የሽረ እንዳሥላሴ ስታዲየም ጨዋታዎች ለማዘጋጀት ፍቃድ አገኘ

ስሑል ሽረዎች ከስድስት ወራት የመቐለ ቆይታ በኋላ ወደ ከተማቸው መመለሳቸው እርግጥ ሆኗል።

ላለፉት ስድስት ወራት እድሳት ላይ የቆየውና ከቀናት በፊት በዐቢይ ኮሚቴ አባላት ግምገማ የተደረገበት የሽረ እንዳሥላሴ ስታዲየም ለጨዋታ ብቁ መሆኑን ተረጋግጧል። በዚህም ላለፉት ወራት ዋና ሜዳቸውን ትግራይ ስታዲየም አድርገው ሲጫወቱ የቆዩት ስሑል ሽረዎች ወደ ዋናው ሜዳቸው ተመልሰው ሲዳማ ቡናን በ17ኛው ሳምንት ይገጥማሉ።

ባለፈው ዓመትም ተመሳሳይ መጠነኛ እድሳት ተደርጎበት የነበረው ይህ ስታዲየም በዚህ ወቅት የመጫወቻ ሜዳው ሙሉ ለሙሉ ተቀይሮ ሳር ሲለብስ የደጋፊዎች መቀመጫም የቀለም መቀባት ጨምሮ መጠነኛ ጥገና ተደርጎበታል።

ባለፈው ዓመት አቧራማ እና ለጨዋታ ምቹ አይደሉም ተብለው ጥያቄ ሲነሳባቸው ከነበሩት ሜዳዎች ውስጥ የነበረው የሽረ እንዳሥላሴ ስቴድየም የመጫወቻ ሳሩ ጥራት በተሻለ ጥሩ ደረጃ እንደተሰራ እየተነገረ ይገኛል።

© ሶከር ኢትዮጵያ