ጅማ አባጅፋሮች ናይጄሪያዊውን አጥቂ ላኪ ሰኒን ለማስፈረም የተቃረቡ ሲሆን አማካዩ ሄኖክ ገምቴሳ በስምምነት ተለያይቷል፡፡
በበርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥ እየተጓዘ የሚገኘው ጅማ አባጅፋር የጠበበው የቡድኑን ስኳድ ለማስፋት በማሰብ ከቀናት በፊት ለቀድሞው ወልቂጤ፣ ጅማ አባቡና፣ ሲዳማ ቡና፣ አርባምንጭ ከተማ እና ደቡብ ፓሊስ ተጫዋች ላኪ ሰኒ የሙከራ ዕድልን መስጠቱ ይታወሳል፡፡ አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸውም ተጫዋቹን አስፈርሙልኝ በማለት ለክለቡ የበላይ አካላት ጥያቄን ቢያቀርቡም በጀት የለንም በማለታቸው የተነሳ ተጫዋቹ ከካምፕ ለቆ መውጣቱ ይታወሳል። ከክለቡ የበላይ አካላት ጋር የተነጋገሩት ያደረጉት አሰልጣኝ ጳውሎስም ተጫዋቹ እንዲመለስ በማድረግ በአሁኑ ሰዓት ከክለቡ ጋር የሚገኝ ሲሆን በገንዘብ የሚስማሙ ከሆነ የጅማ አባ ጅፋር የሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ፈራሚ ይሆናል፡፡
በሌላ የክለቡ ዜና ዓምና ክለቡን ተቀላቅሎ ላለፉት አንድ ዓመት ከስድስት ወራት በአማካይ ስፍራ ላይ ሲጫወት የነበረው ሄኖክ ገምቴሳ የስድስት ወራት ኮንትራት እየቀረው ከክለቡ ጋር በስምምነት ተለያይቷል፡፡ የቀድሞው አዳማ ከተማ እና ፋሲል ከነማ ተጫዋች ለክለቡ ባስገባው የልቀቁኝ ጥያቄ መሠረት ነው ሊለያይ የቻለው፡፡ በዚህም ከብሩክ ገብረአብ በመቀጠል ሁለተኛ ከክለቡ ጋር የተለያየ ተጫዋች ሆኗል፡፡
ክለቡ በቀጣዩ ቀንም ከአቋም ጋር በተገናኘ ከጋናዊው አጥቂ ያኩቡ መሐመድ ጋር ሊለያይ የሚችልበት ዕድል የሰፋ ነው ተብሏል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ