በአዲሱ የኢትዮጵያ ሚሌኒየም በእግርኳሱ ብቅ ካሉ ጥሩ አጥቂዎች መካከል አንዱ የሆነው ሙሉዓለም ጥላሁን የት ይገኛል ?
ቀልድ አዋቂ ነው ይሉታል። ትውልድና ዕድገቱ አዲስ አበባ መርካቶ በልዩ ስሙ ጭድ ተራ በሚባል አካባቢ ነው። በሰፈር የጀመረው የእግርኳስ ህይወቱ ለአዲስ አበባ ከ15 እና ከ17 ዓመት በታች ምርጥ ቡድን ውስጥ ተመርጦ ባሳየው ድንቅ ብቃቱ በአሰልጣኝ ያሬድ ቶሌራ (ድሬ) አማካኝነት ዘጠናዎቹ መጨረሻ ላይ ኢትዮጵያ መድንን ተቀላቅሎ መጫወት ችሏል። በመድን ካሳየው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ በኋላ ድንቅ የውድድር ጊዜ ወደሳለፈበት ኢትዮጵያ ቡና አምርቶ በተለይ በ2003 ኢትዮጵያ ቡና ፕሪምየር ሊጉ በአዲስ መልክ ከተጀመረ ወዲህ የመጀመርያውን ዋንጫ ሲያነሳ ትልቁን ሚና ከተወጡ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነበር። በኋላም በመከላከያ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ወልዋሎ ዓዲግራት ክለቦች እስከ 2010 ድረስ መጫወት ችሏል። ያለፉት 18 ወራትን ከሜዳ የራቀው ይህ አጥቂ እግርኳስ አቆምክ? ወይስ በምን ሁኔታ ላይ ትገኛለህ? ስንል ጠይቀነው ተከታዩን ምላሽ ሰጥቶናል።
“እግርኳስን አላቆምኩም። ለማቆምም ጊዜው አይደለም። የመጫወት አቅሙ አለኝ የ። እድሜም ገና ነው። አሁን የምገኘው ከባለቤቴ እና ከልጆቼ ጋር ጀርመን ሀገር ነው። ከሜዳ የራቅኹባቸው የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም በቀጣይ ነገሮች ሲስተካከሉ ወደ እግርኳሱ በቅርቡ እመለሳለው። ጎን ለጎን ከጀርመን ሀገር የተለያዩ ትጥቆችን በማምጣት በሀገሬ የንግድ ሱቅ በመክፈት እየተንቀሳቀስኩ እገኛለው።” ብሏል።
ሶከር ኢትዮዽያ ከሙሉዓለም ጥላሁን ጋር አጠቃለይ የእግርኳስ ህይወቱ ዙርያ ሰፊ ቃለ መጠይቅ ያደረገች መሆኗን እየገለፅን በቅርቡ ለንባብ የምናቀርብ መሆኑን ከወዲሁ እንጠቁማለን።
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ