ሠላሳ ዓመታት የዘለቀው የጓደኝነት እና እግርኳስ ጉዞ

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ረጅም አመታትን በወጥ አቋማቸው ተጫውተዋል። በአንድ ክለብ አብሮ ከመጫወት አንስቶ በርካታ ክለቦች ያዳረሱት ሁለቱ ጓደኛሞች ስላሳለፉት ዘመናት አውግተውናል፡፡

ከጋሞ ጎፋ ዞን ትውልዳቸውን ያደረጉት ሁለቱ የእግር ኳስ ተጫዋቾች በአካባቢው የእግርኳስ ህይወታቸውን አሀዱ ብለው ጀምረዋል፡፡ ገረሱ ሸመና ተወልዶ ያደገው በጨንቻ ከተማ ነው። የልጅነት ጊዜውን በዛው ካጣጣመ በኋላ ወደ አርባምንጭ ከተማ ተጉዟል። በአርባምንጭ የክለብ ህይወትን ከጀመረ በኋላ በነበረው አስደናቂ አቋም ወደ ሀዋሳ በመጓዝ ሀዋሳ ከተማን ተቀላቅሏል፡፡ በሀዋሳ ከተማም እጅግ ድንቅ ጊዜያትን ካሳለፈ በኃላ ወደ ትራንስት ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ፖሊስ እና ስልጤ ወራቤ ቀሪ የክለብ ህይወቱን ዕድሜ ሳይገድበው ከተጫወተ በኃላ ከሁለት አመታት በፊት በ2010 ክረምት ላይ ከእግር ኳስ ራሱን አግልሎ 2011 የስልጤ ወራቤ ረዳት አሰልጣኝ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል።

ሌላኛው ተከላካይ አፈወርቅ ዮሐንስ ነው። ከአርባምንጭ እርሻ ጣቢያ የጀመረው የመጫወት ጅምሩ ለደቡብ ክልል ምርጥ ቡድን ተመርጦ በመጫወት ላይ እያለ ያሳየውን አቋም ተከትሎ ወደ ሀዋሳ ከተማ ዋናው ቡድን 1987 መቀላቀል ችሏል። በሀዋሳ ከተማ ቆይታው ከጓደኛው ገረሱ ሸመና ጋር ያሳየው ድንቅ ጥምረትን ተከትሎ እሱም እንደ ገረሱ ሁሉ በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ አማካኝነት ወደ ትራንስ ኢትዮጵያ ተጉዞ በጋራ ክለቡን አገልግለዋል፡፡ አፈወርቅ በትራንስ ቆይታው ከክለቡ ጋር በግል ጉዳዮች ላይ መግባባት ባለመቻሉ ክለቡን ሲለቅ ጓደኛው ገረሱ ግን በክለቡ ቀጥሏል። አፈወርቅም የሰሜኑን ቡድን ከለቀቀ በኋላ ወደ ወደ ንግድ ባንክ አምርቶ ስድስት ዓመታትን ከቆየ በኋላ አዳማ ከተማ፣ ኒያላ፣ ሜታ አቦ ቢራ፣ ሼር ኢትዮጵያ፣ ሻሸመኔ ከተማ እና ደቡብ ፖሊስ ቆይታውን አድርጎ ከ2009 እስካለፈው ዓመት በቡታጅራ ከተማ በአምበልነት እና በተከላካይነት በመጫወት የእግር ኳስ የተጫዋችነት ዘመኑን ዘንድሮ በይፋ ቋጭቷል፡፡

ከ1983 ጀምሮ ከአርባምንጭ ከተማ ጓደኝነትን የጀመሩት ሁለቱ ተጫዋቾች ምንም እንኳን ክለቦችን ሲቀያይሩ ይለያዩ እንጂ በጓደኝነት እና በተጫዋችነት ስኬትን አጣጥመዋል፡፡ በሀዋሳ ከተማ ቡድን ውስጥ የጀመረው በቋሚ አሰላለፍ ገብቶ ጥሩ ጥምረት ከመፍጠር አንስቶ እስከ ብሔራዊ ቡድን የዘለቀው የተጫዋችነት ዘመናቸው ራሳቸውን በመጠበቅ ረጅም ዓመታትን ካሳለፉ በኋላ ሁለቱም የተጫዋችነት ዘመናቸው ቢገባደድም ዛሬም ይህ የጠለቀ ጓደኝነታቸው ዛሬም ቀጥሏል፡፡ በብዙዎች ዘንድ አድናቆት እና ክብር የሚሰጠናቸው ሁለቱ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቾች ዘመናትን ስለ ተሻግረው የእግር ኳስ እና የጓደኝነት ህይወታቸው ከዛም በዘለለ አጥር ስለማይለየው ጉርብትናቸው ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታን ባደረጉበት ወቅት ገልፀዋል፡፡

ገረሱ ከአፈወርቅ ጋር ስለ ነበረው የሜዳ ቆይታ እንዲህ ይናገራል። “ሜዳ ላይም ልክ እንደውጪ እንነጋገራለን። ከነማ እያለን ሁሉም ነገራችን በመነጋገር ነው፡፡ በምንችለው ቋንቋ ሌላው እንዳይሰማን ብለን በራሳችን ቋንቋ እናወራ ነበር። ያን ከተነጋገርን ተግባራዊ እናደርገዋለን። እስከዛ ደረጃ ነበር ግንኙነታችን። በወቅቱ ከኛም አልፎ ዘውዱ በቀለን ወደኛ እንመልሰዋለን እኛም የምንፈልገውን አይነት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ እናደርጋቸው ነበር። ሀዋሳ እያለን ከአሰልጣኝ ከማል ጋር ጥሩ ነገር አሳይተናል። ያለመሸነፍ ስነ ልቦና ይዘን ነው የምንባው። የሀዋሳ ሜዳ እንደ አሁኑ አልነበረም፤ በዛ ሜዳ ሰውነታችን የለም ማለት እስከሚቻል ድረስ መስዋዕትነት እንከፍል ነበር። ለቡድኑ እኔ እና አፈወርቅ ሌሎቹም ቢሆኑ መስዋዕትነት ከፍለዋል። ያኔ ለራሳችን ምንም አልተጠቀምንም፤ ህዝቡ ግን ፍቅር ሰጥቶናል። ህዝቡ አሁንም ሜዳ እኛ ስንገባ እያየን የሚሰጠን ፍቅር በጣም ነው የሚያረካኝ። ይሄ የሆነው አውርተን ሳይሆን አሳይተን ነው። ከእኛ በኃላ የመጡትን እነ ሙሉጌታ ምህረት እና አዳነ ግርማም ከእኛ ያዩት ነገር ተግብረው ነው ዛሬ የደረሱበት የሚገኙት።” በማለት ስለ ሀዋሳ ከተማ ቆይታቸው አውስቶናል፡፡

አፈወርቅ ይቀጥላል… “ገረሱ ሜዳ ላይ እንደ ሀገር መሪ ማለት ነው፤ ያለውን ነገር ጨርሶ ይሰጣል። እሱ ተከላካይ ሆኖ አጥቂ ቦታ ያለውን ያበረታል። ይሄ ማለት አንድ አላማ ስለሆነ እሱ የሚታወቀው ሜዳ ውስጥ እስከ መጨረሻው ዋጋ ይከፍላል። ይመራል ይጮሀል ዳኛን ሁሉ እስከ መቆጣጠር ይደርሳል። እኔ ብዙም አይደለሁም፤ በዚህ ረገድ ከእኔ ይለያል። አብረን ስንሆን ከእኔ ጋር የመነጋገር የመናበብ ነገር አለን። ግን የሱን ያህል የጎላ ነገር እኔ የለኝም። ከሜዳ ውጪም ጨዋታ ነው፤ ነፃ የሆነ ሰው ነው። ይሄ ነው የሱ ባህሪ እስከ አሁንም ያቆየን ይሄ ነው፡፡ ”

ገረሱም ስለ አፈወርቅ ባህሪ እንዲህ ይላል “አፈወርቅ የኔን ነግሮሀል። እሱ ግን ዝምተኛ ነው፤ ከማውራት መስራቱን ነው የሚያስቀድመው። ሥራ ሥራ ነው፡፡ ግን ጭምት ነው፤ እንደውም የሜዳው ይሻላል። ውጪማ ሰው ካገኘ ዝቅ ብሎ አክብሮ ሰላም ብሎ ነው የሚያልፈው። አሁን እሱ ሰውን ሰላም ሲል እኔ አፍራለሁ። እሱ በጣም ነው ታች ወርዶ ሰላም የሚለው። የሱ ባህሪ በጣም የተለየ ነው። ሌሎችንም ብትጠይቅ ይሄው ነው። እኔም ከሰው ጋር እግባባለው የሱ ግን በጣም ወጣ ያለ ነው። ወጣ ያለ ነው ስል ግን በሌላ ነገር አይደለም፤ ለሰው ያለው ክብር ከእኔ የተለየ ነው፡፡”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ