የፕሪምየር ሊግ 17ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

በርከት ያሉ አቻ ውጤቶች በተመዘገቡበት የ17 ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መሪዎቹ በሙሉ ነጥብ ሲጥሉ አዳማ ከተማ፣ ሰበታ ከተማ እና ስሑል ሽረ ብቸኛ ባለድሎች ነበሩ። እኛም በዚህኛው ሳምንት በተደረጉ 8 ጨዋታዎች የተመለከትናቸውን ትኩረት ሳቢ ክለብ ነክ ጉዳዮችን በተከታዩ መልኩ ዳሰናቸዋል።

👉የመሻሻል ምልክቶችን እያሳየ የሚገኘው አዳማ ከተማ

ሁለተኛው ዙር ከተጀመረ ሁለተኛ የጨዋታ ሳምንት ላይ ደርሷል። አሁን ላይ በ22 ነጥቦች ወደ 9ኛ ደረጃ ከፍ ያሉት አዳማ ከተማዎች በሁለተኛ ዙር ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ከመጀመሪያው ዙር የተሻለ መልክን ይዘው ቀርበዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ባህር ዳር አቅንተው በፋሲል ከነማ የ1ለ0 ሽንፈት ቢያስተናግዱም በእንቅስቃሴ ደረጃ መልካም የሚባልን ጨዋታ አሳልፈዋል። በዚህኛው ሳምንት ደግሞ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ወልቂጤ ከተማን ገጥመው 2ለ0 በማሸነፍ ወሳኝ የሜዳ ውጭ ሦስት ነጥብ ማሳካት ችለዋል።

በእንቅስቃሴ ረገድ ደከም ያለ እንቅስቃሴ በዚህኛው ጨዋታ ላይ ቢያደርግም ዳዋ ሆቴሳ እና በረከት ደስታን በተጠባባቂ ወንበር አስቀምጦ የጀመረው ቡድኑ በሁለቱ አጋማሾች በተቆጠሩ ሁለት ግቦች በማሸነፍ ደረጃውን ማሻሻል ችሏል።

👉ስሑል ሽረ የታደሰውን ሜዳ በድል መርቋል

ለግማሽ የውድድር ዘመን በስታዲየማቸው እድሳት ምክንያት ወደ መቐለ አምርተው ሲጫወቱ የቆዩት ስሑል ሽረዎች በቅርቡ እድሳቱን ባጠናቀቀው ስታዲየማቸው ባደረጉት የመጀመሪያ የነጥብ ጨዋታ ጠንካራው ሲዳማ ቡናን አስተናግደው በማሸነፍ የታደሰው ስታዲየምን በድል መክፈት ችለዋል።

ከአስደናቂ ጉዞ በኋላ ለተወሰኑ ሳምንታት ተቀዛቅዝው የነበረው ሽረ በአብዱለጢፍ መሐመድ እና ያስር ሙገርዋ ጎሎች ወሳኝ ድል በማስመዝገብ ነጥቡን ወደ 24 በማሳደግ ወደ 6ኛ ደረጃ ከፍ ማለት ችሏል። ሽረ ወደ ሜዳው መመለሱ ብሎም ድል ማስመዝገቡ ለሁለተኛ ዙር ጉዞው ወሳኝ መነቃቃት እንደሚፈጥርለት ይገመታል።

👉ያለ ግብ የተጠናቀቁት ጨዋታዎች

በዚህኛው ሳምንት ከተደረጉት ስምንት ጨዋታዎች ውስጥ በአስገራሚ መልኩ አምስቱ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ሦስቱ ጨዋታዎች ያለ ግብ የተጠናቀቁ ነበሩ።

ሶዶ ላይ ወላይታ ድቻ ከወልዋሎ ፣ ትግራይ ስታዲየም ላይ መቐለ 70 እንደርታ ከባህር ዳር ከተማ እንዲሁም ድሬዳዋ ላይ ላይ ድሬዳዋ ከተማ ከፋሲል ከነማ ያደረጓቸው ጨዋታዎች በዚህኛው ሳምንት ያለግብ የተጠናቀቁ ጨዋታዎች ናቸው።

አሰልቺ መልክ በነበራቸው ጨዋታዎቹ ጥንቃቄ መር አጨዋወቶች ለውጤቶቹ አይነተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ማስተዋል ይቻላል። ገና ከወዲሁ በሁለተኛው ዙር እያንዳንዱ ነጥቦች ከፍ ያለ ዋጋ ስለሚኖራቸው በቀጣይ ቀሪ ሳምንታት ሊኖሩ የሚችለውን የውድድር መልክ የጠቆሙ ጨዋታዎች ነበሩ።

👉ከአስደናቂ ድሉ ማግስት እጅግ የወረደው ወልቂጤ

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስን በሜዳው እና በደጋፊው ፊት አሸንፈው ከፍ ያለ ሞገሳ ሲቸራቸው የሰነበቱት ወልቂጤዎች በዚህኛው ሳምንት ከአዳማ ከተማ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ሽንፈትን አስተናግደዋል።

ከሽንፈቱም በላይ ቡድኑ ሲከላከልም ሆነ ሲያጠቃበት የነበረው መንገድ ፍፁም ከወትሮው የተለየ እና ጥድፊያዎች እና ስህተቶች የተሞሉበት መሆን ለማስተዋል ችለናል።

ቡድኑ ምንም እንኳን የኋላ መስመሩ በተለያዩ ምክንያቶች መታመሱን ከግምት ውስጥ ማስገባት ተገቢ ቢሆንም በጥቂት ቀናት ልዩነት በዚህ መልኩ የወረደ እንቅስቃሴ ማድረጋቸው ግን ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው።

👉ግራ የተጋባው ቅዱስ ጊዮርጊስ

በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ከፍ ያለ ግምት ከሚሰጣቸው ክለቦች አንዱ የሆነው እና በአሁኑ ሰዓት በሰንጠረዡ በሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ተከታታይ ሁለተኛ ሽንፈቱን በሰበታ ከተማ እጅ ቀምሷል።

ከጨዋታ ስልት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ሲታመስ የከረመው ቡድኑ ከቀናት በፊት የቡድኑን አሰልጣኝ ጨምሮ በርካታ አካላት ላይ የእግድ ውሳኔ ማሳለፉ የሚታወስ ሲሆን በሰበታ ከተማ በተሸነፉበት ጨዋታ ቡድኑ ያለ አሰልጣኝ በተጫዋቾቹ እየተመራ ባደረገው ጨዋታ ሽንፈትን ማስተናገድ ችሏል።

ምንም እንኳን ቢሸነፉም ከአናቱ የሚገኙት ፋሲል ከነማ እና መቐለ 70 እንደርታ ጨዋታቸውን በአቻ ውጤት በማጠነቀቃቸው ያለው ልዩነት ይበልጡን ሳይሰፋ ቀርቷል።

በውድድር ዘመኑ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ አሰልጣኛቸውን ያገዱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በቀጣይ በአሰልጣኞቹ ዙርያ ያለውን ብዥታ ፈትተው ወይም የአዲስ አሰልጣኝ ቅጥር ፈፅመው የዋንጫ ፉክክር ጉዟቸውን ዳግም ወደ መስመር ያስገቡ ይሆን የሚለው ጉዳይ አጓጊ ነው።

👉ድራማዊ ክስተት ያስተናገደው የጅማው ጨዋታ

ጅማ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ላይ ባሳለፍነው ሳምንት በባህር ዳር ከተማ ሽንፈት ያስተናገደው ጅማ አባ ጅፋር በ16ኛ ሳምንት አስደናቂ ድል ያስመዘገበውን ኢትዮጵያ ቡናን የጋበዘበት ጨዋታ በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች ላይ በተቆጠሩ ግቦች አንድ ለአንድ ሊጠናቀቅ ችለዋል።

እስከ 89ኛው ደቂቃ ድረስ ምንም ግብ ያላስተናገደው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ አቡበከር ናስር በ89ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ግብ ኢትዮጵያ ቡና በመጨረሻ ደቂቃ ከሜዳ ውጭ ድል አድርጎ ተመለሰ ተብሎ ሲጠበቅ በ90ኛው ደቂቃ ኤርሚያስ ኃይሉ ለባለሜዳዎቹ ባስቆጠረው ግብ ጨዋታው በአቻ ውጤት ሊጠናቀቅ ችሏል።

መሰል ሁኔታዎች በሊጉ አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ሲሆን ከዚህ ቀደም በ2009 ኢትዮጵያ ቡና ከ ሀዋሳ ከተማ ባደረጉት ጨዋታ ቡናዎች በጭማሪ ደቂቃ ግብ አስቆጥረው ጨዋታውን አሸነፉ ተብሎ ሲጠበቅ በቅፅበት ሀዋሳዎች ጎል አስቆጥረው አቻ መጠናቀቁ የሚታወስ ነው።

👉በትላልቅ ጨዋታዎች ጠንክሮ የሚቀርበው ሰበታ ከተማ

በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመሩት ሰበታ ከተማዎች በተለይ ከሰንጠረዡ ወገብ በላይ ከሚገኙ ቡድኖች ጋር በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ላይ ከወትሮው በተለየ የፍላጎት ደረጃ ላይ ሆነው በማድረጋቸው የተሻለ ተንቀሳቅሰው ውጤት ይዘው መውጣታቸውን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንትም ቀጥለውበታል።

በ17ኛ ሳምንት አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስን የገጠመው ቡድኑ በአስቻለው ግርማ ብቸኛ ግብ በማሸነፍ በመሰል ጨዋታዎች ላይ ያለውን የተለየ መልክ አሁንም ያስመሰከረበት ጨዋታ ነበር።

ሰበታ በመጀመሪያው ዙር ከኢትዮጵያ ቡና ፣ ፋሲል ከነማ ፣ ባህር ዳር ከተማ ፣ ሲዳማ ቡና እና መሰል ቡድኖች ጋር በተጫወተባቸው ጨዋታዎች ከወትሮው የተለየ ጥንካሬን ሲላበስ ተስተውሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ