የወልቂጤ ከተማ ምክትል ፕሬዝደንት በግላቸው ለኮሮና ቫይረስ የገንዘብ ድጋፍ አደረጉ

የወልቂጤ ከተማ ምክትል ፕሬዝደንት አቶ አበባው ሰለሞን ለአቅመ ደካሞች የንፅህና ቁሳቁስ መግዣ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል።

የወልቂጤ ከተማ እግርኳስ ክለብ ከምስረታው አንስቶ ክለቡን በአመራርነት እና የተለያዩ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ የሚታወቁት እንዲሁም የክለቡ ምክትል ፕሬዝደንት በመሆን እያገላገሉ የሚገኙት አቶ አበባው ሰለሞን በወልቂጤ ከተማ ለሚገኙ አቅመ ደካሞች የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች መግዣ የሚውል የአንድ መቶ ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ በግላቸው አድርገዋል።

አቶ አበባው በግላቸው ይህን መልካም ተግባር ይፈፅሙ እንጂ በቅርቡ የወልቂጤ ከተማ እግርኳስ ክለብ አመራሮች በሚያሳልፉት ውሳኔ መሠረት መሰል ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚችል ለማወቅ ችለናል።

በተመሳሳይ ዜና የፋሲል ከነማ እግርኳስ ክለብ የቡድኑን መጓጓዣ አውቶቢስ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስን ለመቆጣጠር ለሚያደርገው ጥረት አገልግሎት እንዲውል ዛሬ ድጋፍ ማድረጉ ተሰምቷል።

ወረርሽኙን ተከትሎ የሚመጡ ሰባዊ ቀውሶችን አስቀድሞ መከላከል ይቻል ዘንድ በስፖርቱ ዘርፍ በሁሉም አቅጣጫ የሚደረገው እርብርብ በቀጠለበት በአሁኑ ሰዓት በቀጣይም መሰል ትብብሮች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚችሉ መረጃዎች እየጠቆሙ ይገኛል።

© ሶከር ኢትዮጵያ