በ8ኛ ሳምንት የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ መከላከያ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ድል ሲቀናቸው ደደቢት እና ሎዛ አበራ ግብ ማምረታቸውን ቀጥለዋል

 

ከእለተ እሁድ የጀመረው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ማዕከላዊ-ሰሜን ዞን 8ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ በተደረጉ 2 ጨዋታዎች ተገባዷል፡፡ ዛሬ በተደረጉ ጨዋታዎችም መከላከያ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለድል ሆነዋል፡፡

በ9፡00 ኤሌክሪክን የገጠመው ቅዱስ ጊዮርጊስ 4-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡ ኤሌክትሪኮች በጽዮን ፈየራ ግብ ቀዳሚ መሆን ቢችሉም ፣ ከግቡ መቆጠር በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስ አስናቀች ትቤሶ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዶበት አመዛኙን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በ10 ተጫዋቾች ቢጫወትም በተጋጣሚው ላይ 4 ግብ ከማስቆጠር አላገደውም፡፡ ለብሄራዊ ቡድን ተመርጣ ሪፖርት ባለማድረጓ ከቡድኑ ውጪ የሆነችው ትዕግስት ዘውዴ ባስቆጠረቻቸው ግቦች ታግዞ ቅዱሰ ጊዮርጊስ በ2-1 መሪነት የመጀመርያው አጋማሽ አጠናቋል፡፡ ከእረፍት መልስ ትመር ጠንክር እና አምበሏ ሄለን ሰይፉ ተጨማሪ ግቦች አክለው ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

በ11፡00 መከላከያ ልደታን በቀላሉ 3-0 አሸንፎ ከመሪው ጋር ያለውን ርቀት መልሶ አጥብቧል፡፡ የመጀመርያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ካለ ግብ የተጠናቀቀ ሲሆን የልደታዋ ግብ ጠባቂ ወሃዚት ገበየሁ ከግብ ክልሏ ርቃ በመውጣት ጭምር የመከላከያን ሙከራዎች ማዳን ችላለች፡፡ ከመከላከያ የድል ግቦች መካከል ሁለቱን ምስር ኢብራሂም ከመረብ ስታሳርፍ ተቀይራ የገባችው ፍቅርተ ብርሃኑ ሶተኛውን ግብ ከመረብ አሳርፋለች፡፡ በጨዋታው የመከላከያዋ ግብ ጠባቂ ማርታ በቀለ በሰራችው ጥፋት በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥታለች፡፡

እሁድ በተደረገ ብቸኛ ጨዋታ ጎንደር ላይ ዳሽን ቢራ ሙገር ሲሚንቶን አስተናግዶ ካለግብ አቻ ሲለያይ ሙገር ሲሚንቶ በውድድር ዘመኑ የመጀመርያውን ነጥብ ማግኘት ችሏል፡፡

ማክሰኞ እለት በተደረጉ ጨዋታዎች ደደቢት ሲያሸንፍ እቴጌ የውድድር ዘመኑን የመጀመርያ ነጥብ አሳክቷል፡፡
ደደቢት ቅድስት ማርያምን 5-0 በረታበት ጨዋታ ሎዛ አበራ ሁለት ግቦች ከመረብ ስታሳርፍ ሰናይት ባሩዳ ፣ ወይንሸት ጸጋዬ እና ውባለም ፀጋዬ አንድ አንድ ግብ አስቆጥረዋል፡፡ ሎዛ አበራ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ባደረገቻቸው 7 ጨዋታዎች በሙሉ ግብ ማስቆጠር ስትችል ከመረብ ያሳረፈቸው የግብ መጠንም በአስገራሚ ሁኔታ 21 ደርሷል፡፡

ተከታታይ ሽንፈቶችን ያስተናገደው ኢትዮጵያ ቡና ከእቴጌ ጋር ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል፡፡ ቁምነገር ካሳ ለኢትዮጵያ ቡና ስታስቆጥር ዘነበች ዘውዱ ለእቴጌ አስቆጥራለች፡፡ ይህ ውጤት የሊጉ ደካማ ቡድን እቴጌ የውድድር ዘመኑን የመጀመርያ ነጥብ እንዲያስመዘግብ አስችሎታል፡፡

የፕሪሚየር ሊጉ መካከለኛ – ሰሜን ዞን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ በሚያደርገው ዝግጅት ምክንያት እስከ መጋቢት መጀመርያ ድረስ ይቋረጣል፡፡ የ9ኛ ሳምንት ጨዋታዎችም ከመጋቢት 2 ጀምሮ ይቀጥላሉ፡፡

የመካከለኛ-ሰሜን ዞን የደረጃ ሰንጠረዥ ይህንን ይመስላል፡-

8

 

ያጋሩ