ከአራት ወራት ገደማ በፊት ከቻይናዋ ሁዋን ግዛት የተነሳው የኮሮና ቫይረስ ከፍ ባለ ፍጥነት እየተሰራጨ ለዓለም ሀገራት ከፍ ያለ የራስ ምታትን ፈጥሯል። ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያም ቫይረሱ ዘግየት ብሎ ቢገባም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ከዕለት ወደ ዕለት እያሻቀበ ይገኛል።
መንግስት የዚህን ቫይረስ ስርጭት ለመግታት ከአንድ ወር በፊት በወሰደው እርምጃ መሰረት ስፖርታዊ ውድድሮች በቅድሚያ ለ15 ቀናት ቀጥሎም ላልተወሰነ ጊዜ መቋረጣቸው የሚታወስ ነው። ታድያ ይህ ክስተት በርከት ያሉ አሉታዊ ተፅዕኖዎች ማሳደሩ አይቀሬ ይመስላል። ሁሉም የሀገር ውስጥ የእግርኳስ ውድድሮች ገና እኩሌታቸው ላይ በሚገኙበት በዚህ ወቅት መቋረጣቸውን ተከትሎ በርካታ መፍትሔ የሚሹ ጥያቄዎች ተደቅነዋል። እኛም የተወሰኑትን ጥያቄዎች ለመዳሰስ እንሞክራለን።
የሊጎቹ ቀጣይ እጣ ፈንታ
በተመጋጋቢው የሊጉ ስርዓት ውስጥ በወንዶቹ ከፕሪምየር ሊጉ እስከ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና እንዲሁም በሴቶቹ ደግሞ ከፕሪምየር ሊጉ እስከ ሁለተኛ ዲቪዝዮኑ ባለው የውድድር መዋቅር የሚገኙ ክለቦች በዓመቱ በሚያስመዘግቡት ውጤት አንፃር በሁለቱ የሰንጠረዡ ፅንፎች የሚመዘገቡ ደረጃዎች ከፍ ያለ ትርጉም የሚሰጣቸው መሆኑ ይታወቃል።
ይህ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ በዚህ ጊዜ ያበቃል የሚለውን ቁርጥ ያለ ቀን ማስቀመጥ ካለመቻሉ ጋር ተያይዞ የእነዚሁ ውድድሮች ቀጣይ እጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት በጣም አስቸጋሪ ነው። መሰል ችግሮች በሚገጥሙበት ወቅት ውድድሮች በምን መልኩ ይቋጫሉ በሚለው ጉዳይ ዙርያ በግልፅ የተቀመጠ አንቀፅ ባለመኖሩ ውድድሩ በምን መልኩ ይቋጫል የሚለው ጉዳይ ለተለያዩ መላ ምቶች ክፍት እንዲሆን ያስገደደ ሆኗል።
ነገርግን ውድድሮቹን በበላይነት የሚመሩት አካላት በዚህ ወቅት ከክለቦች ጋር ለውይይት ሊቀርቡ የሚችሉ አማራጮችን ማዘጋጀት ይኖርበታል። ለዚህም ስርጭቱን በፍጥነት መቆጣጠር ከተቻለ እንዲሁም ረዘም ያለ ጊዜ ቢወስድ በሚሉ ሁለት ፅንፎች የተቃኙ አማራጮችን ያዘሉ የውድድር ንድፎችን (proposal) ማዘጋጀት የግድ የሚል ይመስላል። ለወትሮውም ቢሆን እርስ በእርስ በጥርጣሬ የሚተያዩት ክለቦቻችን በመሰል አስገዳጅ የውድድር ንድፎች ተዘጋጅተው የማሰብያ አውዳቸው ካልታጠረ በውይይት ይስማማሉ ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው።
የውድድር አካሄዱ ምን መምሰል ይኖርበታል የሚለውን በሌላ ፅሁፍ የምንመለስበት ቢሆንም ቫይረሱ በቁጥጥር ስር በቶሎ የሚውል ከሆነና ምናልባትም በክረምት ውድድሮችን የማካሄድ አማራጭ የሚወሰድ ከሆነ የአየር ሁኔታው፣ የተጫዋቾች ኮንትራት ጉዳይ፣ የቡድኖች የሜዳ ላይ የብቃት ደረጃ እና ፋይናንስ ዝግጁነት ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባቸው ናቸው። ቫይረሱ በቁጥጥር ስር የመዋሉ ጉዳይ ረጅም ጊዜያትን የሚወስድ ከሆነ ግን ውድድሩን ለቀጣይ ዓመት ማዞር አዳጋች ይመስላል። ሊጎቹ ባሉበት ይዞታ እንዲጠናቀቁ በማድረግ ለመሪዎቹ ቡድኖች አሸናፊነትን ለመስጠት ቢወሰን ውድድሮቹ ገና አጋማሽ ላይ ከመሆናቸው ጋር በተገናኘ የሚኖራቸው ቅቡልነት አጠራጣሪ ነው። በዚህም በ30 ዓመታት ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ ውድድር ያልተደረገበት / አሸናፊ የሌለበት የውድድር ዓመት ሆኖ የመመዝገብ ዕድልም ይኖረዋል።
የተጫዋቾች ኮንትራት ጉዳይ
በእዚህ ዙርያ ሌሎች ልብ ሊባል ከሚገቡ ጉዳዮች ውስጥ የተጫዋቾች የኮንትራት ጉዳይ አንዱ ነው። እንደሚታወቀው በሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ የውድድር ወቅት የሚባለው ከመስከረም መጨረሻ እስከ ሰኔ መጨረሻ እንደሆነ ይታወቃል። ይህም ውድድሩ ከሰኔ 30 በኋላ ባሉት ጊዜያት የሚቀጥል ከሆነ ውላቸውን በወቅቱ የሚያበቁ ተጫዋቾችን ሁኔታ የሚዳኙ ደንቦች መዘጋጀት ይኖርባቸዋል። ለዚህኛው ሁኔታ ግን የኢትዮጵያ እግርኳስ ከዚህ ቀደም ልምዶቹ በመነሳት ምላሽ የሚኖረው ይመስላል። ከዚህ ቀደም ለበርካታ ጊዜያት ውድድሮች በክረምት ሲጠናቀቁ ተጫዋቾች ከውላቸው ውጪ እንዲጫወቱ ሲገደዱ ተስተውሏል።
የኮሮና ቫይረስ ተፅዕኖ እየተራዘመ መሄድ በእግርኳሱ ከሁሉም በበለጠ ተጫዋቾችን የሚጎዳ ይመስላል። ለዘመናት እንደ ባህል በተያዘው የአጭር ጊዜያት ውሎችን የመዋዋል አካሄድ ምክንያት በሀገሪቱ ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ተጫዋቾች ኮንትራት ዘንድሮ ሰኔ 30 የሚጠናቀቅ ሲሆን ቫይረሱ ምናልባትም ለረጅም ጊዜ ከቆየ ውላቸው የሚጠናቀቅ ተጫዋቾች ያለ ክለብ በመቆየት ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸው አይቀሬ ነው።
የፋይናንስ ቀውስ
እንደሚታወቀው ከፊታችን የተደቀነው የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ለመግታትም ሆነ በድህረ ኮሮና የሚኖሩትን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን ለመቀልበስ ከመንግስታት እስከ እያንዳንዱ ግለሰቦች ድረስ የሚደረግ የተቀናጀ ጥረት እንደሚጠይቅ ይታወቃል።
በተለያዩ የዓለም መንግስታት ስርጭቱን ለመቆጣጠር የተወሰኑት የእንቅስቃሴ ግደባ እና ተቋማትን የመዝጋት ውሳኔዎች በርካታ ሰዎችን ስራ አጥ ከማድረግ አንስቶ በተለይ እንደ ሀገራችን ኢትዮጵያ አይነት ደከም ያለ የኢኮኖሚ አቅም ያላቸው ሀገራት ላይ የዜጎችን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫና መፍጠሩ አይቀሬ ነው።
በቅርቡ ዓለምአቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) ይፋ እንዳደረገው ከሆነ በዓለምአቀፍ ደረጃ ኢኮኖሚው ከዜሮ በታች 3% እንደሚያሽቆለቁል ተንበይዋል። ይህም በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉት ሀገራት ላይ እስከ ከዜሮ በታች 5.1% ሊደርስ እንደሚችልም ተገልጿል። በሀገራችን ደረጃ በመንግስት የስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን በተሰራው ትንበያ መሰረት ከ1.4 ሚልየን እስከ 2.5 ሚልየን የሚጠጉ ዜጎች በቀጣዮቹ ከሶስት እስከ ስድስት ወራት ስራቸውን ሊያጡ ይችላል ተብሏል።
ወደ እግርኳሱ አውድ ስናመጣው በተለይ እንደ እኛ አይነት በመንግስት የሚዘወሩ የእግርኳስ ክለቦች ባላቸው ሀገራት ይቅር እና ራሳቸው ከተለያዩ የገቢ ማግኛ አማራጮች በሚያመነጩት ገቢ የሚተዳደሩት የአውሮፓ ክለቦች እንኳን የክለባቸውን ሰራተኞች ወርሃዊ ደሞዝ ለመክፈል እየተንገራገጩ ባለበት በዚህ ወቅት የሀገራችን ክለቦች በዚህ አስከፊ ጊዜ እንዴት ምላሽ እንደሚሰጡ ማሰብ እጅግ አስጨናቂ ነገር ነው።
ከ90% ያላነሱ የሀገራችን ክለቦች በመንግስት እና ከከተማ አስተዳደሮች የገንዘብ ቋት በሚፈስ ገንዘብ የሚዘወሩት የሀገራችን ክለቦች እንኳን ዘንቦብሽ እንደሚባለው በደህናው ጊዜ ኢ-ስፖርታዊ በሆነ አመክንዮ ራሳቸው ወደ ሰማይ በሰቀሉት የተጫዋቾች የደሞዝ ጣርያ ካዝናቸው ተሟጦ ደሞዝ ለመክፈል አቅም አጥተው መተራመስ ከጀመሩ ሰንበትበት ብሏል።
ቫይረሱን ለመዋጋት በሚደረገው ጥረት የተሻለ ኢኮኖሚ እና የህክምና መሠረተ ልማት ባለቤት የሆኑት ያደጉት ሀገራት እንኳን በተቸገሩበት በዚህ ወቅት የሀገራችንም መንግስት ይህን በመገንዘብ ቫይረሱን ለመመከት የመንግስት ሀብት ብቻ በቂ ባለመሆኑ ከህብረተሰቡን በተለያዩ መልኮች ሀብት በማሰባሰብ ላይ ይገኛል።
መንግስትም ለመጠባበቂያነት ይዟቸው የነበሩት ሀብቶች በሙሉ ይህን ወረርሽኝን ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት እያዋለም እንደሚገኝ እያስተዋልን ይገኛል። ይህም በሀገሪቱ መፃኢ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ለዓመታት የሚዘልቅ ተፅዕኖ ይኖረዋል ተብሎ ሲገመት ይህ ተፅዕኖ የሚነካው አንዱ ስፖርቱ በተለይም እግርኳሱ እንደሚሆን ይገመታል።
በአጠቃላይ ወደ 2 ቢልየን የሚጠጋ ሀብት ከሚዘዋወርበት የሀገራችን ስፖርት ውስጥ ከፍ ያለውን ድርሻ የሚወስደው እግርኳሱ እንደሆነ ይታወቃል። በመሆኑም ድህረ ኮሮና በ2013 በጀት ዓመት መንግስት ትኩረቱ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው በቀጣይ ወራት ክፉኛ መንገራገጭ የሚገጥመውን የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ለማነቃቃት የኢኮኖሚው ምሶሶ የሆኑ እንደ የወጪ ንግድ እንዲሁም ሌሎች ከፍ ያለ የኅብረተሰብን ክፍል ወደ ስራ ሊያስገቡ የሚችሉ የኮንስትራክሽን እና አገልግሎቱን ዘርፍ ለማነቃቃት በሚደረገው ጥረት መነሾነት የእግርኳስ ዘርፉ በመንግስት የሚደረግለት ድጋፍ ማሽቆልቆል እንደሚያሳይ ይገመታል።
ይህም ክለቦቻችን እንደከዚህ ቀደሙ ያለ ጠያቂ እንደልብ ይፈስላቸው የነበረው በጀት መንግስት እጁን የሚሰበስብ ከሆነ መላ ቅጥ አጥቶ የነበረውን የክለቦች የፉይናንስ አወጣጥን መልክ ሊያሲዝ እንደሚችል ይገመታል። ክለቦችም ከዘልማዳዊ አሰራር በመውጣት በተወሰነ በጀት ክለባቸውን በውድድር ዘመኑ ተወዳዳሪ ሆነው እንዲዘልቁ ለማስቻል በስክነት አዳዲስ መንገዶችን እንዲቃኙ ያስችላል ተብሎ ይጠበቃል።
በተለይ ክለቦች እንደ በፊቱ ረብጣ ሚልየኖችን እያፈሰሱ የበቁ ተጫዋቾችን ከማዘዋወር ይልቅ ታዳጊ ተጫዋቾች ማብቃት እና መጠቀም ላይ ይበልጥ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ የሚያስገደድ ይመስላል። ይህም በጥቂት ዓመታት ያልተጠበቀ የሰላ የዋጋ ንረት ያሳየው የተጫዋቾች ዋጋ ለማርገብ አይነተኛ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።
በተጨማሪም ሀገሪቱ ይገጥማታል ተብሎ ከሚጠበቀው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ጋር ተዳምሮ በገፍ ወደ ክለቦች ይዘዋወሩ የነበሩት የውጭ ሀገራት ተጫዋቾች ቁጥርም እንዲሁ ሊቀንስ እንደሚችል ሲገመት ይህም ለብሔራዊ ቡድናችን በተወሰኑ የመጫወቻ ቦታዎች ላይ ለተጫዋቾች ምርጫ የጠበበ የሚመስለውን የመምረጫ አድማስን ማስፋት ሌላኛው ቱሩፋት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
በተመሳሳይ በቅርቡ የኢትዮጵያ ቡናው ስራ አስኪያጅ ከአንድ ሚዲያ ጋር በነበራቸው ቆይታ ክለባቸው ከሜዳ ገቢ በ2012 የውድድር ዘመን የመጀመሪያ ዙር ብቻ 5.5 ሚልየን ብር ማግኘታቸው ሲገልፁ ተደምጧል። ይህም አሁን ላይ ውድድሮች በመቋረጣቸው በቀጥታ ተቀራራቢ መጠን ያለው ገንዘብ እንደሚያጡ ይጠበቃል። በተመሳሳይም ከሜዳ ገቢ እና ከስፖንሰርሺፕ ስምምነት በሚገኙ ገቢዎች የሚንቀሳቀሱ ክለቦች በተመሳሳይ የዚህ ገፈት ቀማሽ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የክለቦቹ ስፖንሰሮች በአንድም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ መቀዛቀዝን እያሳየ ከሚገኘው የዓለም አቀፍ ገበያ ሆነ የሀገራችን ገበያ ገፈት መቅመሳቸው አይቀርም።
ረጅም እረፍት እና የተጫዋቾች አካል ብቃት
የዚህን አሰከፊ ወረርሺኝ ወደ ሀገራችን መግባት ተከትሎ የሀገራችን ክለቦች ወደ እረፍት ካመሩ ወደ አንድ ወር የሚጠጋን ጊዜ አሳልፈዋል። በዚህ ወቅትም ተጫዋቾች በቤታቸው ሆነው የአካል ብቃታቸውን ጠብቀው እንዲቆዩ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እንዲያደርጉም ይመከራል። ይህ የእረፍት ወቅት ሁለት ወርን ከተሻገረ ውድድሩ እንኳን ይቀጥል ቢባል ተጫዋቾች የቀደመ የአካል ብቃት ደረጃቸውን እንዲያገኙ ዳግም ከ6-8 ሳምንት የሚሆን የቅድመ ውድድር ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው ባለሙያዎች ይመክራሉ።
ነገር ግን በሀገራችን ስፖርት ውስጥ ካለው የደካማ የአካል ብቃት አረዳድ ጋር በተያያዘ ተጫዋቾች ይህን ወቅት የሚጠበቅባቸውን እንቅስቃሴ በማከናወን ከሚጠበቅባቸው የአካል ብቃት ደረጃ በቀረበ መልኩ ስለመገኘታቸው እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም። የሀገራችን ተጫዋቾች በአውሮፓ ሀገራት እንደምንመለከተው ሁሉን ያሟላ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማከናወኛ ቁሳቁሶች እና ቀላል የእግርኳስ እንቅስቃሴዎችን የሚያደርጉበት ስፍራ በቤታቸው አይገኝም። ይህን ተከትሎም የክለቦች የአሰልጣኞች ቡድን አባላት ከፍ ያለ የቤት ሥራን መወጣት ይጠበቅባቸዋል። ራሳቸውን ከቫይረሱ ለመጠበቅ የሚወሰዱ ቅድመ ጥንቃቄዎችን በማድረግ በመኖርያ አካባቢያቸው የአካል ብቃት ደረጃቸውን የማሻሻልም አማራጮን መውሰድም ሳይኖርባቸው አይቀርም።
እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ