ሦስት የፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ያነሳውና በቴክኒክ ክህሎታቸው ከሚታወቁ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው አብዱልከሪም ሀሰን (ምርምር) በአሁኑ ወቅት የት ይገኛል?
ማታ ማታ በውጭ ሀገር የሚመለከታቸውን ጨዋታዎች ቀን በልምምድ ሜዳ ለመሞከር የሚያደርገውን ጥረት የተመለከተው አዳነ ግርማ ምርምር የሚል ቅፅል ስም አውጥቶለታል። አብዱልከሪም ትውልድ እና እድገቱ አዲስ አበባ አስኮ አካባቢ ነው። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ተስፋ ቡድን እስከ ዋናው ቡድን ድረስም መጫወት ችሏል። ከፈረሰኞቹ ጋር ሦስት የፕሪምየር ሊግ ዋንጫን በማንሳት መልካም የሚባል ቆይታ አድርጓል። ። በመቀጠል በኢትዮጵያ ቡና እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ መጫወት ችሏል። በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እየተጫወተ ባለበት ወቅት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች በመባል ተመርጠሸል። በመጨረሻም በሀዋሳ ከተማ የወራት ቆይታ አድርጎ ያለፈውን አንድ አመት ከስድስት ወር ከሜዳ ርቋል። የቆሙ ኳሶች አጠቃቀሙ እና ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል መለያዎቹ የሆኑት ይህ የመስመር አጥቂ ኳስ አቆምክ? ወይስ በምን ሁኔታ ላይ ትገኛለህ? ስንል ጠይቀነው የሚከተለውን ምላሽ ሰግቶናል።
“በመጀመርያ አስታውሳችሁ ስለደወላቹሁልኝ አመሰግናለው። እግርኳስን አላቆምኩም። በግሌ ልምምድ እየሰራሁ ነው። ያው በኢትዮጵያ እግርኳስ መጫወት ከባድ ነው። በዚህ ዓመት አንድ ክለብ የመግባት እቅድ ነበረኝ፣ ይሳካልም ብዬ ነበር። ሆኖም በተለያዩ ምክንያቶች ሳይሳካ ቀርቷል። ከፈጣሪ ጋር በቀጣይ ዓመት ወደምወደው እግርኳስ መመለሴ አይቀርም።”
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ