ሰበታ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስን በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚያገናኘው ጨዋታን እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።
በ12ኛው ሳምንት ሀዲያ ሆሳዕናን ካሸነፉ በኋላ ላለፉት አራት ሳምንታት ሙሉ ሦስት ነጥብ ማግኘት ያልቻሉት ሰበታዎች ደረጃቸውን ለማሻሻልም ሆነ ባሉበት ደረጃ ለመርጋት ከዚ ወሳኝ ጨዋታ ነጥብ ማግኘት የግድ ይላቸዋል።
የሰበታ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ) | ||||
አቻ | ተሸነፈ | አቻ | ተሸነፈ | አሸነፈ |
ባለፈው ሳምንት ከሜዳቸው ውጭ የሁለት ለባዶን ውጤት በመቀልበስ ትልቅ ተጋድሎ ያሳዩት ሰበታዎች በበርካታ ጨዋታዎች የታየባቸው ንፁህ የግብ ዕድልን የመፍጠር ክፍተት ካልቀረፉ አሁንም ግቦችም ለማስቆጠር እንደሚቸገሩ ይታመናል። በጨዋታዎች በአጨዋወታቸው ወሳኝ ሚና ያላቸውን ተጫዋቾች አጥተውም የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ የማይቸገሩት ሰበታዎች በነገው ጨዋታም ከተጋጣሚያቸው የአማካይ ክፍል ጥንካሬ አንፃር በኳስ ቁጥጥር ረገድ ይቸገራሉ ተብለው ባይገመትም ቡድኑ በሦስተኛው የሜዳ ክፍል ሲደርስ ያለውን የፈጠራ እጥረት እና የአማራጮች ጥበት መላ ማበጀት ይጠቅባቸዋል።
በመጀመርያው ዙር አጋማሽ አከባቢ የተጠቀሰውን የግብ የዕድሎች መፍጠር ድክመት በመስመር ተጫዋቾች ለመተግበር ጥረት ሲያደርጉ የታዩት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በነገው ጨዋታም ባለፈው ሳምንት ጥሩ በተንቀሳቀሰው አስቻለው ግርማ እና ናትናኤል ጋንቹላ አማካኝነት ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። በተለይም ባለፈው ጨዋታ ብቻውን ተነጥሎ ፍሬያማ መሆን ያልቻለው አጥቂው ፍፁም ገብረማርያም ወደ አጨዋወቱ ይበልጥ ለማሳተፍ የመስመር ተጫዋቾቹን እና የአጥቂ አማካዮቹን ድጋፍ እንደሚሻ በግልፅ ታይቷል።
ሰበታዎች በነገው ጨዋታ መስዑድ መሐመድ በግል ጉዳይ ከቡድኑ ርቆ በመቆየቱ ፤ ጃኮ አረፋት በወረቀት ጉዳዮች ምክንያት እና ከዕረፍት ያልተመለሰው ዳንኤል አጃይን አያሰልፉም። በአንፃሩ ባኑ ዲያዋራ ከቅጣት መልስ ቡድኑን ያገለግላል።
የቅዱስ ጊዮርጊስ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ) | ||||
ተሸነፈ | አቻ | አቻ | አሸነፈ | አሸነፈ |
ከሰዓታት በፊት ዋና አሰልጣኙን ጨምሮ የአሰልጣኞች ቡድኑን ያገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ በተጫዋቾች መሪነት ወደ ሜዳ ይገባል።
ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ካለወትሮ ተዳክመው ደካማ እንቅስቃሴ ያሳዩት ፈረሰኞቹ በሊጉ አናት ለመቆየት ከዚ ጨዋታ ነጥብ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል። ከዋና አሰልጣኙ ውጭ ወደ ጨዋታ የሚገባው ቡድኑ በነገው ዕለት ይዞት የሚገባውን አቀራረብ ለመገመት ቢከብድም ባለፉት ሁለት ሳምንታት የታየው ግልፅ የጨዋታ እቅድ ከሌለው አቀራረብ ግን ለውጦች ይጠበቃሉ።
ባለፉት ጨዋታዎች ሳልሀዲን ስዒድ በሜዳ ውስጥ በቆየባቸው ደቂቃዎች ቀጥተኛ አጨዋወት ጌታነህ ከበደ የማጥቃት ክፍሉ በሚመራበት ወቅትም አማካዮችን በብዛት የሚያሳትፈው መሀል ለመሀል የሚደረግ የማጥቃት አጨዋወት የነበረው ቡድኑ በነገው ጨዋታ ጌታነህ ከበደን በፊት አጥቂነት ያስጀምራል ተብሎ ስለሚገመት መሀል ለመሀል የሚደረገው የማጥቃት አጨዋወት መርጦ ይገባል ተብሎ ይገመታል። ሆኖም ቡድኑ በተጋጣሚ አማካዮች የሚጠብቀውን ፈተና ቀላል ይሆንለታል ተብሎ አይታሰብም። ቡድኑ በተጠቀሰው ቦታ ያለው ውጤታማነትም የጨዋታው ውጤት የመወሰን አቅም አለው።
በተጨሪም ከሰሞነኛ የአቋም መውረድ ጋር በተያያዘ ከፍ ያለ ተቃውሞ እያስተናገዱ የሚገኙት የተወሰኑ የክለቡ ተጫዋቾች በነገው ጨዋታ የተሻሻለ እንቅስቃሴ የማሳየት ግዴታ ውስጥ ሆነው የነገው ጨዋታ ያደርጋሉ።
ፈረሰኞቹ ለዓለም ብርሀኑ፣ ናትናኤል ዘለቀ እና አቤል እንዳለ በጉዳት፤ ደስታ ደሙ በቅጣት ምክንያት አያሰልፉም።
እርስ በርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ሰባት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ አራቱን በማሸነፍ የበላይነት አለው። በሁለቱ አቻ ሲለያዩ በአንዱ ሰበታ አሸንፏል።
– በግንኙነታቸው ጊዮርጊስ 7፤ ሰበታ 3 አስቆጥረዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ሰበታ ከተማ (4-3-3)
ፋሲል ገብረሚካኤል
ጌቱ ኃይለማርያም – አንተነህ ተስፋዬ – አዲስ ተስፋዬ – ኃይለሚካኤል አደፍርስ
ታደለ መንገሻ – ደሳለኝ ደባሽ – ዳዊት እስጢፋኖስ
አስቻለው ግርማ – ፍፁም ገብረማርያም – ናትናኤል ጋንቹላ
ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-2-3-1)
ፓትሪክ ማታሲ
ሄኖክ አዱኛ – አስቻለው ታመነ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ – መሐሪ መና
ያብስራ ተስፋዬ – ሙሉአለም መስፍን – ሀይደር ሸረፋ
ጋዲሳ መብራቴ – ጌታነህ ከበደ – አቤል ያለው
©ሶከር ኢትዮጵያ