የኮሮናን ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል የሚደረገው ድጋፍ የቀጠለ ሲሆን የወላይታ ድቻ የቡድን አባላት የገንዘብ ድጋፍ አበርክተዋል። አሰልጣኞች እና የቀድሞ ተጫዋቾችም የግንዛቤ ማስጨበጫ እና ድጋፍ የማሰባሰብ ስራ አከናውነዋል።
ወላይታ ድቻዎች ከተጫዋቾች፣ የክለቡ አመራሮች እና አሰልጣኞች እንዲሁም በቡድኑ ውስጥ የሚገኙ ሠራተኞች የተሰበሰበ አንድ መቶ ሺህ ብር ለዞኑ የኮሮና ቫይረሰ መከላከል ግብር ኃይል አስረክበዋል። ቡድኑም በቀጣይ በርካታ የገንዘብና ቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚያደርግ ለዞኑ ቃል መግባታቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ ያገኘችው መረጃ ያሳያል።
ክለቡ ከለገሰው ድጋፍ በተጨማሪ የወላይታ ድቻ አሰልጣኝ ደለለኝ ደቻሳ፣ የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ እና የቡዱኑ የቴክኒክ ኃላፊ በሆኑት አቶ ዘላለም ማቴዎስ እንዲሁም በቀድሞ የወላይታ ድቻ ተጫዋቾች ሽመክት ጉግሳ እና በዛብህ መለዮ አስተባባሪነት በወላይታ እና አከባቢዋ የሚገኙ የስፖርት ክለቦች፣ ተጫዋቾች እንዲሁም የክለብ አሰልጣኞች ዛሬ መጋቢት 29 የቡድኑን ባስ በመጠቀም ሰለቫይረሱ መከላከያ ግንዛቤ ሲሰጡ እና የተለያዩ ለአቅመ ደካሞች የሚውል ቁሳቁሶች በማሰባሰብ በጎ ተግባር ያከናወኑ ሲሆን በዚህም መሠረት ከ25 ሺህ ብር በላይ በሚጠጋ ወጪ የተገዙ የእጅ ማጽጃ ሳኒታይዘሮች፣ ምግቦችን (መኮረኒ፣ ሩዝ እና የስንዴ ዱቄት እና ሌሎችንም) በማሰባሰበ በዞኑ ለተቋቋመው የበሽታው መከላከያ ግብረ ኃይል አስረክበዋል።
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ