ቅድመ ዳሰሳ | ጅማ አባ ጅፋር ከ ኢትዮጵያ ቡና

በጅማ ዩኒቨርስቲ የሚደረገውን የጅማ አባጅፋር እና የኢትዮጵያ ቡናን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

በሁለት ተከታታይ የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች ሽንፈት ያስተናገዱት ጅማ አባ ጅፋሮች በ13ኛ ሳምንት ያስመዘገቡትን የሜዳቸው ድል ለመድገም እና ካሉበት የወራጅ ቀጠና ለመውጣት ኢትዮጵያ ቡናን ይገጥማሉ።

የጅማ አባ ጅፋር ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
ተሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ

ግጥግጥ ብሎ በመከላከል እና ለተጋጣሚ ቡድን ክፍተት ባለመስጠት የሚታወቀው ቡድኑ የነገውም አቀራረቡ ከዚህ እንደማይለይ ይታሰባል። በተለይ የኢትዮጵያ ቡና የኳስ ቅብብሎች በሜዳቸው ብቻ እንዲገደብ ለማድረግ ስልቶችን ቀይሶ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይገመታል። ከምንም በላይ ደግሞ በተከላካይ እና በአጥቂ መስመሩ መካከል ያለው የፊትዮሽ ስፋት እንዳይረዝም በመታተር ጨዋታውን እንደሚከውን ይታሰባል።

ከመከላከል አጨዋወቱ በተጨማሪ ፈጣን የመልሶ ማጥቃት ሒደቶችን በቅልጥፍና የሚከውነው ቡድኑ ነገም በዚህ አጨዋወቱ ቡናን ሊፈትን ይችላል። በተለይ የኢትዮጵያ ቡና ተጨዋቾች በኳስ ተስበው የሚፈፅሙትን የቦታ አጠባበቅ ስህተት በመጠቀም ጥቃቶችን ሊሰነዝር ይችላል። እርግጥ ይህ አጨዋወቱ በባህር ዳሩ ጨዋታ ተዳክሞ ቢታይም ነገ ተሻሽሎ ሊቀርብ ይችላል።

በጅማ በኩል የኤሊያስ አህመድ ብቃት ነገ ጨዋታውን ሊወስን ይችላል። ተጨዋቹ ከኳስ ጋር ያለው መስተጋብር ድንቅ ስለሆነ እና የመልሶ ማጥቃት ሂደቶችን የማፋጠን ክሂል ከፍተኛ ስለሆነ ጅማዎች ሊጠቀሙ ይችላሉ። በተጨማሪም የታታሪው አጥቂ ብዙዓየሁ ቅልጥፍና የቡናዎችን ተከላካዮች እንደልባቸው ኳስ እንዳይመሰርቱ ሊያደርግ ይችላል።

ጅማ አባጅፋር መላኩ ወልዴን ከቅጣት መልስ ሲያገኝ በእረፍት ላይ የነበረው ግብ ጠባቂው መሐመድ ሙንታሪም መመለሱ ተነግሯል። ነገር ግን አብርሀም ታምራት እና አሌክስ አሙዙ ቅጣታቸውን ያልጨረሱ ሲሆን ጋናዊው አጥቂ ያኩቡ መሐመድም ከክለቡ ጋር አይገኝም ተብሏል።

የኢትዮጵያ ቡና ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አሸነፈ አሸነፈ አቻ አቻ ተሸነፈ

በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች 9 ግቦችን ተጋጣሚ ላይ ያዘነቡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ያገኙትን የአሸናፊነት መንገድ ላለመልቀቅ እና የመጀመሪያ የሜዳ ውጪ ድላቸውን በጅማ ለማስመዝገብ 9 ሰዓትን ይጠባበቃሉ።

ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻሎችን እያሳየ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታዎችን የማሸነፊያ ቁልፍ ያገኘ ይመስላል። እርግጥ ቡድኑ ከሜዳው ውጪ ሲጫወት ድል ማስመዝገብ ቢሳነውም የቡድኑን ውህደት ከቀን ወደ ቀን በማሻሻል ደጋፊዎቹን በጨዋታ ማስደሰት ተያይዟል።

ከኳስ ጋር ምቾት ባላቸው ተጨዋቾች የተገነባው ቡድኑ አሰልጣኙ ወደሚፈልጉት መንገድ እየተንደረደረ ይመስላል። በተለይ ቡድኑ ከኳስ ጋር ያለው መስተጋብር መሻሻሉ በጎ ነገሮችን ይዞለት ሊመጣ ይችላል። በነገውም ጨዋታ ቡድኑ ኳስን በትዕግስት ከኋላ ጀምሮ በመመስረት የጅማን የግብ ክልል ለመፈተሽ እንደሚጥር ይታሰባል።

የቡድኑ ፈጣን እና ብልጥ የወገብ በላይ ተጨዋቾች ነገ የጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ ሊሆኑ ይችላሉ። በተለይ መስመሩን ይዘው የሚያጠቁት የቡድኑ አጥቂዎች የጅማን ጠንካራ የተከላካይ መስመር ለመዘርዘር ዋነኛ መሳሪያዎች ናቸው። በተጨማሪም ከመስመር ሰብረው በመግባት በሚሰነዝሩት ጥቃት ቡድኑ ሊጠቀም ይችላል።

በመስመሮች መካከል የሚዋልሉ የአማካይ ተጨዋቾች የያዘው ቡና ነገ ከፍተኛ ፈተና ከጅማ ይጠብቀዋል ተብሎ ይገመታል። ለዚህም አጨዋወት ቡድኑ ከተከላካይ ጀርባ የሚጣሉ ኳሶችን በማዘውተር የጅማን ቀዳሚ እቅድ ሊያስቀይር ይችላል ተብሎ ይታሰባል።

በቡናማዎቹ በኩል ምንም የቅጣት እና የጉዳት ዜና እንደሌለ ተነግሯል።

እርስ በርስ ግንኙነት 

በሊጉ ለአምስት ጊዜያት ተገናኝተው ጅማ ሁለት ሲያሸንፍ ቡና አንድ ድል አሳክቷል። ሁለቱን ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ጅማ አባጅፋር (4-2-3-1)

ሰዒድ ሀብታሙ

ጀሚል ያዕቆብ – ከድር ኸይረዲን – መላኩ ወልዴ – ኤልያስ አታሮ

ንጋቱ ገ/ሥላሴ – ሄኖክ ገምቴሳ

ተመስገን ደረሰ – ኤልያስ አህመድ – ኤርሚያስ ኃይሉ

ብዙዓየው እንዳሻው

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

ተክለማርያም ሻንቆ

አህመድ ረሺድ – ፈቱዲን ጀማል – ወንድሜነህ ደረጀ – አስራት ቱንጆ

ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን – ዓለምአንተ ካሳ – ታፈሰ ሰለሞን

ሚኪያስ መኮንን – አቡበከር ናስር – ሀብታሙ ታደሰ

© ሶከር ኢትዮጵያ