ሰበታ ከተማ ቅዱስ ጊዮርጊስን 1ለ0 ከረታበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ የሰበታው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።
ሰለ ጨዋታው
“እንደ አጋጣሚ ሆኖ ከወልዋሎው ጨዋታ ጀምሮ ያሉን ጨዋታዎች ከባዶች ናቸው፤ በዛ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለፈውን ጨዋታ ተሸንፎ በመምጣቱ ጨዋታው ከባድ እንደሚሆን ገምተን ነበር የመጣነው። ጨዋታውን ለመቆጣጠር የተቻለንን አድርገን ጥሩ ነገር ይዘን መውጣት ችለናል።”
ተጋጣሚያቸው ያለ አሰልጣኝ መግባቱ
” እንደውም በእኔ እይታ ተነሳሽነታቸው ጥሩ ነበር። ነገርግን የተወሰኑ ቴክኒካል እና ታክቲካል ስህተቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ምክንያቱም እኔ የማሰለጥነው ቡድን ነው። እነሱ ደግሞ ያለ አሰልጣኝ መቅረባቸው ከባድ እንሚያደርግባቸው እገምታለሁ። ከተነሳሽነት አንፃር ግን ቡድኑን የመምራት ኃላፊነት ወስደው የነበሩት ተጫዋቾቹ ስለነበሩ በከፍተኛ ሞራል ነበር የገጠሙን ማለት እችላለሁ። የአሰልጣኙ ተፅዕኖ ግን ይዘውት የገቡትን እቅድ ስለማላወቅ ብዙ ነገር ለማለት እቸገራለሁ።”
ተጫዋች በቀይ መውጣቱን ስላለመጠቀማቸው
” ከቀይ ካርዱ በኃላ በመልሶ ማጥቃት ያገኘናቸው ሁለት ሶስት 4ለ2 ወይም 4ለ3 ያገኘናቸው አጋጣሚዎች ነበሩ። በእርግጥ ከእንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ አይነት ቡድን ላይ በርካታ ግቦችን አስቆጥሬ አሸንፋለሁ ማለት በራሱ ትክክል አይመስለኝም። ምክንያቱም ቡድኑ ካለው ጥንካሬ አንፃር እንዲሁም ተጫዋቾቹ በደጋፊዎቻቸው ታግዘው የነበራቸው ተነሳሽነት ከፍ ያለ ነበር። ከዚህ አንፃር ሦስት ነጥብ ማግኘታችን በቂ ነው።”
© ሶከር ኢትዮጵያ