የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አይቋረጥም

ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ሲባል ከነገ ጀምሮ እንደሚቋረጥ ተገልጾ የነበረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የማጣሪያ ጨዋታዎች በመሰረዛቸው ምክንያት ሊጉ እንደሚቀጥል የሊግ ካምፓኒ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በቅርቡ ከኒጀር ብሔራዊ ቡድን ጋር ላለበት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ሲባል የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛው ዙር ጨዋታ ጀምሮ ሁለት መርሀግብሮች ከተደረጉ በኋላ ፕሪምየር ሊጉ እንደሚቋረጥ በቅርቡ በጂፒተር ሆቴል በነበረው የአንደኛው ዙር የሊጉ ግምገማ ላይ መገለፁ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ከዛሬ የ17ኛው ሳምንት ጨዋታ በኃላ ለሀያ አንድ ቀናት ይቋረጣል የተባለው ውድድር እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ካምፓኒ ይፋ አድርጓል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የአፍሪካ እግር ኳስ የበላይ አካል ካፍ ከኮሮና ቫይረስ ሥጋት ጋር በተያያዘ የአፍሪካ ውድድሮች ለተወሰኑ ጊዜያት እንዳይካሄዱ በመወሰኑና ኢትዮጵያም ከኒጀር ጋር የነበራትን ጨዋታ ስለማታከናውን ሊጉ እንዲቀጥል ምክንያት ሆኗል፡፡

ሊጉ እንደሚቀጥል ከመገለፁ ውጪ የ18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መቼ እንደሚደረጉ ያልተገለፀ ሲሆን በአዲስ የመርሀ ግብር ሽግሽግ ተደርጎ ይፋ እስከሚደረግ ድረስ ክለቦች ተጫዋቾችን ለዕረፍት እንዳይበትኑ አሳስቧል።

በኢትዮጵያ /አዲስ አበባ/ በዛሬው ዕለት ቫይረሱ በአንድ ጃፓናዊ ግለሰብ ላይ መገኘቱ መረጋገጡ የሚታወስ ነው።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ