የኢትዮጵያ ተጫዋቾች ማኅበር ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ የቀድሞ እና የአሁኖቹ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች ከፍተኛ ወጪ የሚያወጣ ቁሳቁስ ልገሳ አድርገዋል።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሀገራችን ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ የሚፈጠረውን ማኀበራዊ ችግር ለመቀነስ በማሰብ የኢትዮጵያ ተጫዋቾች ማኀበር ያስተላለፈውን ጥሪ በመቀበል በቅርቡ የቀድሞ እና የአሁን የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋችች የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸው ይታወቃል። ዛሬ ደግሞ የቀድሞ እና የአሁኖቹ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች በአዲስ አበባ ስታዲየም ከሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽት የቆየ የንፅህና መጠበቂያ ፣ የምግብ እህሎች፣ የምግብ ዘይቶች እና የተለያዮ ቁሳቁሶችን በግላቸው እና ከደጋፊዎች በማሰባሰብ ለማኀበሩ አስረክበዋል።
በዚህ መልካም ተግባር ላይ አዳነ ግርማ፣ ደጉ ደበበ፣ አሉላ ግርማ፣ ፍፁም ገብረ ማርያም፣ ምንተስኖት አዳነ፣ አቤል ያለው፣ ሀይደር ሸረፋ የተገኙ ሲሆን እንዲሁም ሌሎችም ተጫዋቾች ከያሉበት አካባቢ በመሆን ድጋፍ ማድረጋቸውን ለማወቅ ችለናል።
በቀጣዮቹ ቀናትም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች እና ሌሎች ክለቦችም ይህን ዘመቻ እንደሚቀላቀሉ ጉዳዮን በዋናነት ትኩረት በመስጠት እያስተባበረ የሚገኘው የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋች ኤፍሬም ወንድወሰን ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግሯል።
ከማኀበሩ ጎን በመሆን ይህን በጎ ተግባር ለማገዝ የምትፈልጉ ሌሎች አባሎች እና የስፖርት ቤተሰቦች ለዚህ አላማ ማኀበሩ ባዘጋጀው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አካውንት ድጋፍ ማድረግ የምትችሉ መሆኑን ያሳውቃል።
© ሶከር ኢትዮጵያ