በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት እንደሌሎች ውድድሮች ሁሉ ተቋርጦ የሚገኘው ከፍተኛ ሊግን የተመለከቱ አጫጭር መረጃዎች እንደሚከተለው አሰናድተናል።
ነቀምቴ ከተማ ሁለት ተጫዋቾች አስፈረመ
አሰልጣኝ ቾንቤ በዋና አሰልጣኝነት እየተመራ ምድብ ለ በመሪነት ያጠናቀቀው ነቀምቴ የቀድሞ ሁለት ተጫዋቾቹን ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል።
አምሳሉ መንገሻ ከፈረሙት መካከል ነው። ተከላካዩ ከዚህ ቀደም በነቀምቴ ከተማ የእግርኳስ ህይወቱን የጀመረው አምሳሉ በ2010 በአምበሪቾ በቀጣይም በነቀምት ዘንድሮ ደግሞ ወደ ጌዲኦ ዲላ አምርቶ የተጫወተ ሲሆን በሁለተኛ ዙር ነቀምቴን ለማገልገል ተስማምቷል።
ገዘኸኝ ባልጉዳ ሌላው ተጫዋች ነው። በአጥቂ ሥፍራ የሚጫወተው ገዛኸኝ ከ2011 ነቀምትን ተቀላቅሎ ስምንት ግቦችን ያስቆጠረ ሲሆን በዚህ አመት ወደ ሲዳማ ቡና በመዘዋወር ቆይታ አድርጎ ወደ ቀድሞ ቡድኑ የተመለሰ ሁለተኛ ተጫዋች ሆኗል።
የካ ስድስት አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርሟል
የካ በሁለተኛው ዙር ይበልጥ ጠንክሮ ለመቅረብ የአምስት የሀገር ውስጥ እና አንድ ጋናዊ ዝውውር አጠናቋል።
በወልቂጤ፣ ስልጤ ወራቤ እንዲሁም ሀላባ ሲጫወት የቆየው የፊት መስመር ተጫዋቹ መሐመድ ናስር ወደ ቡድኑ ሲቀላቀል ሌላው የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች ክብረአብ ማቱሳላ ከነቀምቴ፣ የመስመር አጥቂው ዮናስ ሀብቴ ከአራዳ፣ አማካዩ እዮብ ካሳዬ ከደብረማርቆስ እንዲሁም ግብ ጠባቂው ወርቅነህ ዲባባ ከቂርቆስ ከ/ከተማ ለቡድኑ የፈረሙ አዳዲስ ተጫዋቾች ሆነዋል። ቤንጃሚን ኦዱም የተባለ ጋናዊ ተጫዋችም ሌላው የካን የተቀላቀለ ተጫዋች ነው።
አክሱም ከተማ ሦስት ተጫዋቾች አስፈርሟል
በዝውውር መስኮቱ ዝምታን መርጠው የነበሩት አክሱም ከተማዎች ሦስት ጋና እና ናይጄርያዊ ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾችን አስፈርመዋል። ሙሳ አሊዋሴጉን ከአልሸሪፍ፣ አይዛክ ኦዱሮ ከናይጀርያው ደልታ ፎርስ እና አሴይዲ ቤንጃሜን ከአክራ ላዮንስ የፈረሙት ተጫዋቾች ናቸው።
ደደቢቶች የሁለት ተጫዋች ዝውውር አጠናቀቁ
ከዚህ ቀደም ሲሳይ ጥበቡን አስፈርመው ከሁለት ተጫዋቾች ጋር በስምምነት የተለያዩት ሰማያዊዎቹ ብሩክ ገብርአብ እና ኬኔዲ ገብረፃድቅን አስፈርመዋል።
ከጅማ አባጅፋር ጋር በስምምነት ተለይቶ ወደ ቀድሞ ክለቡ ወልዋሎ አምርቶ የነበረው ብሩክ ገብርአብ ቢጫውን ማልያ ሳይለብስ ከክለቡ ጋር በስምምነት ተለያይቶ ወደ ሰማያዊዎቹ አምርቷል። በበርካታ ቦታዎች መጫወት የሚችለው ይህ ተጫዋች ደደቢቶች በፊት መስመር ላይ ያላቸው ጠባብ አማራጭ ያሰፋል ተብሎ ይጠበቃል።
ሌላው ወደ ሰማያዊዎቹ ያቀናው በዘንድሮው የመላው ትግራይ ጨዋታዎች የውድድሩ ኮከብ ተጫዋቾች ተብሎ የተሸለመው ኬኔዲ ገብረፃድቅ ነው። ከወዲሁ ብዙ ተስፋ ተጥሎበት ወደ ቡድኑ ያመራው ይህ ተጫዋች ክለቡ በዝውውር መስኮቱ ያስፈረመው ሦስተኛው ተጫዋች ነው።
የጌዴኦ ዲላ ተጫዋቾች ቅሬታ
በምድብ ሐ እየተፎካከረ የሚገኘው ጌዴኦ ዲላ ተጫዋቾች ደሞዛቸው በወቅቱ አለመከፈሉን በመግለፅ ቅሬታቸውን ገልፀዋል። 27 የቡድኑ ተጫዋቾች ለሦስት ወራት እንዳልተከፈላቸው ቅሬታቸውን የገለፁ ሲሆን በተመሳሳይ በሴቶች ፕሪምየር ሊግ እየተሳተፈ የሚገኘው ቡድን 27 ተጫዋቾችም ለአምስት ወራት እንዳልተከፈላቸው በመግለፅ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ