በዓበይት ጉዳዮች ሦስተኛው ክፍል በዚህ ሳምንት ትኩረት የሳቡ አሰልጣኝ ነክ ጉዳዮች እና አስተያየቶችን ይቃኛል።
👉 የአሰልጣኝ ደለለኝ የጫጉላ ጊዜ ያበቃ ይመስላል
በሶዶ ስታዲየም ወላይታ ድቻ ወልዋሎን አስተናግዶ ያለ ግብ ያጠናቀቀበት ጨዋታ በሳምንቱ ያለ ግብ ከተጠናቀቁት አሰልቺ ጨዋታዎች አንዱ ነበር።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የወላይታ ድቻ ደጋፊዎች በአሰልጣኝ ደለለኝ ደቻሳ ላይ ተቃውሞን ያሰሙ ሲሆን አሰልጣኙም ከደጋፊዎቹ ጋር በፈጠረው የቃላት ልውውጥ ከደጋፊዎች የድንጋይ ውርወራን ለማስተናገድ ተገደዋል።
ክለቡን በጊዜያዊ አሰልጣኝነት ተረክቦ ባስመዝገበው ጥሩ ውጤት ከሳምንታት በፊት በቋሚነት ክለቡን ለቀጣይ አንድ ዓመት ማሰልጠን የሚያስችለውን ውል መፈረም የቻለው አሰልጣኙ እነዛ በስኬት የተጓዘባቸው ሳምንታት አልፈው በመጨረሻ ካደረጓቸው ሦስት ጨዋታዎች በሁለቱ ተሸንፎ በአንዱ አቻ መለያየት ችለዋል። በተለይም በተቀናቃኛቸው ሲዳማ ቡና የተረቱበት እንዲሁም በዚህኛው ሳምንት አሰልቺ መልክ በነበረው የወልዋሎ ጨዋታ ያሳዩት ደካማ እንቅስቃሴ በደጋፊዎቻቸው አልተወደደላቸውም።
ከአሰልጣኝ ለውጥ ጋር ተያይዞ የሚመጣውን የተጫዋቾች ሰሞነኛ የማሸነፍ ተነሳሽነት ወቅት አሁን ያበቃ ይመስላል። በቀጣይም የአሰልጣኙ ትክክለኛ አቅም የሚፈተንበት ወቅት ላይ የደረስን ይመስላል።
👉 ያለ አሰልጣኝ የቀረበው ቅዱስ ጊዮርጊስ
ከሰሞኑ የአሰልጣኝ ቡድኑ እንዲሁም ቴክኒክ ኮሚቴው ላይ ጠንከር ያለ ውሳኔን ያስተላለፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ በዚህኛው ሳምንት ሰበታ ከተማን በገጠመበት ጨዋታ ዘሪሁን ሸንገታን በዋና አሰልጣኝነት ቢያስመዘግብም ያለ አሰልጣኝ ጨዋታውን አድርጎ ሽንፈት አስተናግዷል።
በሜዳ ውስጥ የነበረው አስቻለው ታመነ ቡድኑን በሜዳ ውስጥ ሆኖ ሲመራ በተጠባባቂነት ወንበር የነበረው ሰልሀዲን በርጌቾ ደግሞ የተወሰኑ እገዛዎችን ሲያደርግለት ተስተውሏል።
ቡድኑ ያለ አሰልጣኝ መቅረቡ በጉልህ በሚታይ መልኩ ያጎደለበት አንዳች ነገር ስለመኖሩ በተስተዋለበት ጨዋታ አስቻለው ታመነ የመጀመሪያውን የተጫዋች ቅያሬ ካደረገበት ቅፅበት በኋላ ከጨዋታው ደቂቃ መግፋት ጋር ተዳሞሮ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ቅያሬ ለማድረግ እጅጉን ዘግይቶ በተጠባባቂነት በነበረው ሰልሀዲን ቅያሬዎቹ መፈፀማቸው ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ ነበር።
በተጨማሪም የቡድኑ የህክምና ባለሙያ ሙሉነህ ቤካ በሜዳው ጠርዝ ቆሞ ቢስተዋልም ከመቆም በዘለለ መልዕክቶችን ሲያስተላልፍ መመልከት አልቻልንም።
👉ዐበይት አስተያየቶች
🗣 አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ስለ ቡድኑ የሜዳ ውጭ ብቃት
“ዛሬ ተጫዋቾቼ ከሜዳ ውጭ ያላቸውን ስነ-ልቦና መቀየር የጀመሩበት ቀን ነው ብዬ ነው የማስበው። ሜዳ ላይ የአሸናፊነት ስሜት የአለመሸነፍ ስሜት ነበራቸው። ይሄንንም በቀጣይ ጨዋታዎች አሳድገን የተሻለ ቡድን እንዲኖረን ጠንክረን እንሰራለን። ከመሪዎቹ ጎራ ነው ያለነው። ያንን ደረጃ አስጠብቀን ለመሄድ ከፊታችን ያሉንን ወሳኝ ጨዋታዎች በአሸናፊነት ለመወጣት እንጥራለን።
ዛሬ በተጫዋቾቼ በኩል በነበረው ጥረት በጣም ደስተኛ ነኝ።”
🗣 የሀዋሳ ከተማው ጊዜያዊ አሰልጣኝ ብርሀኑ ወርቁ ስለ ቡድኑ
“ጨዋታውን እንደጠበቅነው አይደለም ያገኘነው። እነሱም እኛም ተሸንፈን ነው የመጣነው። እኛ ሜዳችን ላይ የማሸነፍ አቅም ነበረን። ሆኖም ዛሬ ትንሽ ተቀዛቅዘን ነበር የገባነው። በዛም ምክንያት ውጤት ልናጣ ችለናል፡፡ ልጆቹ ጋር የነበረው ችግር ምን እንደሆነ አላውቅም። ወደ ዛሬው ጨዋታ ከመግባታቸው በፊት የሚያሳዩት ነገር ጥሩ ነው። ሜዳ ላይ የነበረው ደግሞ የሚታይ ነው። ከዚህ ቀደም የነበራቸው ነገር አውጥተው እየተጫወቱ አይደለም። ይህ መነሻው ምን እንደሆነ ግን አላውቅም፡፡”
🗣 አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ተጋጣሚያቸው ያለ አሰልጣኝ መግባቱ በጨዋታው ስለነበረው ተፅዕኖ
” እንደውም በእኔ ዕይታ ተነሳሽነታቸው ጥሩ ነበር። ነገርግን የተወሰኑ ቴክኒካል እና ታክቲካል ስህተቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ምክንያቱም እኔ የማሰለጥነው ቡድን ነው፤ እነሱ ደግሞ ያለ አሰልጣኝ መቅረባቸው ከባድ እንደሚያደርግባቸው እገምታለሁ። ከተነሳሽነት አንፃር ግን ቡድኑን የመምራት ኃላፊነት ወስደው የነበሩት ተጫዋቾቹ ስለነበሩ በከፍተኛ ሞራል ነበር የገጠሙን ማለት እችላለሁ። የአሰልጣኙ ተፅዕኖ ግን ይዘውት የገቡትን እቅድ ስለማላወቅ ብዙ ነገር ለማለት እቸገራለሁ።”
🗣 ደጉ ዱባሞ አዳማ በወልቂጤው ጨዋታ ይዞት ስለገባው እቅድ
” በጨዋታው ያሰብነውን ያህል ኳሱን ተቆጣጥረን መጫወት አልቻልንም። በውጤት ረገድ ብናሸንፍም በእንቅስቃሴ ረገድ ጨዋታው ያሰብነውን አይገልጽም። እቅዳችን የነበረው ኳሱን ይዘን መጫወት ነበር። በጨዋታው ካሰብነው ረገድ ታክቲካሊ ተጫዋቾቻችን ሙሉ ለሙሉ አልተገበሩልንም ማለት እንችላለን። ሁላችንም የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ አለብን ብለን ነበር የገባነው። ውጤቱ ጥሩ ቢሆንም ጨዋታችን ረጃጅም ኳሶች ይበዙት ነበር።”
© ሶከር ኢትዮጵያ