29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ትውስታ በሲሳይ ባንጫ አንደበት

ከ31 ዓመታት በኃላ ኢትዮጵያ በ2013 የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ተሳታፊ በሆነችበት ወቅት በቀይ ካርድ ከሜዳ ስለወጣበት እና ፈገግ ስለሚያሰኘው አጋጣሚ ግብጠባቂው ሲሳይ ባንጫ ይናገራል።

በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በተመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ29ኛው የደቡብ አፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎው በምድብ ጨዋታ ሦስቱንም ግብ ጠባቂዎችን አፈራርቆ ተጠቅሟል። በመጀመርያው (ከዛምቢያ 1-1) ጀማል ጣሳው ቀይ ካርድ በመመልከቱ በሁለተኛው ጨዋታ (በቡርኪናፋሶ 0-4) ዘሪሁን ታደለን የተጠቀመው ብሔራዊ ቡድኑ በመጨረሻው የምድብ ጨዋታ (በናይጄርያ 0-2)  የዛሬው እንግዳችን ሲሳይ ባንጫን ማጫወት ችሏል። ሆኖም ሲሳይ በተሰለፈበት የመጨረሻ ጨዋታ በ85ኛው ደቂቃ በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል። በዚህ ወቅት በተፈጠረው አስገራሚ ገጠመኝ ዙርያ ሲሳይ ባንጫ ለትውስታ ይሄን ይናገራል።

” ወቅቱ በእግርኳስ ዘመኔ የማልረሳው ምርጡ ጊዜ ነው። ለአፍሪካ ዋንጫ እና ለቻን ውድድር ያለፍንበት፤ ለዓለም ዋንጫም ቢሆን የመጨረሻው ምዕራፍ ደርሰን የነበረበት የማይረሳ አንድነት፣ ህብረት ያለው ጠንካራ ስብስብ ነው። በወቅቱ የቡድኑ ሦስተኛ ግብጠባቂ ነበርኩ። ጀማል ጣሳው በመጀመርያ ጨዋታ በቀይ ካርድ በመውጣቱ በሁለተኛው ጨዋታ ዘሪሁን ታደለ ገብቶ አራት ጎል በማስተናገዱ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በመጨረሻው ጨዋታ ከናይጄርያ ጨዋታ ላይ ለመሰለፍ ችያለው። በወቅቱ የማስታውሰው ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረግን የነበረ ቢሆንም ዳኛው በጣም ይጫነን ነበር ። ያው ቪክተር ሞሰስ ብቻውን ስላገኘሁት ለማስቆም ወስኜ ጥፋት ሰርቼበት ፍፁም ቅጣት ምት ሊያገኙ ችለዋል። ዳኛው በእኛ ላይ በተደጋጋሚ በሚያደርገው በደል ተበሳጭቼ ደጉ ደበበን ይህን ሰውዬ አንድ ነገር በለው ብዬ በራሳችን ቋንቋ ስናገረው ዳኛው በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ አስወጥቶኛል።

ግን አንዳንድ የቡድን አባላት ከጨዋታው በኃላ ሲናገሩ “ዳኛው በማይሰማው ቋንቋ ተሳድቦ በቀይ ካርድ የወጣ ተጫዋች” በማለት ፈገግ የሚያደርግ ቀልድ ይቀልዳሉ። ለዚህ ያለህ ምላሽ ?

(በጣም እየሳቀ)… አዎ እሰማለው። ያው እነርሱ በወቅቱ ሲቀልዱ ለጨዋታ ያህል ይሄን ይናገራሉ። የሆነው ግን በወቅቱ ቅድም እንዳልኩሁ በዳኛው አንዳንድ አላስፈላጊ ውሳኔዎች ተበሳጭቼ ለደጉ ነው በእኛ ቋንቋ ንገረው ባክህ ብዬ በአካላዊ እንቅስቃሴ እየጮውኩኝ ያወራሁት። ዳኛው ምን እንደገባው አላውቅም በቀይ ካርድ አስወጥቶኛል። ምን አልባት እየተወራጨሁ እያወራሁ ስለነበር ለዛ ይመስለኛል በቀይ ካርድ ልወጣ የቻልኩት። በጊዜው ቀይ ካርድ የተመለከትኩበት ደቂቃ የጨዋታው መጨረሻ ላይ ስለነበር አዲስ ህንፃ በቀሪው ደቂቃ ግብጠባቂ በመሆን መጫወት ችሏል።

በመጨረሻም ማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት እጅግ አስከፊ የሆነ የኮሮና ቫይረስ ወርሽኝ በዓለም እና በሀገራችን ተከስቷል በጎ ጊዜ እስኪመጣ ሁላችንም በቤታችን እንቀመጥ የጤና ባለሙያ ምክር እንስማ እላለው።

በሀዋሳ ከተማ የተወለደው ሲሳይ ባንጫ ሲዳማ ቡና ከታችኛው ሊግ (የወቅቱ ብሔራዊ ሊግ) ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እንዲገባ ካስቻሉ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው። በ2003 ለመጀመርያ ጊዜ በተከናወነው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ግብጠባቂ ሽልማት ላይ ተሸላሚ መሆን ችሏል። በደደቢት በቆየባቸው ሦስት ዓመታት በ2005 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ፣ በ2006 የኢትዮጵያ ዋንጫን ማንሳት ችሏል። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በተለያዩ ዓመታት ጥሪ ቀርቦለት መጫወት የቻለ አንጋፋ ግብጠባቂ ነው። በክለብ ደረጃ ከደደቢት በመቀጠል በወልዲያ፣ አዳማ ከተማ፣ ጅማ አባ ቡና እና አርባምንጭ ከተማ የተጫወተ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ሊግ ለሻሸመኔ ከተማ እየተጫወተ ይገኛል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ