚምባብዌ ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ ዛሬ ዝግጅት ይጀምራል ቢባልም አልተሳካም።
ቡሩንዲን በድምር ውጤት 7-1 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ያለፈው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከዚምባብዌ ጋር መጋቢት 13 በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የመጀመርያ ጨዋታውን እንደሚያደርግ ይታወቃል።
ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ ዛሬ ተሰባስበው ነገ ወደ ባህር ዳር ለማቅናት የአውሮፕላን ትኬት ተቆርጦ፣ ሆቴል ተይዞ ዝግጅታቸውን በሚጫወቱበት ሜዳ ለማድረግ ታስቦ ነበር። ሆኖም ጠዋት በአዲስ አበባ ስቴዲየም የዝግጅቱን መጀመር ለመዘገብ በተገኘንበት ወቅት የተመለከትነው የብሔራዊ ቡድኑን ጥሪ አክብረው ሪፖርት ያደረጉት የሦስት ክለቦች (ስድስት ተጫዋቾች) ናቸው። የአቃቂ ቃሊቲ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና መከላከያ የቀሩት ተጫዋቾች ለምን በቦታው አልተገኙም ?
ይህ ጉዳይ ለማጣራት ያደረግነው ጥረት ባይሳካም የሴቶች ሊግን በዋናነት የሚመራው አካል ለብሔራዊ ቡድኑ ዝግጅት ቅድሚያ ከመስጠት ይልቅ የሴቶች አንደኛ ዲቪዚዮን የመጨረሻ ሳምንት ውድድር ረቡዕ እና ሐሙስ እንዲጠናቀቅ ከመፈለግ አኳያ እንደሆነ ተገምቷል።
አሁን ባለው መረጃ ብሔራዊ ቡድኑ ዓርብ ተሰባስቦ ቅዳሜ ባህር ዳር ልምምዱን ለመጀመር ነው። ይህ ደግሞ ከጨዋታ መጥተው በቀጥታ ጠንካራ ልምምድ መስጠት ካለው ጫና አንፃር በተጨማሪም ከጨዋታው ቀን በፊት ቅዳሜ፣ የጨዋታው ቀን እሁድ ጨምሮ ያሉት አራት ቀናት ሲቀነሱ ቡድኑ የተሟላ ዝግጅት የሚያደርገው ለአራት ቀን ይሆናል ማለት ነው።
ይህ ደግሞ ለአሰልጣኙ እና ለቡድኑ አባላት ላይ ስራቸውን አስቸጋሪ ያደርገዋል። የመጀመርያውን ዙር ጨዋታውን በስኬት በማጠናቀቅ ተስፋ ሰጪ ነገር ላሳየው እና እስከ መጨረሻው ምዕራፍ ለመድረስ እገዛ ሊደረግለት የሚገባው ቤሔራዊ ቡድን የተሰጠው ትኩረት አናሳ በመሆኑ የፌዴሬሽኑ አመራሮች ትኩረት ሊሰጡት ይገባል እንላለን።
በዚህ ጉዳይ ላይ የሚቀያየሩ አዳዲስ ነገሮች ካሉ ተከታትለን እናቀርባለን።
© ሶከር ኢትዮጵያ