(መረጃው የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን ነው።)
በኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን አስተባባሪነት የሀገር አቀፍ ስፖርት ማኅበራት እና የአትሌቶች ማህበር የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚውል የ3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አበረከቱ ።
በዓለማችን ብሎም በሀገራችን በፍጥነት እየተስፋፋ የመጣውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል መንግስት የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ተማቋቋሞ የተለያዩ ድጋፎችን በማሰባሰብ ላይ ይገኛል ፡፡
መንግስት ያቀረበውን የድጋፍ ማሰባሰብ ጥሪ በመቀበል የኢፊድሪ ስፖርት ኮሚሽን ሀገር አቀፍ የስፖርት ማህበራት እና የአትሌቶች ማህበርን በማስተባበር ያሰባሰበውን 3 ሚሊዮን ብር ለብሔራዊ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ በአዲስ አበባ ስታዲየም በመገኘት አስረክቧል ፡፡
በርክክብ ስነ ስርዓቱ በመገኘት ድጋፉን ያስረከቡት የኢፊድሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኤሊያስ ሽኩር እንዳሉት “የኮሮና ቫይረስ ዓለማችንን በከፍተኛ ሁኔታ እያስጨነቀ እና ለዜጎች ህልፈተ ህይወት ምክንያት የሆነ ወረርሽኝ መሆኑን ጠቁመው ፤ ወረርሽኙ በዓለም እና በሀገራችን ኢኮኖሚያዊ ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ ባሻገር በስፖርቱ ረገድም በውድድሮች እና ስልጠናዎች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ የፈጠረ እና ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ያስቆመ ተግባር ነው ብለዋል ።
በመሆኑም የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል እና የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ በሚደረገው ርብርብ የስፖርት ቤተሰቡ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ ይገኛል ብለዋል ፡፡ በዛሬው ዕለትም የሀገር አቀፍ ስፖርት ማህበራት እና የአትሌቶች ማህበር ከአላቸው ውስን በጀት እና ሀብት ላይ በመቀነስ ቫይረሱን ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት አጋርነታቸውን አሳይተዋል ሲሉ ከምስጋና ጋር ገልፀዋል ፡፡ ወረርሽኙ እስኪጠፋ ድረስ በግልም ይሁን በቡድን የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል ፡፡
ኮሚሽነሩ አያይዘውም እያንዳንዱ ዜጋ ቫይረሱን ለመከላከል መንግስት እና የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን መመሪያዎች ሳይሰለች መተግበር እንደሚገባ እና ቫይረሱን ለመከላከል ከቤት ውጭ የሚደረገውን እንቅስቃሴ በመገደብ እቤት ውስጥ መቀመጥ እንደሚገባ ገልፀዋል ፡፡ ከቤት ውስጥ ስንቀመጥም ከጭንቀት እና ከድብርት ለመውጣት ቀለል ያሉ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል ፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተ/ፕሬዝዳንት አትሌት ኮሮኔል ደራርቱ ቱሉ በበኩሏ ሆቴል ያለው ሆቴሉን ፤ መኪና ያለው መኪናውን ገንዘብ ያለው ገንዘቡን በመለገስ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ድጋፉን እያሳየ ነው በዚህም ኢትዮጵያዊ በመሆነ ኮርቻለሁ ብላለች ፡፡ በመሆኑም እኛ ኢትዮጵያዊያን ተባብረን እና አንድ ሆነን የቫረሱን ስርጭት ልንከላከል ይገባል ፤ አሁን ከምንም ጊዜ በላይ ከህዝባችን ጎን የምንቆምበት ነው ፤ ሁላችንም በአለን አቅም ልንረባረብ ይገባል ስትል መልዕክቷን አስተላልፋለች ፡፡ ስፖርተኞች ፣ አሠልጣኞችና ማናጀሮች ሳንዘናጋ በአለንበት እራሳችንን እየጠበቅን ፤ ምን እና እንዴት ልስራ የሚለውን እያቀድን ልምምድ ልናደርግ ይገባል ብላለች ፡፡
የተሰበሰበውን ድጋፍ የተረከቡት የብሔራዊ የኮሮና ቫይረስ ድጋፍ አሰባሳቢ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር ምስጋናው አረጋ በበኩላቸው ፤ ስፖርት ከማዝናናት ባለፈ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው ፤ ሀገራችን አሁን ያለችበት ሁኔታ እና ወረርሽኙን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ትልቅ አቅም እና ብሔራዊ አንድነትን ፤ መተባበርን የሚጠይቅ ሲሆን፤ በእንደዚህ ዓይነት ሀገራዊ ጥሪ ቅድሚያ ተሰላፊ የሆነው የስፖርት ቤተሰብ ይህንን ተረድቶ ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ ስለሆነ በብሔራዊ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል ፡፡ መሰል ድጋፎችም ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አምባሳደሩ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል ፡፡
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ