መቐለ 70 እንደርታ እና ባህር ዳር ከተማ ካለ ጎል አቻ ከተለያዩ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል።
“ያገኘናቸው ዕድሎች አልተጠቀምንም በዚህም ዋጋ ከፍለናል” ጎይትኦም ኃይለ (የመቐለ 70 እንደርታ ም/አሰልጣኝ)
ስለ ጨዋታው
ጨዋታው ጥሩ ነበር። ሁለታችንም ጥሩ ነበርን። እኛ ያገኘናቸው ዕድሎች አልተጠቀምንም፤ በዚህም ዋጋ ከፍለናል። በቀጣይም እናስተካክለዋለን። ባለፉት ጊዜያት ያልተጠቀምንባቸው ተጫዋቾችም ተጠቅመናል። በቀጣይ ያሉብም ክፍተቶች አርመን እንመለሳለን።
ስለ ቡድኑ የአማካይ ክፍል ድክመት
የአማካይ ክፍላችን ከመጀመርያው ዙር በጣም ተሻሽሏል። በሂደትም ያሉበትን ክፍተቶች አርመን የሊጉ ዋንጫ እናነሳለን።
“ዛሬ በተጫዋቾቼ በኩል በነበረው ጥረት በጣም ደስተኛ ነኝ” ፋሲል ተካልኝ (ፋሲል ተካልኝ)
ስለ ጨዋታው
ከባድ ጨዋታ ነበር። አንደኛ ከመሪዎች አንዱ የሆነው መቐለን ነው የገጠምነው። በዚ ላይ ቡድኑ በሜዳው ጠንካራ እንደሆነ እናውቃለን። የመጀመርያ እቅዳችን ማሸነፍ ሁለተኛ እቅዳችን አቻ መውጣት ነበር። ሁለተኛው እቅዳችን አሳክተናል። መቐለ ተጭኖን ተጫውቷል። ተጋጣመሐያችን ከኛ የተሻለ እንቅስቃሴ አድርጓል ብዬ አስባለው።
ስለ ቡድኑ የሜዳ ውጪ ብቃት
ዛሬ ተጫዋቾቼ ከሜዳ ውጭ ያላቸውን ስነ-ልቦና መቀየር የጀመሩበት ቀን ነው ብዬ ነው የማስበው። ሜዳ ላይ የአሸናፊነት እና ያለመሸነፍ ስሜት ነበራቸው። ይሄንንም በቀጣይ ጨዋታዎች አሳድገን የተሻለ ቡድን እንዲኖረን ጠንክረን እንሰራለን። ከመሪዎቹ ጎራ ነው ያለነው። ያንን ደረጃ አስጠብቀን ለመሄድ እና ከፊታችን ያሉንን ወሳኝ ጨዋታዎች በአሸናፊነት ለመወጣት እንጥራለን። ዛሬ በተጫዋቾቼ በኩል በነበረው ጥረት በጣም ደስተኛ ነኝ።
© ሶከር ኢትዮጵያ