ከኳስ አቀባይነት እስከ ብሔራዊ ቡድን – ሙሉዓለም ጥላሁን

በአዲሱ የኢትዮጵያ ሚሌኒየም በእግርኳሱ ብቅ ካሉ ጥሩ አጥቂዎች መካከል አንዱ ነው። በመድን ተስፋ ሰጪ አጀማመር አድርጎ በ2003 ኢትዮጵያ ቡና ፕሪምየር ሊጉ በአዲስ መልክ ከተጀመረ ወዲህ የመጀመርያውን ዋንጫ ሲያነሳ ትልቁን ሚና ከተወጡ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነበር። በኋላም በመከላከያ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ክለቦች እስከ 2010 ድረስ መጫወት ችሏል። በአጠቃላይ በእግርኳስ ህይወቱ ዙርያ ከሙሉዓለም ጥላሁን ጋር ያደረግነውን ሰፊ ቆይታ እንዲህ አቅርበነዋል።

ትውልድ እና ዕድገትህ የት ነው ?

ተወልጄ ያደኩት አዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ “ጭድ ተራ” በሚባለው አካባቢ ነው። እንደምታውቀው የተወለድኩበት አካባቢ የንግድ እንቅስቃሴ በስፋት የሚካሄድበት ነው። የዛኑ ያህል ደግሞ እግርኳስን በልዩ ሁኔታ የሚወድ ማኅበረሰብ ያለበት አካባቢ ነው። እግርኳስን እንደማንኛውም ኳስ ተጫዋች እየተጫወትኩ ያደግኩት በዚሁ ሠፈር ነው።

ለቤተሰብህ ስንተኛ ልጅ ነህ? እግርኳስን ተጫውቶ ያሳፈ ቤተሰብስ አለህ?

ለቤተሰቤ አምስተኛ ልጅ ነኝ፤ አጠቃላይ ስድስት የቤተሰብ አባል አለን፣ አባቴ አሁን በህይወት የለም ነፍሱን ይማረው። ከቤተሰባችን ውስጥ እግርኳስን ተጫውቶ ያለፈ አንድም ተጫዋች የለም ከእኔ በቀር። ያም ቢሆን ሁሉም የቤተሰቤ አባላት ለእግርኳስ ልዩ ፍቅር ያላቸው በመሆናቸው እኔ በእግርኳሱ ትልቅ ደረጃ እንድደርስ አስተዋፅኦ አድርገውልኛል።

ታዲያ ምድነው ኳስ ተጫዋች እንድትሆን ያነሳሳህ ?

ብዙ ምክንያቶች አሉኝ። የመጀመርያው አባቴ መምህር በመሆኑ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ኳስ እየተጫወትኩ ማደጌ በጣም ጠቅሞኛል። ከምንም በላይ ግን ፕሮጀክት እያለው በአዲስ አበባ ስታዲየም ኳስ የማቀበል አጋጣሚ ተፈጥሮልኝ ስለነበረ ተጫዋቾች ሜዳ ላይ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እየተመለከትኩ ማደጌ እና ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በአካል የተለያዩ ተጫዋቾችን የማገኛቸው በመሆኑ እንዲሁም እነርሱ የሚመክሩኝ ምክር እግርኳስ ተጫዋች እንድሆን ትልቅ መነሳሳት ፈጥሮልኛል።

አስገራሚ ገጠመኝ ነው አንተ ኳስ በምትመለከትበት ወቅት በጣም ዓይን ውስጥ ይገቡ ታደንቃቸው የነበሩ ተጫዋቾች ካሉ ብታጫውተኝ አሪፍ ነው?

በወቅቱ በሻምበል መላኩ አብርሃ ፕሮጀክት ውስጥ ታቅፌ እሰለጥን ነበር። ኳስ አቀባይ በመሆናችን ምንም ክፍያ የለውም በፍቅር ነበር የምንሰራው። ታዳጊዎች ኳስን እየተመለከቱ ኳስን ቢያቀብሉ ለነገ ህይወታቸው መነሳሳትን ይፈጥርላቸዋል ተብሎ በወቅቱ የስፖርት አመራሮች ስለታመነበት እየተመረጥን እንላክ ነበር። አስበው በዚያ ዕድሜዬ አዲስ አበባ ስቴዲየም በነፃ መግባት እጅግ ትልቅ አጋጣሚ ነው። ይህን አጋጣሚ በማግኘቴ በጣም ደሰተኛ እሆን ነበር። ጊዜው ዘጠናዎቹ አጋማሽ አካባቢ ስለነበር ኮከብ የነበሩት እንደነ ዮርዳኖስ ዐባይ ፣ አሸናፊ ግርማ የመሰሉ ምርጥ ተጫዋቾችን እመለከት ነበር።

በአዲስ አበባ ምርጥ የታዳጊ ፕሮጀክት ውድድር ላይ ጥሩ አቅምህን በማሳየትህ የእግርኳስ ህይወትህን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ቀይሮታል ትላለህ?

በሚገባ! ቅድም እንዳልኩሁ በሠፈር የጀመረው እግርኳስ መጫወት በኋላም በትምህርት ቤት ቀጥሎ (አሁን በኢንስትራክተር ሆኗል) አለባቸው እንዲሁም ሻምበል መላኩ አብርሃ ጋር በፕሮጀክት ሰልጥኛለው። አዲስ አበባን በመወከል ለተከታታይ ሁለት ዓመታት ከ15 እና ከ17 ዓመት በታች የፕሮጀክት ውድድር መሳተፍ ችያለው። ድሬዳዋ ላይ በተካሄደው ከ17 ዓመት በታች ውድድር ላይ ባሳየሁት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ እኔም ሆንኩ በሙሉ የቡድኑ አባላት አሰልጣኝ ያሬድ ቶሌራ (ድሬ) ጨምሮ ከድሬዳዋ እንደተመለስን በ1997 ኢትዮጵያ መድን ሊወስደን ችሏል። ይህም በክለብ ደረጃ በታዳጊ ቡድን ታቅፌ ነገ የማስበውን ትልቅ ተጫዋች የመሆን ህልም ጉዞን ጀምሬያለው።

በኢትዮጵያ መድን ምን ያህል ጊዜ ቆየህ ?

ሦስት ዓመት በታዳጊ ቡድን ቆይቼ በ2000 ወደ ዋናው ቡድን ማደግ ችያለው። በነገራችን ላይ ወደ ዋናው ቡድን እንዳድግ የአንጋፋው አሰልጣኝ ሥዩም አባተ አስተዋፆኦ የላቀ ነበር። በእርሱም የተወሰኑ ጊዜያት የመሰልጠን እድል አግኝቻለው። ለተከታታይ ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያ መድንን በዋናው ቡድን አገልግዬ በመቀጠል ነበር ብዙ እውቅና ወዳገኘሁበት ኢትዮጵያ ቡና በ2003 መቀላቀል የቻልኩት።

ኢትዮጵያ ቡና ስለነበረህ ቆይታ እመለስበታለሁ። ግን ለአንተ እግርኳስ ህይወት መነሻ የሆነህ በኢትዮጵያ እግርኳስ በርካታ ትውልድ ያፈራው ታሪካዊ ክለብ ኢትዮጵያ መድን በዚህ ወቅት ወደ ፕሪምየር ሊግ መመለስ አቅቶት ሲቸገር ስታይ እንደ አሳዳጊ ክለብ ምን ይሰማሀል?

በጣም ነው ቁጭት የሚፈጥርብኝ። ይህ የሆነው ብዬ የማስበው ከአመራሩ ድክመት የመነጨ እና የከነማ ቡድኖች እየበዙ መምጣት፤ በተጨማሪም የድርጅት ክለቦች የመውረድ እና የመፍረስ አደጋ ውስጥ መግባት ችለዋል። የከተማ ቡድኖች መጠናከር እና ተፅዕኖ መፍጠር ምን አልባት መድን እንዳይመጣ ያደረገ ሳይሆን አይቀርም። ያም ቢሆን እንደ አሳዳጊ ክለብ አሁን ያለበትን ደረጃ ስመለከት አዝናለው እቆጫለው። እዚህም በጀርመን የሚኖሩ የቀድሞ የመድን ስመ ጥር ተጫዋቾች አሉ ዳንኤል አስገዶም እና ሙሉጌታ የሚባሉ ከእነርሱ ጋር ቁጭ ብለን ሻይ ቡና በምንባባልበት ወቅት ይህን ጉዳይ አንስተን በፀፀት እናወራለን። ይህ ታላቅ ክለብ እንዲህ መሆኑ ያሳስበናል።

በጣም ጎልተህ የወጣህበት እና ታዋቂነትን ያገኘህበት የኢትዮጵያ ቡና ቆይታህን አጫውተኝ?

በጣም ዕድለኛ ነኝ ማለት ይቻላል። ኢትዮጵያ ቡናን በተቀላቀልኩበት ዓመት የፕሪምየር ሊጉን በማንሳት በደጋፊዎች ዘንድ የማይረሳውን ታሪካዊ ማሳካት ችያለው። በተጨማሪም የኢትዮጵያ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን አንስቻለው። ይህ ስኬት የመጣው ሁላችንም በወቅቱ እንደ ቡድን በጋራ በመንቀሳቀሳችን ነው። በግሌም ቢሆን በውድድር ዓመቱ ለራሴ እስከዛሬ በአንድ የውድድር ዓመት ያላስቆጠርኩትን 13 ጎሎች አስቆጥሬያለው፣ ብዙ ፍፁም ቅጣት ምቶችን አስገኝቻለው እንዲሁም ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቼ አቀብያለው። በእግርኳስ ህይወቴ ስኬታማ የሆነ ዓመት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር አሳልፌለው። በእግርኳሱ ቤተሰብ እንድታወቅ ሆኛለው። ኢትዮጵያ ቡናን ከልጅነቴ ጀምሮ የምወደው ስቴዲየም በመሄድ ጭምር ስደግፈው የነበረ ቡድን በመሆኑ ይህን ማልያ አድርጌ ዋንጫ በማንሳት ታሪክ በመስራቴ እስካሁን ድረስ የሚሰማኝ ደስታ ወደር የለውም።

ከዋንጫ ድሉ በኋላ በኢትዮጵያ ቡና የነበረህ ቆይታ በፈተና የተሞላ ነበር። እስኪ ስለ እርሱም አጫውተኝ?

በኢትዮጵያ ቡና እስከ 2005 ድረስ መቆየት ችያለው። በቆየሁባቸው ዓመታት በጣም ደስተኛ ነበርኩ። የቤቴ ያህል ይሰማኝ ነበር። በኢትዮጵያ ቡና የሰራሁት ነገር በጣም አሪፍ ነው። ሁሌም ሳስታውሰው የምኖረው ከልቤ የማይጠፋ የቤተሰቤም አካል የሆነ ትልቅ ክለብ ነው። ሆኖም የተወሰኑ ደጋፊዎች ሆን ብለው እኔን ለማጥቃት የተደረገብኝ ሴራ እንደ ነበረ ከወጣሁ በኋላ ነው ያወቅኹት። በጊዜው ሌሎች እንዳደረጉት በየሚዲያው እየወጣው እኔ ቡናን እወደዋለሁ እያልኩ ማውራቱን አልፈለኩም። አንድ ነገር የሚታወቀው በልብ ባለ ነገር እንጂ በማውራት አይደለም። ያው በወቅቱ በጣም ያስቸግሩኝ ስለነበር የራሴን ብቃት ከማስተካከል ይልቅ እነርሱ ላይ ትኩረት ማድረጌ ከምወደው ክለብ በዚህ ምክንያት ልለቅ ችያለው።

በመቀጠል ወደ መከላከያ ነው ያመራኸው፣ በመከላከያም የጥሎ ማለፍ ዋንጫ ማንሳት ችለሀል፤ በአፍሪካ መድክ ለመሳተፍ እድሉን አግኝተሀል። የመከላከያ ቆይታህ ምን ይመስላል?

በ2006 የዝውውር መስኮቱ ተዘግቶ ወደ ሌላ ክለብ ማምራት የማልችልበት ጊዜ በመሆኑ ለአምስት ወር ለመቀመጥ ተገድጄ በግማሽ ዓመት ነው መከላከያን መቀላቀል የቻልኩት። በመከላከያም ጥሩ የሚባል የውድድር ቆይታ አድርጌያለው። በካፍ ኮፌዴሬሽን ካፕ ላይ መሳተፍ ችያለው። እንዲያውም የኬንያው ክለብ ሊዮፓርድ ሊያስፈርመኝ አንዳንድ እንቅስቃሴ ጀምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ሳይሳካ እንጂ አሪፍ ጊዜ ነበር። በአጠቃላይ በመከላከያ በቆየሁባቸው ወቅቶች ጥሩ የሚባል ጊዜ አሳልፌለው። ተደጋጋሚ የጥሎ ማለፍ ዋንጫን ማንሳት ችያለው።

መከላከያ እያለህ የጉዳት ሁኔታ የእግርኳስ ህይወትህን መረበሽ ጀምሮ ነበር። ለመሆኑ ምን ነበር ያጋጠመህ ጉዳት?

የጉልበት ጉዳት ነው። እንዳጋጣሚ ሆኖ ባለቤቴ ጀርመን የምትገኝ በመሆኗ ክለቡን አስፈቅጄ ወደዛ በማቅናት የቀዶ ጥገና ህክምና አድርጌ ተመልሻለው። ሆኖም ስመለስ እንደ አጋጣሚ ኮንትራቴ ከመከላከያ ጋር አብቅቶ ስለነበር መከላከያ ሊያስቀጥለኝ አልቻለም። በወቅቱ በዚህ ነገር ቅር ተሰኝቼ ነበር። ምክንያቱም ለብሔራዊ ቡድን ተጠርቼ መግባት ሲገባኝ መከላከያ ከንግድ ባንክ ጋር ያለውን ጨዋታ ተጫውቼ እገባለው ስል ነው ጉዳት ያስተናገድኩት። ለቡድኑ ተጎድቼ ቡድኑ ሳያሳክመኝ በራሴ ወጪ ታክሜ ስመለስ በዚህ መልኩ እኔን መቀበላቸው አስከፍቶኛል። በዚህ ሁኔታ ከመከላከያ በመቀጠል ወደ ሌላ አራተኛ ክለብ ማምራት ችያለው።

ከመከላከያ በኋላ ባመራህባቸው ክለቦች ብዙም ስኬታማ አልነበርክም። ለምን ?

አዎ። በዋናነት ኢትዮ ኤሌክትሪክ የነበረኝ ቆይታ በእግርኳስ ህይወቴ ጥሩ የማይባል ጊዜ ነው። የተለየ ምክንያት ኖሮ ሳይሆን ያው በእግርኳስ ያጋጥማል። ጥሩ የማይባል አቋም ላይ ነበርኩ። በዚህም የተነሳ ደካማ የሚባል የውድድር ጊዜን አሳልፌ ወደ ወልዋሎ አምርቻለው። በወቅቱ ግን ከኢትዮ ኤሌትሪክ ጋር የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫን ማንሳት ችያለው።

በወልዋሎም በተመሳሳይ ወጣ ገባ የነበረ ቆይታ ነበረህ። እንዲያውም ኮንትራትህ ሳይጠናቀቅ ነው ከክለቡ ጋር የተለያየህው?

ለእኔ በወልዋሎ የነበረኝ የግማሽ ዓመት ቆይታ በጣም አሪፍ ነበር። የአዲግራት ህዝብ በጣም ሰው አክባሪ ሰው የሚወድ ፍቅር የሆነ ህዝብ ነው። በዚህ አጋጣሚ ማመስገን እፈልጋለው። በነበረኝ ወልዋሎ ቆይታ ጎሎችን በማስቆጠር ክለቡን እያገለገልኩ ነበር። ሆኖም ከግማሽ ዓመት በኋላ ነገሮች እንደፈለኩት አልሄደልኝም። በዚህ መሐል ቡድኑ ውስጥ አላስፈላጊ ነገር ሲፈጠር በገዛ ፍቃዴ ኮንትራት እያለኝ ልለቅ ችያለው።

ለመልቀቅህ ምክንያት የሆነው ምድነው? በተጨማሪም ይዘህው የሄድከው ገንዘብ አለ ይባላል። ለዚህ ያለህ ምላሽ ምድነው ?

እግርኳሱ በዚህ መልክ መሄድ የሌለበት በሚል ነው በራሴ ውሳኔ የለቀቅኹት። በመጀመርያው ዙር ቡድኑን በጥሩ ሁኔታ አገልግያለው። ሁለተኛው ዙር ላይ ግን ወደ ተጠባባቂ ወንበር ላይ መቀመጥ ጀምሬ ሁለት ደቂቃ፣ አምስት ደቂቃ እኔን ማጫወት ጀምሩ። ይህ የሆነው በብቃት እንዳልሆነ በሚገባ አውቃለው። ስለዚህ ቡድኑ ከሚጎዳ እኔ ደግሞ ደሞዝ እየተከፈለኝ የማልጫወት ከሆነ ምን እሰራለው በማለት ከወልዋሎ ምንም የወሰድኩት ገንዘብ ሳይኖር ወጥቻለው። እንዲያውም ያልተከፈለኝ የወር ደሞዝ እያለ ትቼ የሄድኩት። ይህ ሆኖ ሳለ የወጣሁበትን እውነተኛ ምክንያት በሌላ መንገድ ተዛብቶ በማቅረብ ያልሆነ ነገር ሲወራ ሰምቻለው። እውነታው ግን ደጋፊው እንዲረዳ ይሄ ነው።

ከክለቦች ጋር የምትለቅባቸው መንገዶች አወዛጋቢ እና በቅራኔ የተሞሉ ናቸው። በመድን ለረጅም ዓመት ኮንትራት ነበረህ። ይህን ኮንትራት አፍርሶ ለመውጣትም ውዝግብ ነበር። በቡና (ከቲፒ ማዜምቤ ጋር ሲጫወቱ) ከደጋፊዎች ጋር በፈጠርከው እሰጣገባ እስከመቀጣት ደርሰህ ነበር። በመጨረሻም ውል አፍርሰህ ለቀቅህ… በወልዋሎም በሰላም አልተለያየህም። እነዚህን ነገሮች እንዴት ታያቸዋለህ?

በእርግጥ ልክ ነው የምለያይበት መንገድ በውዝግብ የተሞላ ነው ማለት ይቻላል። ከኢትዮጵያ መድን ጋር ገና “ቢ” ቡድን ውስጥ እያለው። ልጅነትም ስላለ፣ ለዋናው ቡድን ለመጫወት ጉጉት ስለነበረን ጭምር በደስታ ለቢ ቡድኑ በነጭ ወረቀት ላይ ፈረምን። ሆኖም እነርሱ በራሳቸው መንገድ ኮንትራቱን ለስምንት ዓመት አደረጉት። እኔ ደግሞ አንድ ተጫዋች በታዳጊ ቡድን አንድ ልጅ ለሦስት ዓመት ብቻ መጫወት እንደሚችል ስላወቅኹ መከራከር ብችልም የትኛውም ቦታ ስሄድ መርታት አልቻልኩም። በዚህ ምክንያት ለዋናው ቡድን ሦስት ዓመት ከተጫወትኩ በኃላ 75 ሺህ ብር ከፍዬ ልለቅ ችያለው። በኢትዮጵያ ቡናም እንዲህ ያለ አጋጣሚ ተፈጥሯል። በጥሩ ሁኔታን ቡናን እያገለገልኩ ባለሁበት ወቅት 2005 ላይ ከቲፒ ማዜምቤ ጋር ስንጫወት የተወሰኑ ደጋፊዎች እኔ ላይ የተለየ ዓላማ ኖሯቸው ተቃውሞ ሲያነሱ ከዚህ በኋላ መቆየት ይከብደኛል ብዬ በማሰብ የአንድ ዓመት ኮንትራት እየቀረኝ 225 ሺህ ብር ከፍዬ ልለቅ ችያለው።

አሁን በምን ሁኔታ ትገኛለህ? ከዕይታ ርቀሀል.. እግርኳስን አቁመሀል?

እግርኳስን አቁሜያለው የሚል ውሳኔ ላይ አልደረስኩም። ገና የመጫወቱ አቅሙ እድሜውም አለኝ፣ በአሁኑ ወቅት ከባለቤቴ እና ከልጆቼ ጋር ጀርመን እገኛለሁ። ከእግርኳሱ አልራቅኩም በግሌ ልምምዶችን እየሰራው ነው። የሀገሬ ልጆች የሚሰባሰቡበት ኢትዮ አዲስ ፍራንክፈርት የሚባል ቡድን አለ። ከእነርሱ ጋር በመሆን ልምምድ እየሰራን ከሌሎች ቡድኖች ጋር እጫወታለን። የመጀመርያ (ክርስቲያን ሙሉዓለም) ገና 15 ቀን ያስቆጠረው ሁለተኛ (ማታን ሙሉዓለም) ልጆች አሉኝ። በዚህም ደስተኛ ነኝ፣ ደስ የሚል ኑሮ እየኖርኩ ነው። በሌላ አጋጣሚ በእግርኳስ ውስጥ አልራቅኩም። ከጀርመን ሀገር የተለያዩ የስፖርት ቁሳቁሶችን በማምጣት ሀገሬ ላይ ሱቅ ከፍቼ የንግድ ስራ ጀምሬ እየሰራው እገኛለው።

እስቲ አብርሀቸው ከተጫወትካቸው ተጫዋቾች ውስጥ የምታደንቀው እና ለእኔ ከባድ ተከላካይ ነው የምትለው ካለ ንገረኝ ?

በእግርኳሱ ከተለያዩ ተጫዋቾች ጋር ተጫውቼ አልፌያለው በተለይ ከአማካይ ስፍራ ተጫዋቾች ጋር የተለየ የአጨዋወት ቅርርብ ነበረኝ። ለምሳሌ ታደለ መንገሻ መድን እያለን በጣም ጥሩ ህብረት እና መናበብ ነበረን። በኋላም ከዳዊት እስጢፋኖስ፣ መስዑድ መሐመድ እንዲሁም ቢንያም ታዬ (ግስላ)፣ በመከላከያ ከሚካኤል ደስታ ጋር በጣም ተግባብቼ በደንብ እጫወት ነበር። በተቃራኒ ከገጠምኳቸው ደግሞ ለእኔ በጣም ከባዱ እና ያስቸገረኝ ተከላካይ የምለው ደጉ ደበበ ነው።

ስለ አንተ አንዳንድ ተጫዋቾች ስጠይቅ በጣም ቀልድ አዋቂ ሳቅ የሚጭር ተጫዋች ነው ይሉሀል?

አዎ ቅድም እንዳልኩሁ ተወልጄ ያደኩት መርካቶ ነው። መርካቶ ደግሞ በጣም ቀልድ ጨዋታ የበዛበት አካባቢ ነው። በተጨማሪም ቀልድ አዋቂ ጓደኞች ነበሩኝ። ያው እኔም እቀልዳለው እጫወታለው። ሜዳ ላይም የተለያዩ ነገሮችን እያነሳን ሳቅ የሚያጭሩ ነገሮችን ከተጫዋቾች ጋር እናደርጋለን። በመድንም ቡናም በሌሎች ክለቦችም በቀልድ በጨዋታ እታወቃለው።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የነበረህን ቆይታ ንገረኝ?

በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ አማካኝነት ለብሔራዊ ቡድን በተደጋጋሚ ለመጠራት ችያለው። ሆኖም በአራት አጋጣሚ ጉዳት አጋጥሞኝ ብሔራዊ ቡድንን ማገልገል አልቻልኩም። ዮሐንስ ሳህሌ በእኔ አጨዋወት እምነት ስለነበረው ከጉዳቴ አገግሜ በድጋሚ ሊጠራኝ ችሏል። እንዲያውም በአንዳድ ሚዲያ እንዴት ከጉዳቱ ሳያገግም ይጠራል ብለው ሀሳብ ሰጥተው ነበር። ይህም ቢሆን ሩዋንዳ በተዘጋጀው የቻን ውድድር ላይ በሁለት የምድብ ጨዋታ ላይ የመጀመርያ ተሰላፊ በመሆን ሀገሬን በጥሩ ሁኔታ ማገልገል ችያለው። ከዚህ በኋላ ጉልበቴን ቀዶ ጥገና ካደረኩ በኋላ ተመልሼ ብሔራዊ ቡድን መጠራት አልቻልኩም።

የእግርኳሳችን ድክመት የምትለው ምንድነው?

አንዳንድ የማይመቹ ነገሮች አሉ። ከእግርኳሱ ችሎታ በላይ የሚጮህ ነገር ይበዛል። ለሰዎች ገኖ እየተወራ ነው። ተጫዋቹ ትኩረት ማድረግ ያለበት ጨዋታው ላይ ብቻ መሆን አለበት። ሆኖም በየሚዲያው ጩኸት ይበዛል። ጋዜጠኛው ተጫዋቹን ማድነቁ ወይም ህዝቡ አይቶ ይፍረድ እንጂ በየሚዲያው ማውራት በፌስቡኩ ማጮህ ተገቢ አይደለም። ይህ ለራሱ ተጫዋቹ ለቀጣይ ህይወቱ መጥፎ ነው። የሌለህን አለ ተብሎ ሲገን ጥሩ አይደለም ። ለምሳሌ በ2003 ቡና ቻምፒዮን ሲሆን እንደ ቡድን ሰርተን ነው እንጂ እኔ ጎል አሰቆጥሬ ለጎል የሚሆን ኳስ አመቻችቼ እያልኩ ባወራ አይጠቅምም። በወቅቱ እንደነ ተስፋዬ ዲባባ፣ ሲሳይ ደምሴ አይነት ጠንካራ ተከላካዮች አሉ። ስለ እነርሱ ብዙ አልተወራም። እናም ተጫዋች ተመርጦ በቲፎዞ የሚጮሆው ነገር በአጠቃላይ ለእግርሏስ እድገታችን ጥሩ አይደለም፤ ከታዘብኩት ነው።

በብዙ አሰልጣኞች ሥር አልፈሀል። ካሰለጠኑህ አሰልጣኞች የማን አድናቂ ነህ ?

እንዳልከው ከብዙ አሰልጣኞች ጋር ሰርቻለው። ሁሉም የራቸው አቅም እና የተለየ የአጨዋወት ፍልስፍና አላቸው። ያም ቢሆን ከጠየከኝ አንፃር ካሰለጠኑኝ አሰልጣኞች መካከል በስብዕና፣ በእግርኳሳዊ እውቅት እና በሚከተሉት የጨዋወት መንገዳቸው እንዲሁም ጥሩ ቡድን በመስራት የአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ እና ውበቱ አባተ አድናቂ ነኝ።

የመጨረሻ ጥያቄ ላድግ የመጀመርያ እና የመጨረሻው ጎልህን አስታውሰኝ። እንዲሁም ለእግርኳስ ህይወቴ ረዳኝ የምትለውን አካል አመስግን?

በክለብ ደረጃ በመጫወት የመጀመርያ ጎሌ ከኢትዮጵያ መድን ጋር የሚሌኒየሙ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ኢትዮጵያ ውሃ ስራ ላይ ያስቆጠርኩት ነው። ወደ ኋላ ሆኜ ሳስበው ያቺ ዕለት ልዩ ነበረች። ሜዳው ውስጥ ህይወቴ የተቀየረ ያህል ነው ስሜት የተሰማኝ። ወደ ጀርመን ከማቅናቴ በፊት የመጨረሻ ጎሌ በወልዋሎ ማልያ ዐዲግራት ላይ ከወላይታ ድቻ ጋር አንድ አቻ በወጣንበት ወቅት ያስቆጠርኩት ነው። ማመስገን የምፈልገው ቤተሰቤ፣ ባለቤቴ እንዲሁም ጋደኛዬ እንደ ወንድሜ የማየው አምሀ አስፋው (ቤቢ) ትልቁን ሚና ይወስዳሉ። በተለይ አምሀ በእግርኳሱ ትልቅ ዘደረጃ እንድደረስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረገው እርሱ በመሆኑ በዚህ አጋጣሚ እንድታመሰግንልኝ እፈልጋለው።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ