ፕሪምየር ሊግ 16ኛ ሳምንት | የሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ 11

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዙር ቅዳሜ እና እሁድ በተደረጉ የ16ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ተጀምሯል። በነዚህ ጨዋታዎች በአንፃራዊነት ጥሩ ብቃታቸውን ማሳየት የቻሉትን 11 ተጫዋቾችንም በሚከተለው መልኩ አቅርበንላችኋል። 

* ምርጫው የሚከናወነው የሶከር ኢትዮጵያ ሪፖርተሮች እንዲሁም ጨዋታዎችን የሚከታተሉ ባለሙያዎች ለተጫዋቾች በሚሰጡት ነጥብ መነሻነት ነው። 

* ምርጫው ተጫዋቾች በዕለቱ በተሰለፉበት ጨዋታ ላይ ባሳዩት ብቃት ላይ የተመረኮዘ ነው።

* ፎርሜሽኖች እና የተጫዋቾች ቦታዎች ምርጫውን ባማከለ መልኩ በየጊዜው ሊቀያየሩ ይችላሉ። 

አሰላለፍ ፡ 3-4-3


ቴዎድሮስ ጌትነት (ፋሲል ከነማ)

ይህ ቁመተ መለሎ የግብ ዘብ በቅዳሜው የፋሲል ከነማ እና አዳማ ከተማ ጨዋታ ያሳየው ብቃት መልካም ነበር። የቡድኑ ቀዳሚ ግብ ጠባቂ ሚኬል ሳማኬን ዘግይቶ ቡድኑን መቀላቀል ተከትሎ ተመራጭ የሆነው ይህ ተጫዋች ያገኘውን አጋጣሚ በአግባቡ በመጠቀም ተስፋዎችን አስመልክቷል። በተለይ ተጨዋቹ ቅልጥፍናን እጅግ የሚሹ ኳሶችን በማዳን የጨዋታው ክስተት ሆኖ አልፏል። ከጨዋታው በኋላም የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ተጫዋቹን አሞካሽተው በቀጣይም ቀዳሚ ተመራጫቸው እንደሚሆን ተናግረዋል።


ይበልጣል ሽባባው (ወልቂጤ ከተማ)

ወልቂጤ ከተማ አዲስአበባ ስታዲየም ላይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ወሳኝ ሶስት ነጥብ ባሳካበት ጨዋታ ላይ ይበልጣል ሽባባው በቅዱስ ጊዮርጊስ የማጥቃት ጨዋታ ውስጥ አይነተኛ ሚና ያላቸውን የመስመር አጥቂዎች ሙሉ ለሙሉ በመነጠል ረገድ እጅግ ስኬታማ ነበር ፤ በዚህም የተነሳ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ጋዲሳ መብራቴ እና አቤል ያለውን በተደጋጋሚ ቦታ እየቀያየሩ ቢሞክሯቸውም ይበልጣል ግን የሚቀመስ አልነበረም። በሙሉ 90 ደቂቃ ተጫዋቹ በአንድ ለአንድ ግንኙነት ወቅት ምን ያህል ታጋይ እንደሆነ አስመስክሯል።

አዲስ ተስፋዬ (ሰበታ ከተማ)

በዚህ ሳምንት በግላቸው ጥሩ ሳምንት ካሳለፉት ተጫዋቾች የሰበታ ከተማው ተከላካይ በቅድሚያ ይጠቀሳል። ሰበታዎች ወደ ዓድግራት አምርተው ከወልዋሎ ጋር ሁለት ለሁለት አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ምንም እንኳ ቡድኑ ሁለት ግቦች ቢያስተናግድም አዲስ ተስፋዬ በግሉ ጥሩ ቀን አሳልፏል። በጨዋታው ያገኛቸው የአንድ ለአንድ አጋጣሚዎች በሙሉ በሚባል መልኩ ያሸነፈው ደንዳናው ተከላካይ በተለይም በወሳኝ ቦታ ላይ ያቋረጣቸው የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች እና በተጠቀሰው የአንድ ለአንድ ግኑኝነቶች የነበረው ብርታት በሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ አካቶታል።

አሥራት ቱንጆ (ኢትዮጵያ ቡና)

ኢትዮጵያ ቡናን ሽረን በረታበት ጨዋታ ከወትሮው በተለየ ከመከላከሉ በበለጠ በነፃነት ኳሶችን በተጋጣሚ የሜዳ አጋማሽ ከመስመር እየተነሳ ወደ ውስጥ ሰብሮ በመግባትና ለቡድን አጋሮቹ በተለየ አጥቂዎቹ ከፍተኛ ድጋፍ ሲያደርግ ተስተውሏል። በኢትዮጵያ ቡና መለያ ካደረጋቸው ምርጥ እንቅስቃሴዎች አንዱ በነበረው የቅዳሜው ጨዋታ አስራት በሽረዎች የቀኝ መስመር በኩል እንደልብ ሲፈነጭ ተስተውሏል። በዚህም ለሁለት ግቦች መቆጠር አይነተኛ አስዋፅኦ አበርክቷል።


እድሪስ ሰዒድ (ወላይታ ድቻ)

ወላይታ ድቻ ምንም እንኳን በሲዳማ ቡና የ5ለ3 ሽንፈትን ከሜዳው ውጪ ቢያስተናግድም የመሐል ሜዳው ተጫዋች እድሪስ ሰዒድ የግል አቅም በጨዋታው ጎልቶ ወጥቷል፡፡ በሲዳማ ቡና ቡድኑ ቀድሞ ግብ ቢቆጠርበትም ከመሀል ሜዳው ወደ ሲዳማ ግብ ከተጠጋ ቦታ ላይ እጅግ ማራኪ ግብን ያስቆጠረ ሲሆን ሁለተኛዋንም ግብ በድንቅ አጨራረስ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ከዚህም በዘለለ ተጫዋቹ ለባዬ ገዛኸኝ ተደጋጋሚ ኳሶችን አመቻችቶ በመስጠቱ የተዋጣለት የነበረ ሲሆን ባዬ ገዛኸኝ ያስቆጠራት የፍፁም ቅጣት ምት የተገኘችውም በሳጥን ውስጥ በመጠለፉ የተገኘች ነበረች፡፡

ዳዊት እስጢፋኖስ (ሰበታ ከተማ)

ሰበታ ከተማዎች ከወልዋሎ ወሳኝ አንድ ነጥብ ሲያሳኩ የፈጣሪው አማካይ ሁለት ምርጥ ቅጣት ምቶች አጋዥ ነበሩ። በጨዋታው ከመቼውም ግዜ በላይ ሜዳውን አካሎ ለተጫዋቾች የቅብብል አማራጭ ሲፈጥር የነበረው አማካዩ ከሁለቱ ወሳኝ ግቦች በተጨማሪም በጨዋታው ቡድኑ ባደረጋቸው ሁለት ያለቀላቸው ንፁህ ዕድሎች ቀጥተኛ ተሳትፎ አድርጓል።

ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን (ኢትዮጵያ ቡና)

አማካዩ ቡድኑን ሽረን ሲረታ በተለይ ባልተደረጀ መልኩ ወደ በተወሰነ አካባቢ ተከማችተው ለመከላከሉ ሲሞክሩ የነበሩት የሽረ ተጫዋቾች ድክመት በመገንዘብ እጅግ በሚያስደንቅ የቦታ አረዳድ ኳስን በሰው ወዳልተጨናነቀው የሜዳ ክፍል የሚበትንበት መንገድ እጅግ ድንቅ ነበር። በጨዋታው ድንቅ እንቅስቃሴ ያደረገው ተጫዋቹ በጨዋታው ከተቆጠሩት ግቦች በስተጀርባ በነበሩት ሒደቶች ላይ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

ቢንያም ጾመልሳን (ድሬዳዋ ከተማ)

ለብርቱካናማዋቹ ድል መሪ ተዋናይ ሆኖ የዋለው ቢኒያም ተቀይሮ እስከወጣበት ሰዓት ድረስ ከአጥቂዎቹ ጀርባ በመሆን የተጋጣሚውን ተከላካይ ክፍል የሚርብሽበት መንገድ ጥሩ ነበር። እንዲሁም ከቡድኑ ሦስት ጎሎች መካከል ሁለቱን በማስቆጠር ድሬዳዋ ተከታታይ ድል እንዲያስመዘግብ ረድቷል።


ሀብታሙ ገዛኸኝ (ሲዳማ ቡና)

ሲዳማ ቡና በዚህ ሳምንት በሜዳው በግብ ተንበሽብሾ ወላይታ ድቻን 5ለ3 ሲያሸንፍ የሀብታሙ ገዛኸኝ ድርሻ ግማሹን ይይዛል። በጨዋታ በተሰለፈበት የግራ መስመር የማጥቂያ ቦታ በኩል በወላይታ ድቻ ተከላካዮች ላይ የፈጠረው ተደጋጋሚ ጥቃቶች ውጤታማ ያደረጉት ከመሆኑ ባለፈ ሦስት ግቦችን ከመረብ ሐት-ትሪክ አሳርፎ ሐት-ትሪክ መስራት ችሏል፡፡

አዲስ ግደይ (ሲዳማ ቡና)

በዚህ ሳምንት ስኬታማ ከነበሩ ተጫዋቾች መካከል እንደ አዲስ ግደይ የተሳካለት የለም ማለት ይቻላል፡፡ ተጫዋቹ ሲዳማ ቡና በሜዳው ወላይታ ድቻን በሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፎ ሲወጣ የዓመቱ ፈጣን ጎል ከማስቆጠሩ በተጨማሪ ለሀብታሙ ገዛኸኝ ሁለት፣ ለዳዊት ተፈራ አንድ ግብ አመቻችቶ በመስጠት የማቀበል የአሲስት ሐት-ትሪክ ሰርቷል፡፡

አቡበከር ናስር (ኢትዮጵያ ቡና)

በአህመድ እና አማኑኤል በጨዋታው አለመኖር ቡድኑን በአምበልነት እየመራ የገባው አቡበከር በኢትዮጵያ ቡና መለያ የመጀመሪያውን ሐት-ትሪክ የሰራበት የጨዋታ ሳምንት ነበር። በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ወደ መስመር ወጥቶ ሲጫወት የነበረው አቡበከር ወደ 9 ቁጥር ሚና ከተሸጋገረ ወዲህ ለካሳዬ አራጌው ኢትዮጵያ ቡና የፊት መስመር ሞገስን እያላበሰ ይገኛል።


ተጠባባቂዎች

ፊሊፕ ኦቮኖ (መቐለ 70 እንደርታ)

መሐመድ ሻፊ (ወልቂጤ ከተማ)

ያሲን ጀማል (ድሬዳዋ ከተማ)

አሳሪ አልመሐዲ (ወልቂጤ ከተማ)

ዳዊት ተፈራ (ሲዳማ ቡና)

ሀብታሙ ታደሰ (ኢትዮጵያ ቡና)

ኦኪኪ አፎላቢ (መቐለ 70 እንደርታ)


©ሶከር ኢትዮጵያ