ሲዳማ ቡና ከነገ ጀምሮ ወደ ልምምድ ይመለሳል

ሲዳማ ቡናዎች ከነገ (ማክሰኞ) ወደ ልምምድ ይመለሳሉ፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እና ሌሎች ውድድሮች ዓለማችንን እያሰጋ ባለው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት ከተቋረጠ ሳምንታት አልፈዋል፡፡ ውድድሩም ሙሉ በሙሉ በመቆሙ ምክንያት ክለቦች ልምምዳቸውን ካቆሙም በተመሳሳይ መልኩ ረዘም ያለ ጊዜን አስቆጥሯል፡፡ ምንም እንኳን ሊጉ መቼ እንደሚጀመር ባይታወቅም ክለቦች ወደ ልምምድ እየተመለሱ ይገኛል፡፡ ከዚህ ቀደም መቐለ 70 እንደርታ ወደ ልምምድ መመለሱን የገለፀ ሲሆን አሁን ደግሞ ሲዳማ ቡና ከነገ ማክሰኞ ጠዋት 12:00 ጀምሮ ወደ ልምምድ እንደሚመለስ አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡

አሰልጣኝ ዘርዓይ እንደገለፁት ከሆነ ሁሉንም የቡድኑን አባላት ያሳተፈ የቴሌግራም ግሩፕ የተከፈተ ሲሆን ነገ ማለዳም ሁሉም ተጫዋቾች ተመሳሳይ መለያን በመልበስ በያሉበት ቦታ ሆነው የሚላክላቸውን የፅሁፍ እና የቪዲዮ የልምምድ መመሪያ በዕኩል ሰዓት መስራት ይጀምራሉ ብለዋል፡፡ ተጫዋቾቹ ልምምዱን ካጠናቀቁ በኃላ በፎቶ እና በቪዲዮ ምስል ልምምዳቸውን በአግባቡ ተግባራዊ ማድረጋቸውን ለማረጋገጥ እያንዳንዳቸው በተከፈተው የቴሌግራም ግሩፕ ቪዲዮዋቸውን ይልካሉም ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ነገ ልምምድ ከጀመሩ በኃላ በየሳምንቱ እቅድ እና ፕላን እየተገመገመ እንደሚላክላቸው የተገለፀ ሲሆን ከልምምድ መርሀ ግብሩ ባሻገር ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህር ጋር በመተባበር ከስነልቡና ጉዳዮች ጋር ያሉትን ትምህርቶች በቪዲዮ ለሁሉም የቡድኑ አባላት ይላክላቸዋልም ብለዋል፡፡

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ