በትግራይ ስታዲየም የሚደረገውን ተጠባቂ የ17ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታን እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።
ወደ ድሬዳዋ አቅንተው ሽንፈት አስተናግደው ከተመለሱ በኋላ ሆሳዕናን አሸንፈው ከመሪው ጋር የነበራቸው የነጥብ ልዩነት ያጠበቡት መቐለዎች በብዙዎች ከሚጠበቀው የሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ ሦስት ነጥብ ይዞ ለመውጣት አቅደው ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይገመታል።
የባህር ዳር ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ) | ||||
አሸነፈ | አሸነፈ | ተሸነፈ | አሸነፈ | ተሸነፈ |
በመጨረሻው የሜዳቸው ጨዋታ ከቀጥተኛው አቀራረባቸው ለውጥ በማድረግ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው ለመጫወት ጥረት ያደረጉት ምዓም አናብስት በነገው ጨዋታ የሚመርጡት አጨዋወት ለመገመት ከባድ ቢሆንም የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ የሆነው ግዙፉ አጥቂ ኦኪኪ ኦፎላቢ የሚያሰልፉ ከሆነ ወደ ቀድሞ ቀጥተኛ አጨዋወታቸው ይመለሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በዚህም ቡድኑ እንደሚገመተው ቀጥተኛ አጨዋወት የሚከተል ከሆነ የቀድሞ አስፈሪው የማጥቃት ጥምረት መልሶ እንደሚያገኝ ሲታሰብ ለኳስ ቁጥጥር አመቺ በሆኑ አማካዮች የተሞላው የባህርዳር ከተማ የአማካይ ክፍል ላይ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ ግን መቸገሩ አይቀሬ ይመስላል። ነገር ግን ባህር ዳሮች ከማጥቃት ወደ መከላከል በሚያደርጉት የዘገየ ሽግግር ምክንያት ቡድኑ በጎ ነገሮችን ወደ ራሱ ሊያመጣ ይችላል። በተጨማሪም አስተማማኝ ያልሆነውን የባህር ዳር የተከላካይ ክፍል በአግድሞሽ እና ተሻጋሪ ኳሶች በመፈተን ግቦችን ሊያስቆጥሩ ይችላሉ። ከምንም በላይ ግን ፈጣኑ አጥቂን አማኑኤል የሚያስሮጡ ረጃጅም ኳሶች ከተከላካይ ጀርባ በመላክ ተጋጣሚን እንደሚፈታተኑ ይታሰባል።
መቐለዎች በነገው ጨዋታ በጉዳት ምክንያት የሚያጡት ተጫዋች የለም። ሆኖም ግን የኦኪኪ ኦፎላቢ መሰለፍ አጠራጣሪ ነው ተብሏል።
የመቐለ 70 እንደርታ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ) | ||||
አሸነፈ | ተሸነፈ | አሸነፈ | ተሸነፈ | ተሸነፈ |
የሁለተኛ ዙር የሊጉ ጨዋታዎችን በድል የጀመረው ባህር ዳር ከተማ ከመሪዎቹ ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ እና የመጀመሪያ የሜዳ ውጪ ድሉን በሰሜናዊቱ የሃገሪቱ ክፍል ለማስመዝገብ ትላንት መቐለ ገብቷል።
በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመራው ቡድኑ ከሜዳው ውጪ ሲጫወት እንደሚቸገር በተደጋጋሚ ታይቷል። እርግጥ በእንቅስቃሴ ደረጃ ቡድኑ የከፋ ብቃት ባያስመለክትም ፍሬያማ ሆኖ በጎ ነገሮችን ወደ ራሱ የማምጣት ከፍተኛ ችግር ተጠናውቶታል። በነገውም ጨዋታ ቡድኑ ከሜዳ ውጪ ያለበትን አይናፋርነት በሚገባ ቀርፎ የማይቀርብ ከሆነ በዓምና የሊጉ አሸናፊዎች ሊቀጣ ይችላል።
ድብልቅ የጨዋታ መንገድ የሚከተለው ቡድኑ ግቦችን በተለያዩ አማራጮች ለማስቆጠር ይታትራል። በተለይ በፈጣን የመስመር ላይ ሽግግሮች እና በቆሙ ኳሶች የተጋጣሚን መረብ በተደጋጋሚ ይጎበኛል። ከዚህ በተጨማሪም ኳስን በትዕግስት በማንሸራሸር እና ተከላላይ ሰንጣቂ ኳሶችን ወደ ፊት በማሾለክ የግብ እድሎችን ይፈጥራል። ከዚህ መነሻነት ነገም እንደ ከዚህ ቀደሞቹ ጨዋታዎች እንደ ተጋጣሚ ቡድን አቀራረብ እና እንቅስቃሴ ስልቱን በመቀያየር ነጥብ ይዞ ወደ ባህር ዳር ለመመለስ እንደሚሞክር ይታሰባል።
አምስት ግቦችን ለቡድኑ ያስቆጠረው ማማዱ ሲዲቤ ከጉዳት መመለሱ ለቡድኑ የፊት መስመር ስልነት ይጨምራል። በተለይ ባሳለፍነው ሳምንት ጨዋታ የግብ እድሎችን ሲያመክን ለነበረው ቡድኑ የሲዲቡ መመለስ ከፍተኛ ጥንካሬ ይለግሳል ተብሎ ይጠበቃል።
ባህር ዳሮች እንደተገለፀው ሲዲቤን ያግኙ እንጂ 3 ወሳኝ ተጨዋቾቻቸውን ሳይዙ ወደ መቐለ እንደተጓዙ ተነግሯል። በዚህም የቡድኑ አምበል ፍቅረሚካኤል ዓለሙ፣ ወሰኑ ዓሊ እና ዜናው ፈረደ ከጉዳታቸው ባለማገገማቸው ከነገው ጨዋታ ውጪ ናቸው። በተጨማሪም ቡድኑን ከቀናት በፊት የተቀላቀለው ሄኖክ አወቀ ከቡድኑ ጋር በቂ ልምምድ ባለመስራቱ ምክንያት ወደ መቐለ አለመጓዙ ተጠቁሟል።
እርስ በርስ ግንኙነት
ሁለቱ ቡድኖች በፕሪምየር ሊጉ ሦስት ጊዜ ተገናኝተው ባህር ዳር ሁለት ሲያሸንፍ መቐለ አንድ አሸንፏል። ባህር ዳር አራት፤ መቐለ ሦስት ጎሎች አስቆጥረዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
መቐለ 70 እንደርታ (4-4-2)
ፍሊፕ ኦቮኖ
ሥዩም ተስፋዬ – አሌክስ ተሰማ – ቢያድግልኝ ኤልያስ – አስናቀ ሞገስ
ዮናስ ገረመው – ሙሉጌታ ወ/ጊዮርጊስ – አልሀሰን ካሉሻ – ያሬድ ከበደ
ኦኪኪ አፎላቢ – አማኑኤል ገብረሚካኤል
ባህር ዳር ከተማ (4-3-3)
ሀሪስተን ሄሱ
ሚኪያስ ግርማ – አዳማ ሲሶኮ – አቤል ውዱ – ሳሙኤል ተስፋዬ
ሳምሶን ጥላሁን – ዳንኤል ኃይሉ – ፍፁም ዓለሙ
ግርማ ዲሳሳ – ማማዱ ሲዲቤ – ሳላምላክ ተገኝ
© ሶከር ኢትዮጵያ