ከነገ ጨዋታዎች አንዱ የሆነው የሀዋሳ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታን እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።
ሁለተኛውን ዙር በሽንፈት የጀመረው ሀዋሳ ከተማ ወደ ድል በመመለስ ደረጃውን ማሻሻልን አልሞ ወደ ሜዳ ይገባል።
የሀዋሳ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ) | ||||
ተሸነፈ | አሸነፈ | ተሸነፈ | አሸነፈ | ተሸነፈ |
ባሳለፍነው ሳምንት በጊዜያዊ አሰልጣኙ ብርሀኑ ወርቁ እየተመራ በድሬዳዋ ሽንፈት ያስተናገደው ቡድኑ ነገ በሜዳው በሚያደርገው ጨዋታ ከቡድኑ የዘንድሮ ባህርይ እና በጊዜያዊ አሰልጣኝ ሥር እንደመሆኑ ይዞት ሊቀርበው ስለሚችለው አጨዋወት ለመተንበይ ቢያዳግትም ኳስን ተቆጣጥሮ በፈጣን አጥቂዎቹ ጫና ለመፍጠር እንደሚገባ ይጠበቃል። ሆኖም በሊጉ ግርጌ ላይ የሚገኘው ሆሳዕና የኋላ መስመሩን አደራጅቶ የሚመጣ ከሆነ የጎል ዕድል ለመፍጠር የሚቸገረው ቡድን የሆሳዕናን የኋላ መስመር ለማስከፈት ሊቸገር ይችላል።
ተስፈኞቹ መስፍን ታፈሰ እና ብሩክ በየነን በፊት መስመሩ የያዘው ሀዋሳ ከሁለቱ ተጫዋቾች ነገም ትልቅ ግልጋሎትን ይሻል። ለሁለቱ አጥቂዎች ውጤታማነት ደግሞ የመስመር አጨዋወቱን ማሻሻልና ከአማካይ ክፍል የሚጣሉ ኳሶችን ማብዛት ይጠበቅበታል። በተለይ በጥሩ የፊት ለፊት ሩጫው የሚታወቀው ዳንኤል ደርቤ አለመኖር የማጥቃት እኖቅስቃሴው ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩ አይቀሬ ነው።
ሀዋሳ አለልኝ አዘነን በእግድ ምክንያት የማያገኝ ሲሆን ወሳኙ ተከላካይ ላውረንስ ላርቴ በአምስት ቢጫ ካርድ አይኖርም። ዳንኤል ደርቤ እና የረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ ያለው እስራኤል እሸቱም በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ ናቸው፡፡
የሀዲያ ሆሳዕና ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ) | ||||
ተሸነፈ | አሸነፈ | አቻ | ተሸነፈ | ተሸነፈ |
እንደ ሀዋሳ ሁሉ ሁለተኛውን ዙር በሽንፈት የጀመረው ሀዲያ ሆሳዕና ከወራጅ ቀጠናው ለማምለጥ ከነገው ጨዋታ ነጥብ ይዞ መውጣት ግድ ይለዋል።
የፀጋዬ ኪዳነ ማርያሙ ስብስብ ከአንደኛ ዙር ደካማ ጉዞው በመነቃቃት ከወራጅነት ለመትረፍ የዝውውር እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን የዝውውሮቹ ውጤታማነትም ከነገ ጀምሮ ባሉት ጨዋታዎች መታየት ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል። ቡድኑ በመቐለ ሲሸነፍ ከነበረው አቀራረብ ለውጥ ያደርጋል ተብሎ ባይጠበቅም የኋላ መስመሩን በማጠንከር በመልሶ ማጥቃት የኋላ ክፍሉ አስተማማኝ ያልሆነው ሀዋሳን እንደሚፈትን ይገመታል። ለዚህ ደግሞ የተስፋዬ አለባቸው ከህመም መመለስ እና የሳሊፍ ፎፋና ለጨዋታ ብቁ መሆን እንደሚያግዛቸው እሙን ነው።
ነብሮቹ አብዱልሰመድ አሊን በጉዳት ወደ ሀዋሳ ይዘው ያልተጓዙ ሲሆን አዲስ ፈራሚዎቹ ተስፋዬ አለባቸው ከሆድ ህመሙ ሲመለስ ቢኒያም ሲራጅ፣ መድሀኔ ብርሀኔ እና ሳሊፍ ፎፋናም ከቡድኑ ጋር አብረው ተጉዘዋል፡፡
እርስ በርስ ግንኙነት
– በሊጉ ከዚህ ቀደም 3 ጊዜ ተገናኝተው ሀዋሳ አንዱን ሲያሸንፍ በሁለቱ አቻ ተለያይተዋል።
– በሦስቱ ግንኙነታቸው 13 ጎሎች ተቆጥረዋል። ሀዋሳ ከተማ ሰባቱን ሲያስቆጥር ሀዲያ ሆሳዕና ስድስት አስቆጥሯል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ሀዋሳ ከተማ (4-3-3)
ሀብቴ ከድር
ወንድማገኝ ማዕረግ – መሳይ ጳውሎስ – ተስፋዬ መላኩ – ያኦ ኦሊቨር
አስጨናቂ ሉቃስ – ሄኖክ ድልቢ – ዘላለም ኢሳይያስ
መስፍን ታፈሰ – ሄኖክ አየለ – ብሩክ በየነ
ሀዲያ ሆሳዕና (4-3-3)
አቬር ኦቮኖ
ፀጋሰው ድማሙ – አዩብ በቀታ – በረከት ወ/ዮሐንስ
– ሄኖክ አርፊጮ
አፈወርቅ ኃይሉ – ተስፋዬ አለባቸው – ይሁን እንደሻው
ቢስማርክ አፒያ – ሳሊፍ ፎፋና – ቢስማርክ ኦፖንግ
© ሶከር ኢትዮጵያ