የ2012 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ውድድር ከበርካታ ችግሮቹ ጋር ስድስተኛ ሳምንት ላይ ደርሷል። እኛም በእስካሁኑ የ6 ሳምንት ጉዞ በሊጉ የተመለከትናቸው ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን በተከታዩ ፅሁፋችን ለመቃኘት ሞክረናል።
ተመጋጋቢ የሆነ የተጫዋቾች የእድገት መሰላል በሌለበት የሀገራችን እግርኳስ የታዳጊ ተጫዋቾች ልማት የተዘነጋ ጉዳይ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። በተለያዩ ወቅቶች እግርኳሱን በበላይነት ከሚመራው አካል ዋንኛ ተዋንያን እስከሆኑት ክለቦች ድረስ በቂ ትኩረት እየተሰጠውም አይገኝገም።
በተለያየ የሕይወት መስመር በግል ጥረት የእግርኳስ ህይወታቸውን መስመር ለማስያዝ ከፍተኛ መስዋትነት የሚከፍሉት እነዚሁ ታዳጊ ተጫዋቾች ወደ ከፍተኛ ደረጃ የፉክክር እግርኳስ መግቢያ ብቸኛ በር በሆነው የክለቦች ውድድር ውስጥ ታቅፈው ለመካፈል ሲታትሩ ይስተዋላል። ከብዙ ድካም እና ያልተመቻቹ ሁኔታዎች አልፈው በተለያዩ ዕድሜ እርከኖች በሚገኙ ክለቦች ታቅፈው በየዓመቱ ከመወዳደር በዘለለ በተጫዋቾቹ የእግርኳስ ህይወት ላይ የሚታዩ እምርታዎች ግን የሉም። ከዚህ የተነሳ በርካታ ወጣቶች ወደ ከፍተኛ እግርኳስ መሸጋገርያ ድልድዩን በማጣት በተለያዩ የእድሜ እርከን ክለቦች እየተዟዟሩ በመጫወት የእግርኳስ ዘመናቸውን ሲገፉ የሚስተዋሉት በአሁኑ ወቅት በፕሪምየር ሊጉ እየተሳተፉ ከሚገኙ ክለቦች ውስጥም ከሀዋሳ ከተማ፣ አዳማ ከተማ እና ወላይታ ድቻ ውጪ በታዳጊ ቡድኖች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ የሚገኝ ክለብ አለ ብሎ ለመናገር አያስደፍርም።
ከላይ የተጠቀሱት ክለቦች በሚታይ መልኩ በታዳጊ ቡድናቸው ውስጥ የሚገኙትን ተጫዋቾች ለዋናው ቡድን በማብቃት ብሎም በቂ የመጫወቻ ደቂቃ በመስጠት ረገድ ለሌሎች በአብነት የሚጠቀስ ስራን በመስራት ላይ ይገኛሉ። በተቀረ ሌሎቹ ክለቦች ግን ለይስሙላ የታዳጊ ቡድን አላቸው ከሚለው የበጀት ማስፈቀጃ እና የሪፖርት ማድመቂያ ፍጆታ በዘለለ ይህ ነው የሚባልን ስራ ሲሰሩ አይስተዋልም። በእርግጥ እንደነ አሰላ ኅብረት ፣ ጥሩነሽ ዲባባ እና ኢትዮጵያ ወጣቶች አካዳሚ አይነቶቹ በከፍተኛ ደረጃ በፉክክር ውድድሮች ላይ የሚሳተፎ ክለቦች ሳይኖራቸው ቡድኖች መያዛቸው የሚበረታታ ተግባር ቢሆንም።
በተቃራኒው በፕሪሚየር ሊግ እየተወዳደሩ የሚገኙት የተወሰኑ ቡድኖች በርካታ ሚልየን ብሮችን ለዋናው ቡድን እየመደቡ ቢንቀሳቀሱም የታዳጊዎች ልማት ላይ ከነጭርሱ እየታሰፉ የማይገኙም አልታጡም።
የዘንድሮው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ 18 ክለቦችን በሁለት ምድቦች በመክፈል ባሳለፍነው ጥር 23 መጀመሩ የሚታወስ ሲሆን ውድድሩ ባሳለፍነው ሳምንት የስድስተኛ ሳምንት መርሐግብር ላይ ቢደርስም በአወዳዳሪው አካልም ሆነ በክለቦች ዘንድ ለውድድር ዝቅ ያለ ግምት በመስጠት በርካታ ግድፈቶች እየተስዋሉ “ይህ ውድድር ባለቤት አለውን?” ለማለት እያስገደደ ይገኛል። በቀጣይ ውድድሩ የተቀመጠለትን ታዳጊዎችን ከፍ ወዳለው የውድድር እርከን የማብቃት አላማን ይመታ ዘንድ በእኛ እምነት መታረም ይገባቸዋል ያልናቸውን ጉዳዮች በተከታይ መልክ ዳሰናቸዋል።
የተጫዋቾች መታወቂያ (ቲሴራ) ጉዳይ እና ደካማ የውድድር አመራር
በፊፋ የተጫዋቾች ሁኔታን እና የዝውውር ደንብ ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው አንድ ተጫዋች በአንድ ፌደሬሽን ጥላ ስር ተመዝግቦ ወደሚወዳደር አንድ ክለብ ሲያመራ በተመዘገበበት ክለብ ስር የተጫዋችነት መታወቂያ (ቲሴራ) አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች ተካተውበት እንዲሰራለት ይደነግጋል። ይህም የተጫዋቾች መታወቂያ (ቲሴራ) ለአንድ ውድድር በቅድመ ዝግጅት ወቅት መሟላት ከሚገባቸው ጉዳዮች አንዱ ቢሆንም የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ተጫዋቾች እስከ አሁን ድረስ ይህ መታወቂያ እንደሌላቸው ለማወቅ ተችሏል።
ምንም እንኳን ውድድሩ በቅድሚያ ከተመቀጠለት የመጀመሪያ ወቅት በተለያዩ ምክንያቶች በአንድ ሳምንት ተገፍቶ የተጀመረ ቢሆንም፤ ውድድሩ ከተጀመረ ስድስት ሳምንት ቢያስቆጥርም ይህ በውድድሩ የቅድመ ዝግጅት ወቅት መከናወን የሚገባው ጉዳይ እስከ ስድስተኛ ሳምንት ድረስ መጠናቀቅ አመለመቻሉ እጅግ አስገራሚ ጉዳይ ነው።
በተመሳሳይ ውድድሩን የሚመራው አካል አስቀድመው ከተያዙ መርሐ ግብሮች ላይ ለውጦች ሲደረጉ በአግባቡ እና በወቅቱ ማሳወቅ ሲገባው ይህን ማድረግ ባለመቻሉ ክለቦችን እንዲሁም የሚድያ አካላትን (ጉዳዬ ብለው የሚከታተሉት እጅግ ጥቂት ቢሆንም) ለተለያየ እንግልት እና መጉላላት ሲዳርጉ በተደጋጋሚ ይስተዋላል። በተያያዘም ውድድሩ ስድስተኛ ሳምንት ላይ ቢደርስም እስኳሁን ለክለቦች ምንም አይነት የውጤት መግለጫ ወረቀት (ኮሚኒኬ) አለመላኩ ሌላው ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው።
የተጫዋቾች የዕድሜ ተገቢነት
በሀገራችን አጠቃላይ እንደ ማኅበረሰብ በትልቁ ደግሞ በእግርኳስ የዕድሜ ጉዳይ እንቆቅልሽ ሆኖ ቢቀጥልም በመሰል የዕድሜ እርከን ውድድሮች ላይ ደግሞ ከሚባለው በላይ አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑ እንደቀጠለ ነው። በውድድሩ ተካፋይ የሆኑት አብዛኞቹ ክለቦች የውድድሩን አላማ ጠንቅቆ ካለመረዳት እንዲሁም ከቸልተኝነት በመነጨ ተደጋጋሚ ፊቶችን በዚህ ውድድር ላይ መመልከት የተለመደ ነው።
ምንም እንኳን ለዚህ ጉዳይ ተጫዋቾችን ተጠያቂ ማድረግ ቢከብድም ከተወሰኑ የውድድሩ አላማ የገባቸው እና ለነገ የተሻሉ ተጫዋቾች ለማፍራት ከሚሰሩ ክለቦች ውጭ አብዛኛዎቹ ክለቦች በግለፅ ለውድድሩ ከተቀመጠው የዕድሜ መስፈርት በላይ የሆኑ ተጫዋቾችን ጊዜያዊ ውጤትን ፍለጋ ሲያሰልፉ መመልከት የተለመደ ጉዳይ ይሆናል።
እንደሀገር ነገ የተሻሉ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት በጋራ ክለቦች መቆም ሲገባቸው ባልተገባ አካሄድ ውጤት ለማምጣት የሚደረጉ መሰል ያልተገቡ አካሄዶች በቀጣይነት ክለቡን ከመጉዳት በዘለለ ለሀገሪቱ እግርኳስ ላይ ጤናማ ያልሆነ ተፅዕኖ ማሳደረቻው አይቀሬ ነው።
ክለቦች ለውድድሩ ትኩረት ያለመስጠት ጉዳይ
ምንም እንኳን የሀገራችን ክለቦች ከአመራር እስከ ደጋፊ ባለው ተዋረድ በተለምዶ የቡድኑ በከፍተኛ ደረጃ የሚወዳደረው ቡድን ብቻ ትኩረት የማድረግ ሀገራዊ ችግር ቢኖርም በተለየ ለዕድሜ እርከኖን ቡድኖች ነገ የዋናው ቡድን ግብዓት የሆኑ ተጫዋቾች የሚገኙበት ቢሆንም ከዋናው ቡድን በተራረፉ ቁሶችና የበጀት ድጋፉች የሚቋቋሙ መሆናቸው የማይካድ ሀቅ ነው።
በሀገራችን ባለው ጤናማ ያልሆነ የስፖርት አመራር ሳቢያ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት መሰራት የሚገባው የታዳጊዎች ልማት መሆን ሲገባው በረብጣ ሚልየኖች ባልተጠና የገንዘብ አወጣጥ ስርዓት ተጫዋቾች በማዘዋወር ጊዜያዊ ውጤትን የመሻት አዝማሚያ ነገን ተስፋ በማድረግ በየክለቦቹ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ ታዳጊዎች ተስፋ ሲያጨልሙ ይታያሉ።
ጤናማ ባልሆነ የገንዘብ አወጣጥ የክለቦቻችን የፋይናንስ ህልውና ማናጋት ከጀመረ ሰንበትበት ማለቱ የሚታወቅ የዚህ ተፅዕኖ እስከታችኛው የእድሜ እርከን ቡድኖች ድረስ መሰማት ጀምሯል። ለአብነትም በስድስተኛ ወልቂጤ ከተማ ከፋሲል ከነማ ጎንደር ላይ ጨዋታ ለማድረግ መርሃግብር ቢያዝላቸውም የወልቂጤ ከተማ ተጫዋቾች ወደ ጎንደር ማቅናት ባለመቻላቸው ፋሲል ከተማ በፎርፌ ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
ሌላኛው የክለቦች ትኩረት አለመሰጠታቸው ነፀብራቅ ውድድሩ የሚካሄድባቸው ሜዳዎች ምቹ አለመሆን ነው። ክለቦች በዋነኝነት ለዋናው ቡድኖች የሚጠቀሙባቸው ሜዳዎች ነፃ በሚሆኑባቸው ወቅቶች እንኳን ዋነኛ ሜዳቸውን ከመጠቀም ይልቅ በአቅራቢያ የሚገኙ ለውድድር ምቹ ባልሆኑ ሜዳዎች ላይ ሲደረጉ ይስተዋላል። ይህም ታዳጊ ተጫዋቾችን ለተለያዩ ጉዳቶች ሲዳርግና ህልማቸው ገና በጊዜ ሲቀጭ ይስተዋላል።
በተጨማሪም በጨዋታ እለት በሜዳ ላይ ጉዳቶች ቢከሰቱ እንኳን የመጀመሪያ የህክምና እርዳታ የሚሰጡ ተቋማት (ቀይ መስቀል፣ ጠብታ አምቡላንስ) በ20 በታች ፕሪምየር ሊግ ውድድር ላይ ሲገኙ አይስተዋልም። ይህም ከፍተኛ ጉዳቶች በጨዋታ ወቅት ቢከሰቱ የሚፈጠረውን ለመገመት አያዳግትም።
የዳኞች ምደባ
የዳኞች ምደባ ሌላው ከውድድሩ ጋር ተያይዞ ተደጋጋሚ ቅሬታ የሚነሳበት ጉዳይ ነው። ውድድሩ ምንም እንኳን በርከት ባለ የደጋፊዎች ቁጥጥር ባይታጀብም ከፍ ያለ ፉክክር የሚስተናገድበት መሆኑ ይታወቃል።
ከዚህ መነሾ የዳኝነት ምደባዎች የጨዋታዎችን ክብደት መሰረት በማድረግ መሰራት ሲገባቸው ፌዴሬሽኑ ጀማሪ ዳኞችን በተደጋጋሚ በመመደብ በርከት ያሉ ውዝግቦች እንዲነሱ ምክንያት ሲሆኑ ይስተዋላል።
ምንም እንኳን ለመሰል ጀማሪ ዳኞች መሰል ጨዋታዎች ራሳቸውን ለማብቃት በቂ ልምድ የማግኛ መድረክ መሆናቸው ቢታመንም በጨዋታች ላይ የሚደረጉት የዳኝነት ምደባዎች ትኩረት ተሰጥቶባቸው ብቃት መሠረት ያደረጉ መሆን ይገባቸዋል።
ከላይ የጠቀስናቸው እና ሌሎች ጉዳዮች በአፋጣኝ እርምት የሚሹ ናቸው። ስለሆነም ለነገ ጠንካራ ተፎካካሪ ብሔራዊ ቡድን እንዲኖረን ከፈለግን ዛሬ በእነዚህ ታዳጊዎች ልማት ላይ የምንሰራት እያንዳንዱ ነገር መልሳ እንደምትከፍለን በማሰብ አወዳዳሪው አካልም ሆነ ክለቦች በፍጥነት ለመፍትሔዎቹ በመረባረብ የተሻለ የውድድር ከባቢን ለመፍጠር መስራት ይኖርባቸዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ