የአዲስ አበባ ከ17 ዓመት በታች ውድድር ዛሬ ተጀመረ

የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን የሚያወዳድረው ከ17 ዓመት በታች የታዳጊዎች ውድድር የተሳታፊ ቁጥር ከዓምናው ከፍ አደርጎ በ14 ቡድኖች መካከል በሁለት ምድብ ተከፍሎ ዛሬ ተጀምሯል።

ዓምና በ10 ቡድኖች መካከል መካሄድ የጀመረው ይህ ውድድር ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ እና ሠላም እግርኳስ ክለቦች ዘንድሮ ተሳታፊ ሳይሆኑ ቢቀርም ሠውነት ቢሻው፣ ከለላ፣ ፍቅር በአንድነት፣ ቤተል ድሪመርስ፣ ጌታቸው ቀጨኔ እና ዲ ኤፍ ቲ አዲስ ቡድኖችን በማካተት እንዲሁም ነባር ቡድኖችን ጨምሮ ውድድሩ በ14 ቡድኖች መካከል በሁለት ምድብ ተከፍሎ በሁለት ዙር ጨዋታዎች ውድድሩ ዛሬ ተጀምሯል።

ያልተጋነነ ተመጣጣኝ የሆነ የእድሜ እርከን በታየበት እና አብዛኛው ቡድኖች አዳዲስ ተስፈኛ ተጫዋቾችን ይዘው በቀረቡበት ይህ ውድድር ከረፋዱ 04:00 ጀምሮ በጃን ሜዳ መካሄድ ጀምሯል። የአአ እግርኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ እና የውድድር ሥነ ስርዓት ኮሚቴ ሰብሳቢ ኢ/ር የኔነህ በቀለ በክብር እንግድነት በመገኘት ውድድሮቹን አስጀምረዋል።

04:00 ቅዱስ ጊዮርጊስን አዲስ ተሳታፊ ከሆነው ከለላ ጋር በተደረገው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁለቴ ከመመራት ተነስቶ 4-2 በሆነ ውጤት አሸንፏል። ፈጣኑ የመስመር አጥቂ የሴፍ በቀለ 35ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ጎል ቀዳሚ መሆን ችለዋል። ይህችም ጎል የውድድሩ የመጀመርያ ጎል ሆና ተመዝግባለች። ጨዋታው ከእረፍት መልስ ቀጥሎ የከለላው ፈጣን አጥቂ ዮሴፍ በቀለ በ46ኛው ደቂቃ ለእራሱም ለቡድኑም ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ ከለላ መምራት ችለው ነበር። ከዚህ በኃላ የጨዋታው መልክ ተቀይሮ በ47፣ 55 እና 58ኛው ደቂቃ ላይ የተገኙትን ተመሳሳይ የቅጣት ምት ኳሶችን ዓምና በዚህ ቡድን ውስጥ መልካም እንቅስቃሴ ሲያደርግ የተመለከት ሚራጅ ሰፋ ሦስት ጎሎችን አስቆጥሮ ሐ ትሪክ ከመስራቱም ባሻገር ፈረሰኞቹን መሪ ማድረግ ችሏል። በመጨረሻም የጨዋታው መጠናቀቂያ 90ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ ዮሐንስ አራተኛ ጎል ለቅዱስ ጊዮርጊስ አስቆጥሮ ጨዋታው በፈረሰኞቹ 4–2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በተመሳሳይ ሰዓት ከምድብ ለ በሌላ ሜዳ በቀጠለው የመከላከያ እና የሀሌታ ጨዋታ በመከላከያ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ብዙም ማራኪ ያልሆ እንቅስቃሴ ባንመለከተም እና በግል ቡድኖቹ ውስጥ ተሰፋ የሚጣልባቸው ታዳጊዎች አስመልክቶን አልፏል። በመጀመርያው አጋማሽ የጨዋታ እንቅስቃሴ ጎል ሳያስመለክተን ቢቀርም በደቂቃዎች ልዮነት መከላከያዎች ጎል አስቆጥረው ማሸነፍ ችለዋል። በ73ኛው ደቂቃ ቶድዩ ዳዊት ባስቆጠረው ጎል መከላከያዎች ቀዳሚ መሆን ከጀመሩ ከሁለት ደቂቃ በኃላ ተቀይሮ በገባው ናትናኤል አንባው አማካኝነት ሁለተኛ ጎል ማግኘት ችለው ጨዋታው 2-0 አሸንፈው መውጣት ችለዋል።

06:00 በቀጠለው እና ከኢትዮጵያ ቡና ከፍቅር በአንድነት ጋር ያገናኘው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ከጨዋታ ብልጫ ጋር 4-0 በሆነ ሰፊ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል። ኢትዮጵያ ቡና ዓምና በዚህ ውድድር ካስመዘገበው ደካማ ውጤት በተሻለ የአሰልጣኝ እና የተጫዋች ለውጥ በማድረግ ጥሩ ቡድን ይዞ መቅረቡን አሳይቶናል። የውድድሩን ፈጣን ጎል በ2ኛው ደቂቃ በሡፍቃድ ገኑ አስቆጥሮ ቡናማዎቹ ቀዳሚ መሆን ችለዋል። ከደቂቃዎች በኃላ በጥሩ እንቅስቃሴ በ38ኛው ፋሲካ መክብብ ሁለተኛ አክሎ ብዙም ሳይቆይ በጨዋታው ላይ የነበራቸውን ብልጫ ማሳያ የግንባር ጎል ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛ ጎል በሡፍቃድ ገኑ አስቆጥሮ ወደ እረፍት አምርተዋል። ወደ ጨዋታው መጠናቀቂያ 80ኛው ደቂቃ ላይ ቃልአብ ተስፋዬ ግሩም አራተኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው 4-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

06:00 በቀጠለው ሌላ ጨዋታ ሁለቱን አዲስ ቡድኖች ያገናኘው የሠውነት ቢሻው አካዳሚ እና ጌታቸው ቀጨኔ አካዳሚን ጨዋታ ከእንቅስቃሴ ብልጫ ጋር ጌታቸው ቀጨኔ ሦስት ለምንም አሸንፏል። ጎሎቹንም ከእረፍት በፊት ፍራኦል ጉንዱማ፣ ቅዱስ ጥሩነህ እንዲሁም የጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ ተቀይሮ የገባው ሚኪያስ ጌታዬ አስቆጥሮ ጨዋታው 3–0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

08:00 በተካሄደው ሌላኛው ጨዋታ ከእረፍት መልስ አሸናፊ አክመል እና ፉአድ ቢንያም ባስቆጠሩት ሁለት ጎሎች አፍሮ ፅዮን ኢትዮጵያ መድንን 2-0 በሆነ ውጤት ሲያሸንፍ በተመሳሳይ ሰዓት አዲስ መጪውን ቤተል ድሪመርስን ያስተናገደው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሱሉስ ፀደቀ፣ አቤል ሽመልስ እና ናትናኤል ዱባለ ባስቆጠሩት ሦስት ጎሎች 3–0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።

© ሶከር ኢትዮጵያ