የጆናታን ዊልሰን Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics የአማርኛ ትርጉም ማቅረባችንን ቀጥለን በዛሬው መሠናዶ የምዕራፍ ዘጠኝን ሁለተኛ ክፍል ወደ እናንተ ማድረስ እንጀምራለን።
በቪክቶር ማስሎቭ የአሰልጣኝነት ህይወት ውስጥ የፈላጭ ቆራጭ አመራር አልነበረም፡፡ እንዲያውም ኋላ ላይ የእርሱ ታላቅ ደቀመዝሙር በሆነው ቫለሪ ሌቫኖቭስኪ ዘንድ ይህ አይነቱ ቡድን የማስተዳደር ሥርዓት በሰፊው ታይቷል፡፡ ማስሎቭ ልዩነትን ለመፍታት በመወያየት ያምን ነበር፡፡ አልፎአልፎም ተጫዋቾቹ የበለጠ ሥልጣን እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡ በ1960ዎቹና 1970ዎቹ ዘመናት በጣም ስመጥር ከነበሩት የእግርኳስ ጋዜጤኞች መካከል አንዱ የሆነው አርካዲ ጋሊንስኪ ” በአንድ የቶርፒዶ ክለብ የሊግ ጨዋታ ወቅት ለሜዳው ቀርቤ በተቀያሪዎች ማረፊያ አካባቢ ተቀምጫለሁ፤ ቶርፒዶዎች ሜዳ ላይ ጥሩ እየተንቀሳቀሱ አልነበሩምና አሰልጣኙ አንዱን ተጫዋች ሊቀይረው ወሰነ፡፡ ተቀይሮ የሚገባው ተጫዋች ጃኬቱን አውልቆ መጠነኛ የማማሟቅ ልምምድ አድርጎ ወደ መሃለኛው የሜዳ ጠርዝ አመራ፡፡ ዳኛው ጨዋታውን አስቁሞ እስኪገባ ድረስ ይጠብቅ ጀመር፡፡ ሒደቱ ሁሌም በእግርኳስ የሚካሄድ መደበኛ ክንውን ነበር፡፡ ቀጥሎ የተመለከትኩት ግን እጅግ ትኩረቴን ሳበው፡፡ ዳኛው ጨዋታው እንዲቆም የፊሽካቸውን ድምጽ ሲያሰሙ ዝነኛው የቡድኑ አጥቂና አምበል ቫለንቲን ኢቫኖቭ መስመሩ ላይ ቆሞ ወደ ሜዳ ለመግባት በመጠባበቅ ላይ ወደሚገኘው ተጫዋች እየሮጠ መጣና ቡድኑ ምንም አይነት ቅያሪ እንደማያስፈልገው ነገረው፡፡ ተጫዋቹ ለጥቂት ጊዜያት በግራ መጋባት ውስጥ ከቆየ በኋላ ወደ ተቀያሪዎች ወንበር ተመለሰ፡፡ ‘እንዲያው ማስሎቭ ምን አይነት አጸፋ ያሳይ ይሆን?’ በሚል አይኔን ወደ አሰልጣኙ ሳማትር እርሱ ጭራሽ በግዴለሽነት ስሜት ትከሻውን ወደላይ ሲሰብቅ አስተዋልኩት፡፡ በተፈጠረው ነገር ምንም የተለየ ስሜት አልተስተዋለበትም፡፡ እኔማ ሜዳ ላይ ሊቀየር የታሰበው ተጫዋች እንዲነቃቃ በአሰልጣኙና በአምበሉ አማካኝነት ሆን ተብሎ የተደረገ ሙከራ መስሎኝ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በአሰልጣኙ የቀረበውን የቅያሪ ትዕዛዝ ሜዳ ላይ ያለው ቡድን አልቀበልም ማለቱ እውነታ ሆነ፡፡ እንዲህ ያለውን ነገር ከዚያ ቀደም በእግርኳስ ፈጽሞ ተመልክቼ አላውቅም፡፡ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ግን ይህን የቅያሪ እምቢታ ድጋሚ ልመለከት ቻልኩ፡፡ ጨዋታው የተካሄደው በተመሳሳይ ስታዲየም ነው፡፡ በሞስኮው በሚገኘው የሌኒን መታሰቢያ ስታዲየም (የአሁኑ ሉዥኒክ ስታዲየም) በተደረገው በዚህም ጨዋታ አሰልጣኙ ራሱ ማስሎቭ ነበር፡፡ ቡድኑ ግን ይለያል፤ ዳይናሞ ኪዬቭ፡፡ ድርጊቱ ሲከሰት ማስሎቭ አሁንም ‘ምን ገዶኝ!’ አይነት አቋም አሳይቷል፡፡” በማለት ጽፏል፡፡
አርካዲ ጋሊንስኪ በኪዬቭ የ<ሶቮቴስኪ ስፖርት> ጋዜጣ አምደኛ ሳለ ወደ ሞስኮው ባደላ ድጋፉ ይታወቃል፡፡ ዳይናሞ ኪዬቭ የሚጠቀመውን በቀጠና የመከላከል ዘዴ (Zonal Marking System) አዘወትሮ ሲተች ታይቷል፡፡ ከቪክቶር ማስሎቭ ጋርም ግላዊ ተራ ግጭት ውስጥ የገባ ይመስል ሁሉ ነበር፡፡ ቢባ ግን ይህን ጉዳይ ብዙም ክብደት አይሰጠውም፡፡ እንዲያውም ማስሎቭ አንዳንዴ ከጠንቃቃነቱ ይልቅ የዋህነቱ የሚያመዝንበት ሰው እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ጋሊንስኪ በሁለቱ አጋጣሚዎች የተመለከታቸው ሁኔታዎች የማስሎቭን ድክመት የሚያሳብቁ እንዳልሆኑ ሞጋች ድምዳሜ ያቀርባል፡፡ ከዚያ ይልቅ የሰውዬው ጥንካሬ ማሳያዎች ስለመሆናቸው ይከራከራል፡፡ ” ተጫዋቾቹ ቅያሪውን ያለመቀበላቸው የእርሱን ክብር ለማውረድ አልያም ትዕዛዙን ላለመተግበር አስበው እንዳልሆነ ይረዳል፡፡ ለቡድኑ ጥቅም ሲሉ የፈጸሙት መሆኑ ይገባዋል፡፡ እንደ ቶርፒዶዎቹ ሁሉ የዳይናሞዎቹም ተጫዋቾች ለአሰልጣኛቸው መልዕክት እያስተላለፉ ነበር። ‘ አንተ አትጨነቅ፤ ሁሉም ነገር መልካም ነው፡፡ አሁኑኑ በጨዋታው የበላይነታችንን እናረጋግጣለን፡፡’ እያሉት ነበሩ፡፡ በሁለቱም ጨዋታዎች የተፈጠረው፥ እነርሱም ያደረጉት ያሉትን ነው፡፡” ብሎ በጽሁፉ ያወሳል፡፡
ውይይትና የጋራ ምክክር በቪክቶር ማስሎቭ የአሰልጣኝነት ህይወት ውስጥ ትልቅ ስፍራ የሚሰጣቸው ቁልፍ ግብዓቶች ናቸው፡፡ ከእያንዳንዱ ጨዋታ በፊት የቡድኑን አጠቃላይ አባላት ይሰበስብና ካልሆነም አንጋፎቹን ተጫዋቾች ይጠራና በቀጣዩ ጨዋታ ዙሪያ ያለውን ጉዳይ ያወያያቸዋል፡፡ የጨዋታ የመጨረሻ ዕቅዱን ከማውጣቱ በፊትም የእነርሱን ሐሳብ ይመረምራል፡፡ ይህ አይነቱ መተማመን እና የጋራ መግባባት ነው ማስሎቭ እንዳሻው ስር ነቀል ታክቲካዊ ግኝቶች ላይ እንዲያተኩር የሚያግዘው፡፡ በዚያን ግዜ የማስሎቭ ቡድኖች አዳዲስ ነገሮችን የሚተገብሩ ከመሆናቸውም በላይ ተጋጣዎቻቸው የእነርሱን አቀራረብ በቀላሉ ለመረዳት አዳጋች ነበሩ፡፡
በ1960ዎቹ መጀመሪያ በሌላው ዓለም እንደሆነው ሁሉ በሶቭየት ህብረትም 4-2-4 እየተለመደ መጣ፡፡ ለዚህም በወቅቱ የሃገሪቱ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ የነበረው ጋቭሪል ካቻሊን ፈር ቀዳጅ ሆነ፡፡ ካቻሊን በ1956ቱ የኦሎምፒክ ውድድር ሶቭየት ህብረት ባለ ድል እንድትሆን ከማድረጉም በላይ በአውሮፓ ሃገራት ዋንጫ ጅማሮ በW-M ፎርሜሽን ስኬታማ መሆን ችሏል፡፡ አሰልጣኙ በ1958ቱ የዓለም ዋንጫ ብራዚል ተዓምራዊ ብቃት ባሳየችበት ወቅት ቀጣዩ የእግርኳስ አጨዋወት አቅጣጫ ወዴት እያመራ እንደነበር ሳይረዳ አልቀረም፡፡ በጊዜው በርካታ የክለብ አሰልጣኞች የእርሱን ፈለግ ተከተሉ፤ በተደጋጋሚ የወግ አጥባቂነት እንተጸናወተውና አላስፈላጊ ውጣ ውረድ በሚያበዛ የአሰራር ሥርዓት ተተብትቦ የታየው የሶቭየት እግርኳስ ተቋም ካቻሊን ታክቲካዊ ሙከራዎቹን በተግባር እንዲፈትሽ እገዛ አደረገለት፥ ለተወሰኑ ጊዜያት ያህል ቢሆንም፡፡ ለውጡ ወይም ተጫዋቾች ከለውጡ ጋር ለመዋሃድ የወሰደባቸው ጊዜ በ1962ቱ የዓለም ዋንጫ ብሄራዊ ቡድኑ ባሳየው ወጥ ያልሆነ አቋም ሳቢያ የካቻሊን ጥረት ተብጠለጠለ፡፡ ሃገሪቱ በውድድሩ ዩጎዝላቪያና ኡሯጓይን ብትረታም በሩብ ፍጻሜው በአዘጋጇ ሃገር በመሸነፏ ብዙም ሳትጓዝ ከቺሊ ተሰናበተች፡፡ ይህም በሩሲያ የአሰልጣኙ ሥልት ላይ ተቃውሞ እንዲበረታ ገፋፋ፡፡ ካቻሊን ከመንበሩ ተነስቶም ኮንስታንቲን ቦስኮቭ በአሰልጣኝነቱ ወንበር ተቀመጠ፡፡ ቦስኮቭ ለአስራ ስምንት ወራት በስራው ላይ ሲቆይ በስሱም ቢሆን የብራዚሎችን የአጨዋወት መንገድ እንዳስቀጠለ ቢደሰኩርም በገሃድ የታየው ግን ከ4-2-4 ይልቅ W-M (3-2-2-3) ፎርሜሽንን መተግበሩ ነበር፡፡
ማስሎቭ ከቦስኮቭ በተሻለ ብልህ ነበር፡፡ ልክ እንደ አልፍ ራምሴይ እርሱም ለብራዚሎች ስኬታማ ጨዋታ ማሪዮ ዛጋሎ ከፊተኛው መስመር ወደኋላ አፈግፍጎ በሶስተኛ የመሃል አማካይነት የሚወጣውን ወሳኝ ድርሻ ተገንዝቧል፡፡ ማስሎቭ ከዚህም ራቅ ባለ መልኩ አሰበ፡፡ እርሱ በማጥቃት ክፍሉ የቀኝ መስመር የሚሰለፈውንም ተጫዋች (Right-Winger) ወደኋላ የመሳብ ፍላጎት አደረበት፡፡ ራምሴይ የመስመር አማካይን ሚና በማደብዘዝ ረገድ ሙገሳውም ወቀሳውም ተፈራርቆበታል፡፡ በእነዚያ ዘመናት በሶቭየትና ምዕራባውያን ሃገሮች መካከል ዓለም አቀፋዊ ግንኙነቱ ተቆርጦ ስለነበር በዚህ የመስመር አማካዮች አጠቃቀም ጉዳይ ዙሪያ ያመጣው ለውጥ ራምሴይ ለብቻው ያደረገው ይሁን-አይሁን ማረጋገጫ ባይኖርም ለመጀመሪያ ጊዜ 4-4-2 ፎርሜሽንን በመፍጠር ረገድ ግን ቪክቶር ማስሎቭ ቀዳሚ ነው፡፡
ማስሎቭ የመስመር አጥቂዎቹ (Outside Forwards) የፈጠራ አቅም ላይ ጥገኛ ሳይሆን እነርሱኑ ወደኋላ እየሳበ ያጫውት ነበር፡፡ ይህን አጨዋወት ሌሎች አሰልጣኞች ሊከተሉት ባይወዱም አልፍ ራምሴይ ግን ተግብሮት ታይቷል፡፡ አንድሪይ ቢባ፣ ቪክቶር ሴሬብሪያንኮቭና ጆዜፍ ዛቦን የመሳሰሉት ተጫዋቾች በቪክቶር ማስሎቭ አማካኝነት የመሃል ሜዳ አማካዮች (Midfielders) ከመሆናቸው በፊት አጥቂዎች (Forwards) ነበሩ፡፡ መደበኛ የአማካይነት ሚና (Orthodox Halves) የነበራቸው ቮሎድሚር ሙንቲያን እና ፌዲር ማድቪድ አይነቶቹ ደግሞ ሁለተኛ የአግድሞሽ የማጥቃት መስመር እየሰሩ ለቡድናቸው የፈጠራ ምንጭ ሆነው ዘልቀዋል፡፡ በእርግጥ አንዳንዴ መጥፎ አጋጣሚዎች ተከስተው ታይተዋል፡፡ ማስሎቭ ከተጫዋቾቹ ጋር ጥሩ ስምምነት መስርቶ የሚሰራ አሰልጣኝ ቢሆንም ለእርሱ አጨዋወት ፍጹም ብቁ ያልሆነ ተጫዋች ከገጠመው ግን ምህረት የለሽ እንደሆነ በተደጋጋሚ አረጋግጧል፡፡ የቀድሞዎቹ ከዋክብት ቪክቶር ካኔቭስኪና ኦሌህ ባዝሌቪች በፍጥነት የመባረር ዕጣ ከደረሳቸው መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ እጅጉን የሚያስገርመው ደግሞ ቫለሪ ሌቫኖቭስኪም ይኸው የማስሎቭ በትር ያረፈበት መሆኑ ነው፡፡
የሁሉቱ ሰዎች አለመስማማት እውነት ከሆነም ማስሎቭና ሌቫኖቭስኪን ያላግባባቸው ጉዳይ እስካሁን ግልጽ አልተደረገም፡፡ አሰልጣኞቹ በአጨዋወት ሥልት በተለያዩ ጎራዎች የሚመደቡ ናቸው፡፡ የእግርኳስ አመለካከታቸውም ለየቅል ነበር፡፡ የጋሊንስኪ መረጃ ተዓማኒ ከሆነ ሁለቱ ሰዎች ሥር የሰደደ የእርስ በርስ ግላዊ ቁርሾ ነበራቸው፡፡ ጋሊንስኪ ሌባኖቭስኪን ከዩክሬይን ወደ ሞስኮ እንዲያመራ ከሚያባብሉት ሰዎች መካከል አንዱ መሆኑን ልብ ማለት ይገባል፡፡ ስለዚህ እርሱ ላይ የሚንተራሰው መረጃ ሙሉ በሙሉ ከድጋፍ ስሜት የጸዳ ሊሆን እንደማይችል ይገመታል፡፡ እንደ ጋዜጠኛው የሁነቶች እይታ በሁለቱ ሰዎች መካከል የተፈጠረው ችግር እየተካረረ የሄደው የ1964 የውድድር ዘመን ከመጀመሩ በፊት በካውካስያኑ የጥቁር ባህር ዳርቻ አካባቢ በነበረው የልምምድ ማዕከል ነው፡፡
” ሁሉም ነገር በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነበር፡፡ ተጫዋቾቹ ከአዲሱ አሰልጣኛቸው ጋር በፍቅር ወድቀዋል፤ ቡድኑም ጠንክሮ ይሰራል፡፡ ማስሎቭም በሌቫኖቭስኪ ብቃት ደስተኛ ይመስል ነበር፡፡” በማለት ጽፏል ጋሊንስኪ፡፡ ጋዜጠኛው የሽኩቻ ተረኩን ይቀጥላል፡፡ ” የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ጨርሰው ወደ ሃገራቸው እየበረሩ ሳሉ በከባድ የአየር ሁኔታ ሳቢያ ዳይናሞዎች የተሳፈሩበት አውሮፕላን በሲምፌሮፖል እንዲያርፍ ተገደደ፡፡ የድጋሚ በረራ መነሻቸውም ጥቂት ዘግየት እንዲል ተወሰነ፡፡ ሰዓቱ እስኪደርስ ማስሎቭ ቡድኑ ምሳ እንዲመገብ አዘዘ፡፡ ተጫዋቾቹን ያስገረመ ሌላ ነገርም ነገራቸው፡፡ ሆሪልካ ከተሰኘው የዩክሬይን ተወዳጅ ዊስኪ አንዳንድ ብርጭቆ እንዲጎነጩ ፈቀደላቸው፡፡ ተጫዋቾቹ ጆሯቸውን ማመን ተሳናቸው፤ በዳይናሞ ክለብ ታሪክ እንዲህ አይነት ነጻነት ታይቶ አይታወቅም፡፡ ማስሎቭ ለቀጣዩ የውድድር ዘመን መልካም ምኞቱን ለመግለጽ ጽዋውን አነሳ፡፡ ሁሉም ጽዋቸውን በአንድነት ሲቀምሱ ሌቫኖቭስኪ ግን ጭራሹኑ ብርጭቆውን እንኳ አልነካም ነበር፡፡ ማስሎቭ ይህን ሲያይ ለቡድኑ ውጤታማ ጉዞ ሲል ሌቫኖቭስኪ ጥቂት ከውስኪው ፉት እንዲል ለመነው፡፡ ተጫዋቹ ግን በአቋሙ ጸንቶ በድጋሚ ‘እምቢኝ!’ አለው፡፡ ይሄኔ ማስሎቭ ሌቫኖቭስኪ ላይ የእርግማን መዓት አወረደበት፡፡ ተጫዋቹ የዋዛ አልነበረምና እርሱም መልሶ አሰልጣኙን ተራገመ፡፡” ይላል ጋሊንስኪ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በሁለቱ ሰዎች መካከል መጥፎ ጥላቻ ተጸነሰ፡፡
ካኔቭስኪ ግን ጋሊንስኪ ሁኔታውን በጣም እንዳጋነነው ይገልጻል፡፡ እርሱ በምሳው ፕሮግራም ላይ ተገኝቷል፡፡ የሆሪልካ ዊስኪ እንደቀረበም ያስታውሳል፤ በቀላሉ ከማይደሰተው ሌቫኖቭስኪ ውጪ የነበሩት ሁሉም ጽዋውን መቋደሳቸውንም አይዘነጋም፡፡ የሌቫኖቭስኪ ጥብቅ ሥርዓት አክባሪነት የታወቀ ነበር፡፡ ይህን ማስሎቭም አያጣውም፤ እንዲያውም በዚህ ባህርዩ ዘወትር እንደተደነቀ ነው፡፡ ተጫዋቹ ከዊስኪው ላለመጎንጨት ራሱን በማቀቡ አሰልጣኙ እምብዛም አልከፋውም፡፡ ” ማስሎቭ ሌቫኖብስኪን ምንም አልተናገረውም፤ አንዳችም የስድብ ቃል ከአንደበቱ እንዳልወጣ እርግጠኛ ሆኜ እናገራለሁ፡፡” ይላል ካኔቭስኪ፡፡
ሌሎች ወገኖች ደግሞ የሁለቱ ግለሰቦች ግንኙነት መሰናክል የገጠመው ሚያዝያ 27-1964 ኪዬቮች በሞስኮ ከስፓርታክ ጋር በነበራቸው ጨዋታ ላይ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ በፍልሚያው ሌቫኖቭስኪ ግብ አስቆጥሮ ክለቡን መሪ ያደርጋል፤ እርሱ ተቀይሮ ሜዳውን እስኪለቅ ዴረስም ኪዬቮች 1-0 ይመሩ ነበር፡፡ ሌቫኖቭስኪ ጨዋታ ሊጠናቀቅ ሃያ ደቂቃ ሲቀር ተቀየረ፤ ይህ በእግርኳስ ተጫዋችነት ጊዜው የመጀመሪያው ነው፡፡ በመጨረሻም ስፓርታኮች ጎል አገቡና ግጥሚያው በአቻ ውጤት ተጠናቀቀ፡፡ ቪክቶር ማስሎቭ ከስፓርታኩ አሰልጣኝ ኒኪታ ሲሞንያን ጋር በመነጋገር የጨዋታው ውጤት ይህ እንዲሆን ቀድም ብሎ መስማማቱ በጭምጭምታ ይወራል፡፡ ሌቫኖቭስኪ እንዲቀየር የተደረገውም በስምምነቱ መሠረት ከአሰልጣኞቹ እቅድ ጋር ለመሄድ ሜዳ ላይ ፈቃደኛ ሆኖ ባለመገኘቱ ነው፡፡ እውነት ይሁን ውሸት ባይረጋገጥም ዳይናሞ ኪዬቮች በዩጎዝላቭ ከሜዳቸው ውጪ በሺኒክ የሚያደርጉት ጨዋታ ለሌቫኖቭስኪ በክለቡ ቆይታው የመጨረሻው ሆነ፡፡
ሌሎች አካላት ደግሞ የማስሎቭና ሌባኖቭስኪን ጉዳይ በባህርይ ካለመግባባት ጋር አያያይዙትም፡፡
ማስሎቭ በ1971 ወደ ቶርፒዶ ሲመለስ ሚኻይል ጌርሽኮቪች፣ ዴቪድ ፔይስና ግሪጎሪ ያኔትስ የክለቡ አንጋፋ ተጫዋቾች የነበሩ ቢሆንም አሰልጣኙ እነርሱ ላይም ፊቱን ከማዞር ወደኋላ አላለም፡፡ ኮከቦቹ ተጫዋቾች ገሸሽ ለመደረጋቸው በማስሎቭ የአጨዋወት ሥልት ውስጥ ብቁ ሆነው መገኘት ባለመቻላቸው እንጂ ሌላ ምንም የተለየ ምክንያት ኖሮ አልነበረም፡፡ ጋሊንስኪ ምንም ይበል ምን በማስሎቭ እቅድ ውስጥ ሌባኖቭስኪ ለምን ሊካተት እንደማይችል መረዳት ቀላል ይመስላል፡፡ ተጫዋቹ በሞስኮ ጋዜጦች “ገመድ” የሚል ቅጽል ስም የተሰጠው በጨዋታ ወቅት ኳስን ከእግሩ ጫማ ክር ጋር ያስተሳሰራት ይመስል ለረዥም ጊዜ ይዞ ስለሚቆይ ነበር፡፡ ሌባኖቭስኪ እውነተኛ ኮከብ፣ ባለ ተሰጥኦና በተመልካች ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነት ማትረፍ የቻለ ተጫዋች ነበር፡፡ በ2002 ህይወቱ ስታልፍ በርካታ ደጋፊዎች በሃዘን መግለጫ መልዕክቶቻቸው በ1960ዎቹ መነሻ ዓመታት የዳይናሞን ጨዋታ ለመታደም ወደ ስታዲየም ሲያቀኑ እርሱ በቄንጠኛ ዘይቤ የማዕዘን ምቶችን በተጋጣሚ ሳጥን ክልል ውስጥ ቁልቁል ሲያሳርፍ ማየት ደስታቸው እንደነበር አውስተዋል፡፡ ጥቂት ዓመታት ወደኋላ ስንመለስ ብራዚላዊው ዲዲ የደረቀ ቅጠል በአየር ላይ የሚያደርገውን ጉዞ የሚመስል የቆመ ኳስ አመታት ዘይቤ ነበረው፡፡ ሌባኖቭስኪም በተመሳሳይ የራሱ የሆነ የቅጣት ምት ዘዴ ፈጥሮ ይህንኑ ይተገብር ነበር፡፡ በዚህ ቴክኒኩ ብዙዎችን ሲያስደምም ኖሯል፡፡ ከማስሎቭ ጋር የተፈጠረው ትልቁ ችግር ሌባኖቭስኪ የግራ መስመር አማካይ (Left Winger) መሆኑ ነው፡፡ የመስመር አማካዮች (Wingers) ደግሞ በማስሎቭ የጨዋታ እቅድ ውስጥ ቦታ የላቸውም፡፡
” በማስሎቭና ሌባኖቭስኪ መካከል የተፈጠረውን ኹነት ግጭት ልለው እቸገራለሁ፡፡” ቢባ ያብራራል፡፡
” ቫለሪ ሁሌም የማስሎቭን አቅጣጫዎች ይቃወም ነበር፡፡ ማስሎቭ አዳዲስ የአጨዋወት ዘይቤዎችን ይፈልጋል፤ እንግዳ ከሆኑ የእግርኳስ አቀራረብ ሥልቶች ጋር በቶሎ የሚላመዱ ተጫዋቾችንም ይሻል፡፡ ኳስ እግራቸው ሥር የሚያቆዩት ደግሞ ለእርሱ የጨዋታ ሥርዓት አይመቹም፡፡ አየር ላይ የደጋን ቅርጽ እየሰራ የሚሄድ የምት አይነትን (Banana Shot) ያመጣው ሌባኖቭስኪ እንኳ ሊያሳምነው አልቻለም፡፡ ይህ ሁሉ ነገር ለቫለሪ ቆይቶ ተገልጦለታል፡፡ አሰልጣኝ ከሆነ በኋላም “ተጫዋቹ ሌባኖቭስኪ” በ<አሰልጣኙ ሌባኖቭስኪ> ቡድን ውስጥ የመጫወት ዕድል እንደማያገኝ ተረድቷል፡፡ ” ሚኻይል ያኩሺን ከስታንሊ ማቲውስ አይነት የተናጠል የተጫዋቾች ብቃት በበለጠ የቡድን ሥራን በመምረጥ ያነሳውን አሳማኝ መከራከሪያ ወደ ተራቀቀ አመክንዮ ወስዶታል፡፡ ተጫዋቾች ምንም ያህል ባለ ክህሎት ይሁኑ በቡድን ስራ ላይ የሚያደርጉት አበርክቶ “እዚህ ግባ” የማይባል ከሆነ ተፈላጊ አይሆኑም፡፡” ይላል ቢባ፡፡
ይህ ማለት ግን ማስሎቭ ሙሉ በሙሉ ከታላላቅ ተጫዋቾችን ጋር መሥራት አይፈልግም ማለት አይደለም፡፡ እንዲያውም በተጻራሪው ዩክሬይን ካፈራቻቸው ተጫዋቾች ቢባ እጅግ ባለ ተሰጥኦው አማካይ ነበር፡፡ አልፍ ራምሴይ ቦቢ ቻርልተንን በእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን ሲያሰልፈው በነበረው ቦታ ቢባም በማስሎቭ የአጨዋወት ዘዴ ውስጥ በተመሳሳይ ሚና ጉልህ ድርሻ ነበረው፡፡
ሶቭየት ህብረት የ1956ቱን ኦሎምፒክ ስታሸንፍ የቡድኑ አባል የነበረውና ኋላም ላይ የተከበረ አሰልጣኝ ለመሆን የበቃው ሎዚፍ ቤዛ ” ቢባ ልክ ኳሷን እንዳገኘ የቡድን አጋሮቹም ሆኑ የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች ምን ሊከውኑ እንደሚችሉ ቀድሞ ይረዳል፡፡ እርሱ ለቀጣይ እርምጃዎቹ ዕቅድ ያዘጋጃል፡፡ የተሳካ ቅብብል ለማድረግ ሲል በመጀመሪያ ንክኪው ኳሷን አመቺ ቦታ ላይ ያስቀምጣታል፡፡ የተጋጣሚ ተጫዋቾች ሃሳቡን ከተረዱበት በፍጥነት የማጥቃት አቅጣጫውን ይቀይረዋል፡፡ ቢባ ኢላማውን የጠበቀ ረዣዥም ቅብብሎች የመከወን ብቃትም ነበረው፡፡ በትክክለኛው ሰዓት ትክክለኛው ቦታ ላይ በመገኘትም በጥሩ አጨራረስ የማጥቃት ሒደቱን
ያሳምራል፡፡” ይላል ስለ ቢባ ምስክርነቱን ሲሰጥ፡፡
በ1965 አንድሪይ ቢባ የብቃቱ ጫፍ ላይ ደረሰ፡፡ በዚሁ ዓመት የጸደይ ወቅት ከዳይናሞ ሞስኮ ጋር ሲጫወቱ ከ36 ሜትር ርቀት ባስቆጠራት ግብ የተነሳ “የሌቭ ያሺን”ን የምርጥ ግብ ሽልማትም መውሰድ ችሏል፡፡ ክረምቱ አባርቶ ወደ በጋ መሸጋገሪያ ወቅት ኪዬቮች ሲ.ኤስ.ኬ.ኤ ሞስኮው ላይ በተቀዳጁት የ4-0 ድል ቢባ ሁለቱን ጎሎች ከማስቆጠሩም በላይ በጨዋታው አስገራሚ ብቃት አሳየ፡፡ ዳይናሞ ኪዬቭ በአመቱ መጨረሻ የጥምር ዋንጫ ባለቤት የሆነበትን ድል ማሳካቱን ባረጋገጠበት የጥሎ ማለፉ ፍጻሜ ከቶርፒዶ ጋር በተደረገው ጨዋታ ወሳኟን የማሸነፊያ ግብ ማግባት ችሏል፡፡ ቢባ የቡድኑ ዋነኛ የፈጠራ ምንጭ ነበር፡፡ ያን ዓመት ሁሉንም ባስማማ ምርጫ የክለቡ የዓመቱ ኮከብ ተብሎ ተመርጧል፡፡
ይቀጥላል...
ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡ ባለፉት አስራ ሦስት ዓመታትም አስር መፅሐፍትን ለህትመት አብቅቷል፡፡