ጥቂት ነጥቦች በብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ምርጫ ዙርያ..

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለ2021 የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታውን እያከናወነ ይገኛል። ከ15 ቀናት በኋላም የምድቡን ሦስተኛ እና አራተኛ ጨዋታዎች በተከታታይ ከኒጀር ጋር ከሜዳው ውጪ እና በሜዳው ሲያከናውን ለዚህ ዝግጅት ይረዳው ዘንድ ለ24 ተጫዋቾች በትናንትናው ዕለት ጥሪ አድርጓል። ምርጫውን ተመርኩዘንም ጥቂት ነጥቦችን በሚከተለው መልኩ ለማንሳት ሞክረናል።

እነማን ተመረጡ?

ከሁለት ሳምንታት በኋላ ለሚከናወኑት ጨዋታዎች ከተመረጡት 24 ተጫዋቾች መካከል 16 የሚሆኑት ባለፈው የምርጫ ወቅት የነበሩ ሲሆን 8 ደግሞ በአዲስ መልክ (ለመጀመርያ ጊዜ እና ከጊዜያት በኋላ የተመረጡ) ናቸው። በዚህም ሰዒድ ሀብታሙ (ጅማ አባጅፋር)፣ ይድነቃቸው ኪዳኔ (ወልቂጤ ከተማ)፣ ፈቱዲን ጀማል (ኢትዮጵያ ቡና)፣ ዮናታን ፍሰሀ (ሲዳማ ቡና)፣ ታደለ መንገሻ (ሰበታ ከተማ)፣ ግርማ ዲሳሳ (ባህርዳር ከተማ)፣ ሚኪያስ መኮንን (ኢትዮጵያ ቡና) እና አቤል ያለው (ቅዱስ ጊዮርጊስ) ባለፈው የማጣርያ ወቅት ያልነበሩ እና በዚህ ምርጫ ወቅት የተጠሩ ናቸው። ሰዒድ፣ ግርማ፣ ዮናታን እና ሚኪያስ ደግሞ ምርጫው ለመጀመርያ ጊዜ የደረሳቸው ናቸው። ከሀገር ውጪ ከሚጫወቱ ተጫዋቾች መካከል ደግሞ አምበሉ ሽመልስ በቀለ ብቻ ጥሪው ደርሶታል።

ምርጫው እንዴት ነበር?

አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ከዚህ ቀደም በብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች ላይ ከምርጫ ጋር በተያያዘ ዕድለኛ አልነበሩም ማለት ይቻላል። ጨዋታዎች የሚደረጉበት ወቅት ውድድር ባልነበረባቸው ወቅቶች መሆኑ ለተጫዋቾች ምርጫም ፈተና ሲሆንባቸው ተስተውሏል። አሁን ላይ ግን በሊግ ውድድር አጋማሽ ላይ በመገኘታችን የተጫዋቾችን ወቅታዊ ብቃት እና ይሆኑኛል የሚሏቸውን ተጫዋቾች ለመገምገም በቂ ጊዜ ማግኘታቸውን ተከትሎ በአግባቡ ተከታትለው ምርጫ እንደሚያደርጉ ቢጠበቅም አሰልጣኙ በካፍ ኢንስትራክተርነታቸው ምክንያት በርካታ ሥልጠናዎችን ለማከናወን ከኢትዮጵያ ውጪ መሆናቸው ይበልጥ የተጫዋቾቹን ባህርይ ለማጥናት ሁኔታዎችን አስቸጋሪ እንዳደረገባቸው መናገር ይቻላል። በዚህም በጉዳት ላይ ያሉ ወይም በጥሩ አቋም ላይ የማይገኙ አንዳንድ ተጫዋቾች ሲካተቱ በሊጉ ጎልተው የወጡ ጥቂት የማይባሉ ተጫዋቾች ደግሞ አለመካተታቸው በእርግጥ ይህ የአሰልጣኙ ምርጫ ነው? የሚሉ አስተያየቶች እንዲደመጡ ያስገደደ ይመስላል።

የብሔራዊ ቡድን ግንባታ ሒደትን ከማከናወን አኳያ ተቀራራቢ እና በየጊዜው የማይቀያየር (ለወጥነት የቀረበ) ምርጫ ቢከናወን ይመረጣል። በተለይ ቡድኑ በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ከሆነ መንፈሱን ጠብቆ ለመቆየት የተጫዋች ምርጫዎች ማለዋወጡ አዲስ ቡድን በየጊዜው እንደመገንባት የሚቆጠር ነው። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በርከት ያለ ዓለምአቀፍ የነጥብ እና ለመሞከርያ የሚሆኑ የወዳጅነት ጨዋታዎች ለማያደርጉ ሀገራትም በየምርጫው አዳዲስ ፊቶች ማከናወን የቡድነ ሥራን የሚያከብድ ነው። በመሆኑም በዚህ ረገድ የአሁኑ ምርጫ በመልካም ጎኑ ሊነሳ የሚችል ነው።

ብሔራዊ ቡድኑ በዓመቱ መጀመርያ ከማዳጋስካር እና አይቮሪኮስት ጋር ባደረጋቸው ጨዋታዎች ላይ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ሲያሳይ አሰልጣኝ አብርሀም የተጠቀሟቸው አመዛኞቹ ተጫዋቾች በዚህም ምርጫ ተካተዋል። በአጠቃላይ ባለፈው የማጣርያ ወቅት ከነበሩት 24 ተጫዋቾች መካከል በዚህ ምርጫ ላይ የ8 ተጫዋቾች ለውጥ ተደርጓል። ባለፉት ሁለት የማጣርያ ጨዋታዎች ሜዳ ገብተው ከተጫወቱ ተጫዋቾች መካከል ጋቶች ፓኖም፣ ምንተስኖት አሎ እና አቤል ማሞ ብቻ በዚህ ስብስብ ሳይካተቱ ሲቀሩ ቀሪዎቹ ስድስት ተጫዋቾች ጥሪ ብቻ የተደረገላቸውና ተሳትፏቸው እምብዛም ነበር። በአንፃሩ በመጨረሻው ጨዋታ (ከአይቮሪኮስት) በመጀመርያ አሰላለፍ ውስጥ ከተካተቱት መካከል በወቅቱ ተቀይሮ የወጣው አቤል ማሞ ብቻ ሳይጠራ ቀርቷል። ከዚሀ አንፃር ምርጫው ወጥ የሆነ ብሔራዊ ቡድን ከመፍጠር አኳያ በመልካም ጎኑ የሚነሳ እንደሆነ ጠቋሚ ነው።

በስብጥር ደረጃ ከተመለከትነው ሁለት ግብ ጠባቂዎች በሁለት ግብ ጠባቂዎች ሲተኩ በተከላካይ መስመርም በተመሳሳይ ሁለት በሁለት ተተክተዋል። በአራት አማካዮች ምትክ አንድ አማካይ (ታደለ) እና ሦስት የመስመር ተጫዋቾች ተካተዋል። ይህም ጥቂት አማራጭ ለነበረው የመስመር ቦታ አማራጭ እንደሚፈጥር ይታመናል።

እነማን ሳይካተቱ ቀሩ?

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ስብስባቸው በሀገር ውስጥ ሊግ ተጫዋቾች ለተዋቀረ ብሎም በሊጉ ከ85% በላይ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ከመሆናቸው አንፃር 24 ተጫዋቾች ብቻ ነጥሎ ምርጫ ማድረግ እጅግ በጣም ፈታኝ ነው። የክለብ ደጋፊዎች፣ የባለሙያውን እና አጠቃላይ የስፖርት ቤተሰቡን ፍላጎትን ላያረኩም ይችላሉ። አሁን አሁን የተጫዋቾች አቋም ከሳምንት ሳምንት ለመገምገም የሚያበቁ ጥቂት ግብዓቶች እና ቁጥራዊ መረጃዎች መኖራቸውም ምርጫዎችን ከቁጥሮች ጋር በማያያዝ አጨቃጫቂነት መጨመራቸው አይቀሬ ነው።

የብሔራዊ ቡድን ምርጫ ከቁጥሮች እና ከወቅታዊ አቋም ይልቅ የአሰልጣኙ እምነት የሚንፀባረቅባቸው፤ ከዛም አልፎ ልምድን ታሳቢ ተደርገው የሚከናወኑ በመሆናቸው በግርድፉ የሚታዩ ቁጥራዊ መረጃዎችን ለምርጫነት ማዋል አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። የበርካታ ውጤታማ ብሔራዊ ቡድኖች ተሞክሮም ከቁጥሮች እና ወቅታዊ አቋም ይልቅ ለአሰልጣኞች እምነት የቀረቡ ናቸው። ሆኖም ምርጫ ምንግዜም አጨቃጫቂነቱ የማይቀር ጉዳይ በመሆኑ በዚህም ምርጫ የስፖርት ቤተሰቡን ያወያዩ ተጫዋቾች አልጠፉም።

የምርጫው ዝርዝር ይፋ ሲደረግ በአብዛኛው የስፖርት ቤተሰብ አዕምሮ ውስጥ ቀድሞ የመጣው ስም ሙጂብ ቃሲም እንደሆነ አያጠራጥርም። ተጫዋቹ ዘንድሮ በወጥነት ጎል እያስቆጠረ እንደመሆኑ ለምን ከምርጫው ተዘለለ የሚሉ ድምጾች የበረከቱ ሲሆን ባለፈው የማጣርያ ወቅትም በተመሳሳይ ከመዘለሉ ጋር ተያይዞ መነጋግርያ ሆኗል። የተጫዋቹ አለመጠራት አንድም “በአሰልጣኙ እና ተጫዋቹ መካከል ያለው ግንኙነት ምን ገብቶት ይሆን?” በሌላ በኩል ደግሞ የአጨዋወት ባህርዩ ለአሰልጣኙ አጨዋወት አመቺ ካለመሆን ጋር ሊያያዝ ይችል ይሆን?” አልያም “ተጫዋቹ ለብሔሪዊ ቡድን ባደረጋቸው ጨዋታዎች አሳማኝ እንቅስቃሴ ስላላሳየ ይሆን?” የሚሉ ጉዳዮች ይነሳሉ። ያም ሆነ ይህ የሊጉ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነትን በርቀት እየመራ የሚገኝ አጥቂን በስብስብ አለማካተት ለብዙዎች ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ ነው። ጎል በሚያስፈልግበት ወቅት እንደ ሙጂብ በድንቅ ወቅታዊ ጎል የማስቆጠር መንፈስ ውስጥ ያሉ አጥቂዎች ሊያስፈልጉ ይችላሉ። ለአሰልጣኙ አጨዋወት አመቺ ባይሆን እንኳ ለሁለተኛ እቅድ ሊጠቅም ስለሚችል ማካተቱ ተገቢ ይሆን ነበር።

በዚሁ በአጥቂ ሥፍራ ላይ ለከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት እየተፎካከሩ ከሚገኙ ቀዳሚ 6 ተጫዋቾች ውስጥ የተካተተው አዲስ ግደይ ብቻ ነው። ብሩክ በየነ፣ ሀብታሙ ገዛኸኝ እና ባዬ ገዛኸኝ ያልተጠሩ ተጫዋቾች ሲሆኑ አማካዩ ፍፁም ዓለሙም ከምርጫው ተዘሏል።

በግብ ጠባቂ ሥፍራ ሀገሪቱ ላይ ካሉት እጅግ በጣም ጥቂት አማራጮች በወቅታዊ ጥሩ አቋም ላይ የሚገኙት የተመረጡ በመሆኑ ብዙም አነጋጋሪ አልነበረም ማለት ይቻላል። በተከላካይ ስፍራ ላይ ጥሩ አቋም ላይ የሚገኙት ወይም ልምዳቸው ሊጠቅም የሚችሉ እንደ ወንድሜነህ ደረጄ፣ ሥዩም ተስፋዬ፣ ያሬድ ባየህ እና አዲስ ተስፋዬ ያሉ ተጫዋቾች ከአሰልጣኙ ጥሪ ያልደረሳቸው ናቸው። የአማካይ ሥፍራ ፍፁም ዓለሙን ጨምሮ ፍቅረየሱስ ተ/ብርሀን፣ በዛብህ መለዮ፣ ዳዊት ተፈራ እና እድሪስ ሰዒድ የመሳሰሉ ጥረለ አቋም ላይ የሚገኙ ሲሆን ለሁለተኛ እቅድ የሚጠቅሙ እና የመከላከል ባህርይ ያላቸው የአማካይ ተጫዋቾች አለመካተትም በዚህ ምርጫ ላይ ታይቷል። የመስመር አጥቂው ጫላ ተሺታም ጥሪው ካልደረሳቸውና በቀጣይ ዕይታ ውስጥ ሊገቡ ከሚገባቸው ተጫዋቾች መካከል ናቸው።

ለማስታወስ ያህል ከኒጀር ጋር ለሚደረገው ጨዋታ የተጠሩ ተጫዋቾች የሚከተሉት ናቸው፡-

ግብ ጠባቂዎች (3)

ተክለማርያም ሻንቆ (ኢትዮጵያ ቡና)፣ ይድነቃቸው ኪዳኔ (ወልቂጤ ከተማ)፣ ሰዒድ ሀብታሙ (ጅማ አባጅፋር)

ተከላካዮች (7)

ፈቱዲን ጀማል (ኢትዮጵያ ቡና)፣ አሕመድ ረሺድ (ኢትዮጵያ ቡና)፣ አስቻለው ታመነ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ ደስታ ደሙ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ አንተነህ ተስፋዬ (ሰበታ ከተማ)፣ ረመዳን የሱፍ (ስሑል ሽረ)፣ ዮናታን ፍሰሀ (ሲዳማ ቡና)

አማካዮች (8)

ታፈሰ ሰለሞን ( ኢትዮጵያ ቡና)፣ ሀይደር ሸረፋ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ ታደለ መንገሻ (ሰበታ ከተማ)፣ ግርማ ዲሳሳ (ባህርዳር ከተማ)፣ ይሁን እንዳሻው (ሀዲያ ሆሳዕና)፣ ከነዓን ማርክነህ (አዳማ ከተማ)፣ ሱራፌል ዳኛቸው (ፋሲል ከነማ)፣ ሽመልስ በቀለ (ምስር ለል-መቃሳ /ግብፅ)

አጥቂዎች (6)

አማኑኤል ገብረሚካኤል (መቐለ70 እንደርታ)፣ መስፍን ታፈሰ (ሀዋሳ ከተማ)፣ አዲስ ግደይ (ሲዳማ ቡና)፣ አቤል ያለው (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ ሚኪያስ መኮንን (ኢትዮጵያ ቡና)፣ አቡበከር ናስር (ኢትዮጵያ ቡና)


© ሶከር ኢትዮጵያ