ሪፖርት |  ጅማ አባ ጅፋር እና ኢትዮጵያ ቡና ድራማዊ በሆነ መልኩ በአቻ ውጤት ተለያይተዋል

በ17ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጅማ ላይ አባ ጅፋር ኢትዮጵያ ቡናን ያስተናገደበት ጨዋታ በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠሩ ግቦች 1-1 ተጠናቋል።

ጅማ አባ ጅፋር ሳምንት በባህር ዳር ሽንፈት ከቀመሰው ስብስቡ ውስጥ ኤልያስ አታሮ ፣ ተመስገን ደረሰ እና ኤርሚያስ ኃይሉን በማሳረፍ ለመላኩ ወልዴ፣ አመረላ ደልታታ እና ሱራፌል ዐወል የመሰለፍ ዕድል ሰጥቷል። ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ በ16ኛው ሳምንት ስሑል ሽረን ከረታው ቡድናቸው ውስጥ ኃይሌ ገብረተንሳይ እና ዓለምአንተ ካሳን በአህመድ ረሻድ እና ሬድዋን ናስር ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ምንም እንኳን የጠሩ የግብ ዕድሎች ባይታዩበትም ሁለቱም ቡድኖች በተለያዩ የጨዋታ ዕቅዶች የተንቀሳቀሱበት ነበር። አጋማሹ በኢትዮጵያ ቡና ግልፅ የሆነ የማጥቃት ፍላጎት እንዲሁም በጅማዎች የመልሶ ማጥቃት አቀራረብ መካከል ጥሩ ፉክክር ታይቶበታል። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች አቡበከር ናስር እና ሀብታሙ ታደሰ ጥሩ የማግባት አጋጣሚዎች ቢያገኙም መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። በግልፅ የመልሶ ማጥቃት ፍላጎት ወደ ጨዋታው የገቡት ጅማዎች በብዙአየሁ እንዳሻው ፍጥነት ላይ የተመሠረቱ ጥቃቶችን ለመሰንዘር ሞክረዋል ፤ በተለይም ብዙአየሁ እና ሱራፌል አወል በ20ኛው እና በ27ኛው ደቂቃ ላይ ያመከኗቸው ኳሶች ተጠቃሽ ነበሩ። በ38ኛው ደቂቃ ደግሞ አቡበከር ናስር እና አቤል ከበደ በቅብብል ወደ ጅማ ግብ ክልል ውስጥ በመግባት አቡበከር ወደ ግብ ቢሞክርም ግብ ጠባቂው በቀላሉ ሊይዝበት ችሏል።

የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ከመጀመሪያው አንፃር በግብ ሙከራዎች እንዲሁም በእንቅስቃሴ ለውጥ ያላሳየ ነበር። አቡበርከር ናስር በ59ኛው ደቂቃ ከተከላካዮች ስህተት በፍጥነት በመድረስ የሞከረው ኳስ ወደ ውጪ የወጣበት እንዲሁም ሚካያስ መኮንን እና አቤል ከበደ ያደረጓቸው የግብ ሙከራዎች ውጪ ግልፅ የግብ ዕድል በእንግዶቹ በኩል ሳይታይ ቆይቷል። በተቃራኒው በመልሶ ማጥቃት መጫወት ምርጫቸው ባደረጉት አባ ጅፋሮች በኩል ኤርምያስ ኃይሉ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው አድኖበታል። ከዚህም በተጨማሪ ባለሜዳዎቹ ከማዕዘን ምት መነሻነት ጫና ለመፍጠር ሲሞክሩም ታይቷል።

ጨዋታው በዚህ መልኩ ያለግብ ለመጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው በሁለቱም ቡድኖች በኩል ግቦች ተቆጥረዋል። ግብ በማስቆጠሩ ቅድሚያ የነበራቸው ኢትዮጽያ ቡናዎች በአቡበከር ናስር አማካይነት 89ኛው ደቂቃ ላይ ኳስ እና መረብን አገናኝተው አሸናፊ መሆናቸውን ሊያውጁ በተቃረቡበት ቅፅበት ጅማዎች ምላሽ ሰጥተዋል። ጨዋታው ከመሐል ሜዳ ሲጀምር የኢትዮጵያ ቡናው ግብ ጠባቂ ተክለማሪያም ሻንቆ ስህተት ታክሎበት ኤርምያስ ኃይሉ ያገኘውን ዕድል ወደ ግብ ቀይሮ ጅማ አባ ጅፋር ነጥብ መጋራት ችሎ በስታድየሙ የተገኘውን ደጋፊ ጮቤ አስረግጧል።

ጨዋታው 1-1 መጠናቀቁን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና 21 ነጥብ በመሰብሰብ 8ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ በአንፃሩ ጅማ አባ ጅፋር በ19 ነጥብ በወራጅ ቀጠናው ለመቆየት ተገዷል።

© ሶከር ኢትዮጵያ