ሪፖርት | ስሑል ሽረ በድል ወደ ሜዳው ተመልሷል

በ17ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሜዳቸው ጥገና ላይ መቆየቱን ተከትሎ ለ6 ወራት በትግራይ ኢንተርናሽናል ስታድየም ሲጫወቱ የቆዩት ስሑል ሽረዎች ወደ ከተማቸው ተመልሰው ባደረጉት የመጀመርያ ጨዋታ ሲዳማ ቡናን በጠባብ ውጤት አሸንፈዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና የግማሽ ደርዘን ጎሎች አሰቃቂ ሽንፈት የተከናነቡት ባለሜዳዎቹ በአዲሱ ሜዳቸው ድል ቀንቷቸዋል። ስሑል ሽረዎች ሳምንት ከተሸነፉበት ስብስብ ዉስጥ ያልተካተቱትን ግብ ጠባቂው ወንድወሰን አሸናፊ ፣ ያስር ሙገርዋ፣ ዓብዱልለጢፍ መሐመድ እንዲሁም አዲስ ያስፈረሙት ጋናዊዉን ራሂም ኦስማኖን በማካተት ወደ ሜዳ ገብተዋል። በሲዳማ ቡና በኩል ደግሞ ወላይታ ድቻን ካሸነፈው ስብስብ መካከል ግርማ በቀለን በዮሴፍ ዮሐንስ፣ ብርሀኑ አሻሞን ዳዊት ተፈራ ምትክ በመጠቀም ጨዋታውን ጀምረዋል።

በሁለቱም ቡድኖች በኩል ማራኪ እንቅስቃሴ ባልታየበት የመጀመሪያዉ አጋማሽ ቀድመው ወደ ጎል የቀረበ ሙከራ ያደረጉት እንግዶቹ ሲዳማ ቡናዎች ነበሩ። በ10ኛዉ ደቂቃ በተሻለ መልኩ የስሑል ሽረ ተከላካዮችን ሲያሸብር የዋለው ሀብታሙ ገዛኸኝ ተከላካዮችን አታሎ በማለፍ ያሻገረለትን ኳስ አጥቂዉ አዲስ ግደይ ከግብ ጠባቂው ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በአዲስ ግደይ የመጀመሪያ ሙከራ የተነቃቁት ሲዳማ ቡናዎች ከአማካይ ተጫዋቾች በረጅሙ ወደ ሀብታሙ በሚላኩ ኳሶች በመጠቀም ለማጥቃት ሞክረዋል። በዚህም ምንም እንኳን ለጥቂት ደቂቃዎች ቢሆንም ስል የሆነዉ የማጥቃት አቅማቸዉን አሳይተዋል። በ13ኛዉ ደቂቃ ሀብታሙ ከሩቅ አክርሮ የመታው ኳስ ወደ ላይ ወጥቷል።

ባለሜዳዎቹ ሽረዎች በ15 ደቂቃው የተወሰደባቸው ብልጫ ለመቀልበስና ወደ ራሳቸው ሪትም ለመምጣት ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። በዚህ ምክንያትም በ18ኛዉ ደቂቃ በቀኝ ተከላካዩ ዓወት ገ/ሚካኤል የተሻማዉ ኳስ ጋናዊ ዓብዱልለጠፍ መሃመድ ለአዲሱ አጥቂ ራሂም ኦስማኖ በጭንቅላቱ አመቻችቶ ቢያቀብለዉም ግዙፉ የሲዳማ ቡና ግብ ጠባቂ መሳይ አያኖ አድኖበታል። ባለሜዳዎቹ ተነቃቅተዉ በተደጋጋሚ ወደ እንግዳዎቹ የጎል ክልል ቶሎ ቶሎ መድረስ ቢችሉም አስፈሪ የሚባል ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። በ22ኛዉ ደቂቃ ግን በሜዳው መሀል ክፍል ላይ በዲዲዬ ሊብሬ ጥፋት መሰራቱን ተከትሎ የተገኘን ቅጣት ምት አንድ ሁለት በመቀባበል ከአዲሱ ጋናዊ አጥቂ ራሂም ኦስማኖ ወደ ግራ ተከላካይ ረመዳን የሱፍ በነፃ ቅብብል የደረሰው ኳሱ ብቻዉን ቁሞ ለነበረው ያሳር ሙገርዋ በማቀበል ወደ ጎልነት ተቀይሯል።

አዲሱ የስሑል ሽረ ሜዳ በጉም በተሸፈነበት አየር ፀባይ ዉጤቱን ለመቀልበስ የታተሩት ሲዳማ ቡናዎች በ27ኛው ደቂቃ በይገዙ ቦጋለ በተሰራዉ ጥፋት ከ20 ሜትር አከባቢ ቅጣት ምት ቢያገኙም እንደ ወትሮዉ ጥሩ ሲንቀሳቀስ ያልታየው አዲስ ግደይ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ስሑል ሽረዎችም ወደ ቀድመው የሚታወቁበት የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት በመመለስ በረጅሙ የተገኘው ኳስ በ31ኛዉ ደቂቃ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የዋለዉ አማካዩ ያሳር ሙገርዋ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በተቀሩት ደቂቃዎችም ሲዳማዎች ኳስ ይዘዉ በማንሸራሸር መጫወት ቢችሉም ዉጤታማ ሙከራ ሳያደርጉ ወደ መልበሻ ክፍል ገብተዋል።

የሁለተኛዉ አጋማሽ መጀመር በዳኛው ፊሽካ ከተሰማ በኋላ ኳሱን የጀመረዉ ያሳር ሙገርዋ በረጅሙ ለዓብዱለጢፍ ያቀበለዉን ኳስ ዓብዱለጢፍ የተከላካዮችን መዘናጋት በመጠቀም እና ሰብሮ በመግባት ጨዋታው ከተጀመረ በ20 ሰከንድ ዉስጥ ጎል አስቆጥሯል።

ከጎሉ መቆጠር በኃላ ሙሉ በሙሉ የመሀል ክፍሉን ብልጫ የወሰዱት ሲዳማ ቡናዎች አቻ ለመሆን ጥረት አድርገዋል። ግርማ በቀለን በዳዊት ተፈራ አማኑኤል እንዳለን በሚሊዮን ሰለሞን ቀይረዉ ያስገቡት ሲዳማዎች በሁለተኛው አጋማሽ ፍፁም የበላይነት ይዘው ታይተዋል። የዳዊት ተፈራ የግል ብቃትም ተመልካቹን ያዝናና እና ያስደነቀ ነበር። ዳዊት ተፈራ ተቀይሮ ከገባ በኃላ ለባለሜዳዉ ቡድን አስጨናቂ ጥቃታቸዉ አጠናክረው የቀጠሉት ሲዳማዎች 71ኛዉ ደቂቃ ዳዊት ከሀብታሙ በተቀበለዉ ኳስ ከግብ ጠባቂ ፊትለፊት ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

የዘርዓይ ሙሉ ቡድን ውጤቱን ለመቀየር የሚያስገርም መነቃቃት አሳይተው ሙሉ ሜዳ አካልለው ሲጫወቱ በአንፃሩ ዉጤቱን ጠብቀው ለመውጣት ጥቅጥቅ ያለ መከላከል የመረጡትን ስሑል ሽረዎች ሰብረዉ ለመግባት ሲጥሩ ተመልክተናል። ነገር ግን የሲዳማ ቡናው ሚሊዮን ሰለሞን ተቀይሮ ከገባ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በ76ኛዉ ደቂቃ ከሽረው አማካይ ያሳር ሙገርዋ ጋር ከኳስ ውጪ በገባው እሰጣ ገባ ምክንያት ቀጥታ በቀይ ካርድ በመኃል ዳኛው ፌደራል አርቢትር አክሊሉ ድጋፌ ከሜዳ ተወግዷል።

ይሁን እንጂ ለ11 የተቀሩ ደቂቃዎች በ10 ተጫዋች ሊጫወቱ የተገደዱት ሲዳማዎች ቀይ ወጥቶባቸውም ቢሆን በኳስ ቁጥጥር ከባለሜዳዉ ቡድን የተሻሉ ነበሩ። ጥረታቸውም ሰምሮ በ83 ደቂቃ ሀብታሙ ገዛሀኝ መናበብ አቅቷቸዉ የታዩት የስሑል ሽረ መሐል ተከላካዮችን እና ግብ ጠባቂውን የግል ብቃቱ በመጠቀም አታሎ በማለፍ ጎል አስቆጥሯል።

ከጎሏ መቆጠር በኋላ ስሑል ሽረዎች ሙሉ በሙሉ በመከላከል ተጠምደዉ ሲታዩ ሲዳማ ቡናዎች ደግሞ ወደ ስሑል ሽረ ሳጥን ሰብረዉ ለመግባት ተቸግረዉ ጨዋታ በባለ ሜዳው 2 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ የዘርዓይ ሙሉ ቡድን ወደ መሪዎቹ መጠጋት የሚችልበት ዕድል ሳይጠቀም በመቅረቱ በ27 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በአንፃሩ ስሑል ሽረዎች በአዲሱ አሰልጣኝ ሲሳይ አብርሃም እየተመሩ ጠንካራ የአጥቂ ክፍል የያዘው ሲዳማ ቡናን በማሸነፍ ጣፋጭ ድል በማስመዝገብ ከ10ኛ ደረጃ 6ኛ ደረጃን ተረክበዋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ