ሪፖርት | ድሬዳዋ እና ፋሲል ያለ ጎል ተያይተዋል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 17ኛ ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ቀን ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከተማ ዐፄዎቹን ያስተናገደበት ጨዋታ ያለምንም ግብ ተጠናቋል።

ድሬዳዋ ባለፈው ሳምንት ሀዋሳን ከረታበት ጨዋታ በቅጣት ባልተሰለፈው ፍሬድ ሙሸንዲ ምትክ ከድር አዩብን እንዲሁም በቢኒያም ጾመልሳን ምትክ አዲስ ፈራሚው እንዳለ ከበደን በማሰለፍ ጨዋታውን ጀምሯል። ዐፄዎቹ በበኩላቸው አዳማን ካሸነፈው ስብስብ በቅጣት ባልተሰለፈው ከድር ኩሊባሊ ምትክ ሰዒድ ሀሰንን በመሐል ተከላካይነት በመጠቀም ኦሴ ማዊሊን በዓለምብርሀን ይግዛው ምትክ በመጠቀም ጨዋታቸውን ጀምረዋል።

በመጀመርያው አጋማሽ ዐፄዎቹ በተጋጣሚያቸው የሜዳ አጋማሽ አመዝነው ኳሶችን ሲያንሸራሽሩ ባለሜዳዎቹ በአንፃሩ በረጃጅም ኳሶች የጎል ዕድል ለመፍጠር ጥረዋል። ወደ ጎል በመድረስ ረገድ የተሻሉ የነበሩት ፋሲል ከነማዎች በ7ኛው ደቂቃ ሙጂብ ቃሲም የብርቱካናማዋቹ ተከላካዮችን አልፎ አደጋ ሳይፈጥር የቀረበት ሙከራ መሪ ልታደርጋቸው የምትችል የ90 ደቂቃው የጠራች የግብ ዕድል ሆና ተመዝግባለች። በረጅም ኳስ አማካይነት ጥቃት ሲሰነዝሩ በተስተዋሉት ድሬዳዋዎች በኩል ደግሞ በ20ኛው ደቂቃ ሪችሞንድ ኦዶንጎ ከርቀት የመታት ኳስ ኢላማዋን ሳትጠብቅ ቀርታለች።

ንፁህ የግብ ዕድል ባላስመለከተው የመጀመሪያው አጋማሽ በእንግዶቹ በኩል ኳስ መስርተው ወደፊት ቢጓዙም የተጋጣሚያቸው ሦስተኛ የሜዳ ክፍል ላይ ሲደርሱ በዛሬው ጨዋታ በመከላከሉ ደረጃ ጠንካራ የነበሩት ድሬዳዋችን ሰብሮ መግባት ተስኗቸው ታይተዋል። በተለይም የፋሲል እንቅስቃሴ መጂብ ቃሲም ላይ ትኩረት ያደረገ በመሆኑ ለድሬዎች የመከላከል ሂደት አመቺነቱ ከፍ ያለ ነበር። ጥንቃቄ የመረጡት ምክትል አሰልጣኝ ፍስሐ ጥዑመልሳን ቡድኑ በራሱ ሜዳ በቁጥር ተበራክቶ በመቆየት የተጋጣሚውን እንቅስቃሴ እንዲቆጣጠር በማድረጉ በኩል ተሳክቶላቸው ታይተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ከመጀመሪያው በተሻለ የማጥቃት ፍላጎት የተስዋለበት ነበር። በ60ኛው ደቂቃ የብሩቱካናማዋቹ ቡድን የመስመር ላይ ተጫዋች አማረ በቀለ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ከርቀት የመታው ኳስ በአግዳሚው ለጥቂት ከፍ ብሎ ወጥቶበታል። በድጋሚ በ77ኛው ደቂቃም ያሲን ጀማል ከርቀት ሌላ ጥቃት መሰንዘር ችሎ ነበር።

በጨዋታው በሁለቱም ተጋጣሚዎች በኩል የተከላካይ ክፍሎቻቸው ጥንካሬ ጎልቶ መውጣቱ ሳጥን ውስጥ ከሚሞከሩ ኳሶች ይልቅ ይልቅ ከርቀት የሚደረጉት የማስቆጠር ጥረቶች ሚዛን ደፍተው የታዩበት ነበር። በዚህም ድሬዎች ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት ግብ ፍለጋቸውን ቀጥለው የነበር ሲሆን በ88ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ፈራሚው እንዳለ ከበደ ግብ ቢያስቆጥርም ሳይፀድቅ ቀርቷል። ምክንያቱ ደግሞ ኳሱ በተሻማበት ወቅታ ሪችሞንድ ኦዶንጎ በግብ ጠባቂው ላይ ጥፋት ፈፅሟል በሚል ነበር።

የሊጉ መሪ ፋሲል ከነማ ወደ ድሬ ሳጥን ሰብሮ መግባት ከብዶት በታየበት የዛሬው ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ ሱራፌል ዳኛቸው እና በዘብህ መለዮ ሲያደርጉት ከነበረው የግል ጥረት እና የግብ ሙከራ ውጪ ተፅዕኖ ባልነበረው እንቅስቃሴ ኳስን በማሸረሻር አብዛኛውን ደቂቃ አሳልፏል። ጨዋታውም ምንም ግብ ሳይታይበት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ፋሲሎች ሊጉን አጠናክረው የሚመሩበትን ዕድል ሲያባክኑ ድሬዳዋም ከወራጅ ቀጠናው በደንብ ሊያርቀው እንዲሁም ከበላዩ ካሉት ቡድኖች ያለውን ልዩነት ሊያጠብ የሚችልበትን አጋጣሚ አምክኗል።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ