በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ በአንደኛ ሳምንት መካሄድ ሲገባው በተስተካካይ መርሐግብር ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም የተካሄደው የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና የድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ በእንግዶቹ ቡድን 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ከአሰልጣኝ ኢየሩሳሌም ነጋሽ ጋር በደሞዝ ክፍያ ዙርያ በፈጠረው እሰጣ ገባ እግድ ተጥሎበት በመቆየቱ ከድሬደዋ ከተማ ጋር የሚያደርጉት የአንደኛ ሳምንት ጨዋታ ተራዝሞላቸው ዛሬ ለማድረግ ችለዋል።
እጅግ በቁጥር ጥቂት የሚባል የግብ ሙከራዎች እና ብዙም ፉክክር ያልታየበት አንደኛው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ወደ ፊት የማይሄዱ ወይም አደጋ የማይፈጥሩ እንቅስቃሴ አስመልክተውናል። የመስመር አጥቂ መሳይ ተመስገን ከቅጣት የሞከረችው እና የድሬደዋ ግብጠባቂ ሒሩት ደሴ ያዳነችባት በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል በጨዋታው የተመለከትነው ብቸኛ ግልፅ የማግባት አጋጣሚ ነው።
በመሐል ሜዳ ብልጫ የነበራቸው ድሬዎች በ34ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረውን የኢትዮ ኤሌክትሪክ ግብጠባቂ እስራኤል እና ተከላካይ ዘለቃ አሰፋ ቀድመው ሳይነጋገሩ በሰሩት ስህተት ዘለቃ አሰፋ በራሷ ላይ ባስቆጠረችው ጎል ድሬዎች ቀዳሚ መሆን ችለዋል። ግብከተስተናገደባቸው በኋላ እንቅስቃሴያቸው የወረደባቸው ኤሌክትሪኮች በክፍተ ሜዳ አጨዋወት ጎል ለማስቆጠር ከነበራቸው ድክመት የተነሳ ከቆሙ ኳሶች በዙም ትርጉም የሌላቸው ሙከራዎችን አድርገዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴ አስመልክቶን ሲቀጥል በ55ኛው ደቂቃ የድሬደዋ ተከላካይ አሳቤ ሙሶ የግል ጥረት የታከለበት ጎል ድሬዎች ማስቆጠር ችለዋል። በድሬደዋ የሜዳ ክፍል አዲስ ንጉሴ እና አሳቤ ሙሶ አንድ ለአንድ ቢገናኙም አሳቤ በጥሩ መንገድ የነጠቀችውን ኳስ ተጫዋቾችን በማለፍ ኳሱን ወደ ፊት ይዛ በመሔድ ታደለች አብርሐም የተቀበለችውን ቁምነገር ካሳ ወደ ጎልነት በመቀየር የድሬን ሁለተኛ ጎል አስቆጥረዋል።
ድሬዎች ተጨማሪ ጎል በማስቆጠር የግብ መጠናቸውን ማስፋት የሚችሉበት ሁለት ግልፅ አጋጣሚ አግኝታው ሳይጠቀሙ ቀርተዋል። በተለይ ስራ ይርታው ከእታለም አሙኑ ከተከላካዮች ጀርባ የተጣለላትን ኳስ ብቻዋን ከግብጠባቂዋ ጋር ተገናኝታ የነበረ ቢሆንም ኳሱን አጥብቃ ባለመምታቷ ምክንያት በቀላሉ የግብጠባቂዋ እስራኤል ሲሳይ ሆኗል።
አሰልጣኝ መሠረት ማኒ ያደረገችው ቅያሪ በውጤት ለውጡ ላይ ብዙም ስኬታማ ሳይሆን በመጀመርያው አጋማሽ ከነበረው ከቆሙ ኳሶች ብቻ ጎል ፍለጋ እንቅስቃሴያቸው ቀጥሎ ሰሚራ ከማል እና መሳይ ተመስገን ከፈጠሩት ዕድል ውጭ ብዙም ትርጉም ያለው ነገር አልተመለከትንም።
በመጨረሻም በጥሩ የመከላከል ጥምረት ውጤቱን አስጠብቀው በዘለቁት ድሬዎች በኩል ሁለተኛውን ጎል ያስቆጠረችው ቁምነገር ካሳ ባሳየችው ያልተገባ ባህሪ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዳ ጨዋታው በእንግዶቹ ድሬዎች 2-0 በሆነ ውጤት አሸናፊነት ተጠናቋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ