የብሔራዊ ስታዲየም ሁለተኛ ምዕራፍ ግንባታን ለማከናወን የፊርማ ሥነ-ስርዓት ተካሄደ

በአዲስ አበባ እየተገነባ የሚገኘው የብሔራዊ ስታዲየም ግንባታን ሁለተኛ ምዕራፍ ግንባታ ለማከናወን የቻይና ስቴት ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን እና የስፖርት ኮሚሽን ዛሬ የፊርማ ስነ-ሥርዓት አከናውነዋል።

የስፖርት ኮሚሽኑ በፌስቡክ ገፁ ባሰፈረው መረጃ መሠረት የፊርማ ስነ-ሥርዓቱን የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ኤሊያስ ሽኩር እና የቻይና ስቴት ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (CSCEC) ማናጀር ሊዩ ጀባህ አካሂደዋል።

900 ቀናት ይፈጃል ተብሎ በሚጠበቀው የሁለተኛ ምዕራፍ ግንባታ በመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ያልተጠናቀቁ ሜዳ ሳር የማልበስና የመሮጫ ትራክ ግንባታ የሚካተቱ ሲሆን የስታዲየሙን ጣሪያ ማልበስና ወንበር መግጠም፣ ሰው ሰራሽ ሀይቅ፣ የሄሊፕተር ማረፊያ፣ ዘመናዊ የደህንነት ካሜራ፣ ሳውንድ ሲስተም፣ የፓርኪንግ አገልግሎት መስጫ ቦታዎች፣ የመለማመጃ ሜዳዎች ግንባታዎች እና ሌሎች ሥራዎችን እንደሚያጠቃልል ኮሚሽኑ ገልጿል።

እስካሁን 2.47 ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ስታዲየሙ የሁለተኛ ምዕራፍ ግንባታውን ለማከናወን ከ5.57 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚፈጅ ኮሚሽኑ ያስታወቀ ሲሆን በአጠቃላይ 62,00 ተመልካች የሚያስተናግደው ብሔራዊ ስታዲየም ወጪ ከ8 ቢልዮን ብር በላይ እንደሆነ ተገልጿል።

© ሶከር ኢትዮጵያ