ሁለቱ በኢትዮጵያ ቡና ይጫወታሉ። አንደኛው ወንድማቸው ደግሞ በአንደኛ ሊግ እየተጫወተ ይገኛል። በአንድ ቤተሰብ ውስጥ የሚገኙ እነዚህ ሦስት ተጫዋቾች በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የቤት ውስጥ ውሏቸው ምን እንደሚመስል ልንቃኝ ወደድን።
የእግርኳስ ዘመናቸው ጥቂት ዓመት ቢሆንም አቡበከር ናስር፣ ሬድዋን ናስር (ኢትዮጵያ ቡና) እና ጅብሪል ናስር (ጉለሌ ክ/ከተማ) በተለያዩ ክለቦች ስኬታማ ጊዜን እያሳለፉ ይገኛሉ። በተለይ አቡበከር ናስር በሁሉም የዕድሜ ዕርከን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከተጫወቱ ጥቂት ተጫዋቾች መካከል አንዱ መሆን የቻለ ሲሆን አሁን በኢትዮጵያ ቡና መልካም ቆይታ ማድረግ ላይ ይገኛል። ታናሽየው ሬድዋን ናስር ዓምና በኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ከዋናው ቡድን ጋር እየተመላለሰ አዲስ አበባ ከተማ ታዳጊ ቡድን ጋር የሊጉን ዋንጫ አንስቷል። በታዳጊ ብሔራዊ ቡድን መጫወት የቻለው ሬድዋን በዘንድሮ ዓመት በኢትዮጵያ ቡና ተቀይሮ በመግባት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል። ታላቅ ወንድማቸው ጅብሪል ናስር ምንም እንኳ እንደ ታናሽ ወንድሞቹ ወጥ የሆነ የእግርኳስ ህይወት አያሳልፍ እንጂ በ2008 ባቱ ላይ በተካሄደው የአንደኛ ሊግ ማጠቃለያ ውድድር ወቅት ኮከብ ተጫዋች በመሆን መመረጥ ችሏል። በአሁኑ ጊዜ ከተለያዩ ክለቦች ቆይታ በኃላ ለጉለሌ ክ/ከተማ እየተጫወተ ይገኛል።
በኮሮና ቫይረስ ወርሺኝ ምክንያት ውድድሮች መቋረጣቸውን ተከትሎ ሦስቱም ወንድማማቾች በአንድ ላይ በመሆን አብረው ጊዜያቸውን እያሳለፉ ይገኛሉ። ይህን ተከትሎ ለአቡበከር ናስር ስለ ውሏቸው አጭር ጥያቄ አቅርበንለት እንዲህ መልሶልናል።
” እንደ አጋጣሚ ሆኖ ከቤታችን አጠገብ ጉቶ ሜዳ አለ። እዛ በመሄድ ሦስታችንም አብረን በመሆን ከኳስ ጋር ልምምድ እየሰራን እንገኛለን። ከልምምድ ውጭ ያለንን ጊዜ ቤታችን በመቀመጥ አብረን እናሳልፋለን። አሁን የረመዳን ፆም በመግባቱ የበለጠ ጊዜያችንን በሃይማኖታዊ አምልኮ እንድናሳልፍ ይረዳናል። ውድድሩ በመቋረጡ በዓለም የመጣ መሆኑን ተረድተን የምንቀበለው ቢሆንም እኔም ወንድሜም በኢትዮጵያ ቡና ጥሩ ጊዜ እያሳለፍን እንገኝ ነበር። በተለይ እኔ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በጥሩ ጊዜ ለማገልገል የተነሳሳሁበት ወቅት ላይ ይህ ነገር መፈጠሩ ቢያስቆጨኝም። ነገ የተሻለ ጊዜ መጥቶ የምወደውን ክለቤንም ሆነ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን የማገለግል ይሆናል። በመጨረሻ እንኳን ለ1,441ኛው የተቀደሰው የረመዳን ጾም በሠላም አደረሳችሁ፤ የወቅቱ ፈተና የሚያልፍበት፤ መልካም ወር እንዲሆን ከልብ እመኛለው።”
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ