ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዝግጅት ጀምሯል

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከዚምባብዌ ጋር ለሚያደርገው የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታ ባልተሟላ ስብስብ ዝግጅቱን ማምሻውን በአዲስ አበባ ስታዲየም ጀምሯል።

ከታሰበበት ቀን ዘግይቶ ዝግጅቱን የጀመረው ብሔራዊ ቡድኑ ጥሪ ከተደረገላቸው 23 ተጫዋቾች መካከል 13 ተጫዋቾች በመያዝ ነው ማምሻውን ከወልቂጤ ከተማ እና ከአዳማ ከተማ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ቀለል ያለ ልምምዱን በአዲስ አበባ ስታዲየም ያከናወነው።

ባለፉት ቀናት ከተደረጉ የሴቶች ፕሪምየር ሊግ የአንደኛው ዙር የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች ውስጥ ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች ነገ ብሔራዊ ቡድኑን እንደሚቀላቀሉ ይጠበቃል። ሆኖም ትናንት እና ከትናንት በስቲያ ጨዋታ አድርገው አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች ብሔራዊ ቡድኑን ሲቀላቀሉ የአዳማ ከተማ ተጫዋች የሆኑት እምወድሽ ይርጋሸዋ፣ ናርዶስ ጌትነት፣ ነፃነት ፀጋዬ፣ ገነት ኃይሉ፣ ምርቃት ፈለቀ እና የምስራች ላቀው የብሔራዊ ቡድኑን ጥሪ አክብረው አለመገኘታቸው ቸልተኝነታቸውን የሚያሳይ ነው።

አስቀድሞ ጥሪ ከተደረገላት ተጫዋች አንዷ የነበረችው አማካይ ሲሳይ ገብረ ዋህድ ጉዳት ላይ መሆኗን ተከትሎ በእርሷ ምትክ የድሬደዋ ከተማዋ ማዕድን ሳህሉ ጥሪ ተደርጎላት ቡድኑን ተቀላቅላለች።

የቡሩንዲ አቻውን በድምር ውጤት 7-1 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ያለፈው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ቀጣይ ተጋጣሚውን በደርሶ መልስ ውጤት በማሸነፍ ጥሩ ውጤት እንዲያስመዘግብ ፌዴሬሹን አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ መልክታችን ነው።

ቡድኑ ከዚምባብዌ ጋር እሁድ መጋቢት 13 በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የመጀመርያ ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል።

©ሶከር ኢትዮጵያ