የከፍተኛ ሊግ መሪ ክለቦች 1ኛ ዙር ዳሰሳ – አርባምንጭ ከተማ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ አንደኛ ዙርን አስመልክቶ የየምድቦቹን ቀዳሚ ቡድኖች ዳሰሳ ማስነበባችንን ቀጥለን በምድብ ሐ ቀዳሚ ሆኖ ያጠናቀቀው አርባምንጭ ከተማን በዚህ መልኩ ተመልክተነዋል።

የመጀመርያ ዙር ጉዞ

ባለፈው ዓመት ቡድኑን እየመሩ እስከመጨረሻዎቹ ሳምንታት ለማደግ እንዲፎካከር የረዱት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪን በማስቀጠልና ለፕሪምየር ሊግ ተሳታፊነት የሚረዳ ዝግጅት ሲያደርግ ቢቆይም አዲሱ የፕሪምየር ሊግ ፎርማት ቀርቶ በከፍተኛ ሊጉ እንዲቀጥል በመወሰኑ ምክንያት በምድብ ሐ ውድድሩን ቀጥሏል።

አርባምንጭ ከነማ በከፍተኛ ሊጉ ላይ ውጤት ለማስመዝገብ እና ወደ ሊጉ ለመቀላቀል ከሰራቸው ጠንካራ ስራዎች ውስጥ በተጫዋቾች አመራረጥ ላይ ትልቁን ሚና ይወስዳል። ሦስት የውጭ ዜጋ ያስፈረሙ ሲሆን ከካፋ ቡና፣ ሀዋሳ ከተማ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ጋሞ ጨንቻ፣ ሺንሺቾ
እና ከደቡብ ፖሊስ ያስፈረማቸው ተጫዋቾች ጠንካራ የተጫዋቾች ስብስብ እንዲኖራቸው አስችሏል።

ክለቡ በውድድሩ ዓመቱ የመጀመርያ ጨዋታውን ከሜዳ ውጭ ያደረገ ሲሆን ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማን 1ለ0 በማሸነፍ ውድድሩን ጀምሯል። ወደ ሜዳው ሲመለስም ድል የቀናው አርባምንጭ ከተማ በሜዳው እንደቀድሞው ሁሉ ጥንካሬውን ይዞ የቀጠለ ሲሆን ለዚህም ማሳያ በሜዳው ካደረጋቸው ጨዋታዎች ውስጥ አንዱንም አለመሸነፉ ነው። በሜዳው ካደረጋቸው ጨዋታውች ውስጥ ነጥብ የጣለው ከወራቤ ጋር አቻ የተለያየበት ነበር። ከሜዳው ውጪም ጠንካራ የሆነው ቡድኑ በአጠቃላይ በአድኛው ዙር ምንም ጨዋታ ያልተሸነፈ ቡድን ሆኖ ዓመቱን አጋምሷል።

የአርባምንጭ ከተማ አንደኛው ዙር በቁጥሮች

ደረጃ – 1ኛ
ተጫወተ – 11
አሸነፈ – 7
አቻ – 4
ተሸነፈ – 0

ጎል

አስቆጠረ – 12
ተቆጠረበት – 2
ጎል አስቆጥሮ የወጣባቸው ጨዋታዎች – 8
ጎል ሳይቆጠርበት የወጣባቸው ጨዋታዎች – 9
ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ – ኤደም ኮድዞ (6)

የቡድኑ አቀራረብ

አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ የሚታወቁበት ጠንካራ አደረጃጀት እና ቀጥተኛ እግርኳስ የአርባምንጭ ከተማ መገለጫ ነው። በቁጥሮች ባይደገፍም በሊጉ አነስተኛ የኳስ ቅብብል በማድረግ አርባምንጭ ከነማ ተጠቃሽ ክለብ ነው። በክለቡ ውስጥ ፈጣሪ ተጫዋቾች ባለመኖራቸው እና ያሉትንም ያለመጠቀሙ ማራኪ እንቅስቃሴ እንዳይታይ ምክንያት ሆኗል። ለዚህም ደግሞ ማሳያው በየጨዋታው የሚታየው አሰልቺ እንቅስቃሴና የደጋፊው ተቃውሞ ተጠቃሽ ነው። ሆኖም ክለቡ በአጨዋወቱ በመቀጠል ውጤታማ መሆን የቻለ ሲሆን በቀላሉ የማይደፈር የኋላ መስመር እና በግለሰቦች ላይ የተንጠለጠለ ቢሆንም የጎል እድሎችን በመጠቀም ጥሩ ጊዜ በማሳለፍ ላይ ይገኛል።

የአርባምንጭ ከነማ የተከላካይ ክፍል በከፍተኛ ሊጉ ካሉት ክለቦች ሁሉ ጠንካራው ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ለዚህ ማስረጃው ደግሞ በመጀመርያው ዙር የተቆጠረበት የጎል ብዛት 2 ብቻ ነው። ነገር ግን የተከላካይ ክፍሉ ኳስ መስርቶ መጫወት እና በተጋጣሚ ቡድን ላይ የአየር ኳሶችን ወደ የጎል መቀየር ላይ መሻሻል ይታይበታል።

ክለቡ እዚህ ደረጃ እንዲደርስ ትልቁን ድርሻ የሚወስደው የመሐል ክፍሉ ነው። በተለይ የተከላካይ አማካዩን ተሻግሮ የጎል ማስቆጠር የማይታሰብ ነው። በዘንድሮ ውድድር ከጋሞ ጨንቻ የፈረመው ማሜ እና ከሀዋሳ ከተማ በድጋሚ ወደ ክለቡ የተመለሰው ምንተስኖት የመሐል ክፍሉን ጠንካራ አድርገውታል።

የአጥቂ ክፍሉ ከአጠቃላይ ቡድኑ ድጋፍ የማያገኝ እንደመሆኑ የሚፈጠረው የጎል እድል ዝቅተኛ ሲሆን እንደ ምድቡ መሪነቱ ያስቆጠራቸው ጎሎችም ዝቅተኛ የሚባል ነው።

ጠንካራ ጎኖች

የተከላካይ ክፍሉ የቡድኑ ጠንካራ ጎን ነው። ከአማካይ ክፍሉ አስተማማኝ ሽፋን የሚያገኘው የኋላ ክፍሉ በ11 ጨዋታዎች ሁለት ጎሎች ብቻ ያስተናገደ ሲሆን የአሰልጣኝ መሳይ የጥንቃቄ አጨዋወትም ለጥንካሬው መጎልበት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል።

የአማካይ ክፍሉ ሌላው ጠንካራ ጎን ሲሆን የቡድኖችን የማጥቃት እንቅስቃሴ በመገደብና ለተከላካዮች ሽፋን በመስጠት ቡድኑን ጠንካራ አድርገውታል።

ደጋፊው ሌላው የቡድኑ የጀርባ አጥንት ነው። ከፍተኛ ቁጥር ያለው ደጋፊ ካላቸው ክለቦች አንዱ የሆነው አርባምንጭ በደጋፊው ደማቅ ድባብ ታግዞ በሜዳው ለማሸነፍ የሚያስቸግር ቡድን ሲሆን ከአንድ አቻ በቀር ሁሉንም የሜዳው ጨዋታዎች በድል ተወጥቷል።

ደካማ ጎኖች

የቡድኑ አጠቃላይ የማጥቃት አጨዋወት ደካማ ጎኑ ነው። በ11 ጨዋታ 12 ጎሎች ብቻ ያስቆጠረው ቡድኑ በጥቂት ተጫዋቾች ላይ የተንጠለጠለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያለው ሲሆን ቶጓዊው ኤደም ኮድዝ ገሚሱን ማስቆጠር ችሏል። ቡድኑ ከልክ ያለፈ የጥንቃቄ አጨዋወት መምረጡ ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል እንዳይደርሱ ያደረጋቸው ሲሆን በየጨዋታው የሚፈጥሩት የጎል እድልም እጅግ ዝቅተኛ ነው።

ለሁለተኛ ዙር ምን ይጠበቃል?

ቡድኑ በስብስብ ደረጃ ጠንካራ በመሆኑ ዝውውር ላይ በብዛት ይሳተፋል ተብሎ ባይጠበቅም በአጥቂ ስፍራ አማራጩን ማስፋት ይኖርበታል። ለዚህም በሊጉ ልምድ ያለው በድሩ ኑርሁሴንን ለማስፈረም መቃረቡ ጥሩ እርምጃ ይመስላል። በተጨማሪም የፈጠራ አቅሙን የሚያጎለብት አጥቂ አማካይ ማስፈረም ከቻለ ከዚህ በተሻለ መጓዝ እንደሚችል ይታመናል።

አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ከተጫዋቾች ዝውውር ባሻገር የተለያዩ አቀራረቦችን እንደየጨዋታው ባህርይ በመለዋወጥ መቅረብ ከቻሉ በሁለተኛው ዙር ይበልጥ ጠንካራ ቡድን እንደሚሆን ይጠበቃል።

©ሶከር ኢትዮጵያ