ባህር ዳር ከተማ ጉዞው የተስተጓጎለ ሌላው ቡድን ሆኗል

የ17ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ለማከናወን ወደ መቐለ አምርተው የነበሩት የጣና ሞገዶቹ እስካሁን ባህር ደር አልደረሱም።

በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል እየተከሰተ ባለው አቧራ አዘል ያልተለመደ የአየር ሁኔታ መነሻነት ጉዟቸውን ለሁለት ቀናት ያራዘሙት ባህር ዳሮች ቅዳሜ ላለባቸው የ18ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ ዝግጅታቸውን በመቀመጫቸው ከተማ ማከናወን ተስኗቸዋል። በአየር በረራ ወደ ባህር ዳር ከተማ መግባት ያልቻለው ቡድኑም ዛሬ ለሊት 10 ሰዓት በመኪና ጉዞ እንደጀመረ እና ከሰዓት ገደማ ወደ ከተማው ለመግባት እንዳሰበ ታውቋል።

ቡድኑ ዛሬ ባህር ዳር ከደረሰ በኋላም ነገ ቀላል ልምምድ በመስራት ወደ መደበኛ የልምምድ መርሐ ግብሩ እንደሚመለስ ተጠቁሟል።

በበረራው መስጓጎል ምክንያት ሲዳማ ቡና፣ ባህር ዳር ከተማ፣ ፋሲል ከነማ እና ወልዋሎ ወደየከተማቸው ለመጓዝ ችግር የገጠማቸው ሲሆን ሁኔታው በዚህ የሚቀጥል ከሆነም ከነዚህ ቡድኖች በተጨማሪ ወልቂጤ ከተማ፣ መቐለ 70 እንደርታ እና ሀዋሳ ከተማ የጉዞ ሁኔታ ላይም እክል እንደሚፈጥር ይገመታል።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ