ዛሬ ማለዳ ህይወቱ በድንገት ስላለፈው የአርባምንጭ ከተማ ግብ ጠባቂ ፍሬው ገረመው የክለቡ ዋና አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ እና አምበሉ ወርቅይታደስ አበበ ለሶከር ኢትዮጵያ እንዲህ ይላሉ…
አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ
ስለ ተጫዋቹ ህመም
“አብሮት ወላይታ የሄደ እኛ ቡድን የሚጫወት ልጅ ነበር። ጠዋት ላይ ለኛ ሲነግረን ከቁርጭምጭሚቱ በላይ ከጉልበቱ በታች ትንሽ እንደ እጢ ነገር በህክምና ማስወጣት ፈልጎ ሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል አንድ ሁለቴ ከዚህ ቀደም ሄዷል። ከዛም ትላንት ነበር የተሰራው፤ እሱን ዕጢ በማስወጣት ላይ እያለ ነው ህይወቱ ያለፈው፡፡”
ስለ ህልፈቱ
“መጀመሪያ ስትሰማ ትደነግጣለህ፤ ከሱ ጋርም ሆነ ከሌሎች ተጫዋቾች ጋር በዚህ ዓመት የጀመርናቸው ነገሮች አሉ። ከ36ቱ ቡድኖች የተሻለ ወደ ፕሪምየር ሊግ የማደግ ተስፋ ነበረን። ይሄን ዕድል ቢያይ የሚል ስሜት ይሰማኛል። የቡድኑ ህብረት እና መተባበር ደስ ይል ነበር። እሱም ጥሩ አስተዋጽኦ እያደረገ ነበር። ወጣት ስለሆነ በቀጣይ ብዙ ተስፋ ያለው ልጅ ነበር። ቤተሰቡንም የሚረዳ ልጅ ነው እኚህ ሁሉ ካሰበበት ሳያደርሰው በማለፉ ውስጤን ተሰምቶኛል፡፡”
ወርቅይታደስ አበበ
ስለ ድንገተኛ አሟሟቱ
“ለኛ ድንገተኛ ነው የሆነብን። አጋጣሚ ሆኖ እኔ የሰማሁት ለሊት አካባቢ ነበር። እኛ እንደውም ቀልድ ነው፤ አፕሪል ዘፉል እንደሚባለው ጨዋታ ነው ብለን ነበር ያሰብነው። ልምምድ ለመስራት ጠዋት መንገድ ላይ እያለሁ ነው እውነት መሆኑን ያረጋገጥኩት። እኔ በጣም ነው የደነገጥኩት፤ ትላንት በሰፈሩ ሳልፍ ሰላም ነበር። ይሄን ያህል ያመመውም ምንም ነገር አልነበረም። ከእንቅስቃሴ የሚገድበውም ነገር አልነበረም። ልምምድም ሲሰራ ነበር። በጣም ነው ያዘንነው። እንደ አጋጣሚ አሰልጣኛችንም አልሰማም ነበር፤ በቀጥታ ቤቱ ሄጄ ነበር የነገርኩት እና ያልታሰበ እና ፈፅሞ ያልገመትነው ነገር ነው። ከቁጥር አንድ ሰው ጎድሎብናል። ”
ስለ ፍሬው ባህርይ
“እንደሚታየው አይደለም፤ ስትቀርበው ተጫዋች ነው። ስብሰባ እና ስለ ቡድናችን ስንወያይ ፈታ ያደርገናል፣ ያስቀናል፣ ከሁሉም ጋር ተግባብቶ የሚኖር ልጅ ነበር። ቡድናችንም ዘንድሮ ዕቅዱ ወደ ፕሪምየር ሊጉ መግባት ነበር እና ለዚህም ደግሞ ዕርስ በዕርስ የነበረን ግንኙነት በጣም አስገራሚ ነበር። እሱም ጉልህ ድርሻ ነበረው። በባህሪውም በሰፈር ልጆችም የሚወደድ ልጅ ነበር።”
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ