በጎ ፍቃደኛ ሀኪሞች ለስፖርተኞች የሙያ ድጋፍ ለማድረግ ጥሪ አቀረቡ

ከውድድሮች ርቀው በቤታቸው ለሚገኙ ስፖርተኞች ኦንላይን በነፃ የሥነ ልቦና ድጋፍ የማድረግ ዓላማ ያላቸው ባለሙያዎች ዝግጅታቸውን አጠናቀው ወደ ተግባር ሊገቡ ነው።

በኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ምክንያት እንደተቀረው ዓለም ሁሉ በሀገራችንም የሊግ እና መሰል ስፖርታዊ ውድድሮች ላልተወሰነ ጊዜ መቋረጣቸው ይታወቃል። በመሆኑም ከለመዱት በእንቅስቃሴ የተሞላ ውሎ በተቃራኒው ተጫዋቾች ጊዜያቸውን በቤታቸው እያሳለፉ ይገኛሉ። በዚህ ሳቢያ ለሚከሰቱ ከአካል ብቃት ጋር ለየገናኙ ችግሮች ክለቦች እና አሰልጣኞች በተለያዩ አማራጮች ተጨዋቾች ብቁ ሆነው ይህን ጊዜ እንዲያሳልፉ ጥረት እንደሚያደርጉ ይሰማል። ከዚህ ባለፈ ግን አዕምሯዊ የሆኑ ጉዳዮች የተዘነጉ ይመስላሉ። ሆኖም ይህን ክፍተት ያስተዋሉ የህክምና ባለሙያዎች በሙያቸው የበጎ ፍቃድ እገዛ ለማድረግ እንዳሰቡ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል።

ባለሙያዎቹን በመወከል ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ ያደረጉት ዶ/ር በረከት ፀጋዬ እንደገለፁት
ከዚህ በፊት ያልነበሩ እና የተለዩ እንደ ድብርት ወይም ጭንቀት ዓይነት ስሜቶች የሚሰሟቸው የሙሉ ጊዜ እግር ኳስ ተጨዋቾች ፣ አትሌቶች እንዲሁም ሌሎች ስፖርተኞች የዚህ ዕድል ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ገልፀዋል። ዶ/ር በረከት ችግሩ የሚገጥማቸው ስፖርተኞች ላይ የሚታዩ ምልክቶችን ሲዘረዝሩ ” የተሰጣቸውን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለመተግበር ፍላጎት እና አቅም ማጣት ፣ ለተከታታይ ቀናት/ሳምንታት የድብርት ስሜት ውስጥ መቆየት ፣ የእንቅልፍ መዛባት (ለሊት እንቅልፍ ማጣት እና ቀን መተኛት) ፣ የበዛ ጭንቀት (ስለብዙ ነገሮች ማሰብ) ፣ ተስፋ መቁረጥ እና ከሰዎች ጋር ማውራት ያለመፈለግ ስሜቶች ሊስተዋሉባቸው ይችላል። ” ብለዋል።

ህክምናው ለጊዜው ከሦስት እስከ አራት በሚሆኑ የሥነ አዕምሮ ሬዚደንት ሀኪሞች የሚሰጥ ሲሆን እንደ አስፈላጊነቱም ሲኒየር የሳይካትሪ ሀኪሞች የሚሳተፉበት ይሆናል። ለዚሁ ተግባር ሲባል በተከፈተው የቴሌግራም ግሩፕ ላይ (ሊንኩን ከስር ማግኘት ይችላሉ) መሰል ችግሮች ያሉባቸው ስፖርተኞች የህክምና ባለሙያዎቹን ማግኘት ይችላሉ። ሀኪሞቹም ዘወትር ረቡዕ ምሽት ከ11:00 – 01:00 እንዲሁም እሁድ ጠዋት ከ05 ፡00 – 07:ዐዐ ድረስ በቴሌግራም ግሩፑ ላይ ኦንላይን ሆነው የሚጠባበቁ ሲሆን ህክምናውንም ኦንላይን ወይንም በስልክ በኩል ከዛም አለፍ የሚል ከሆነ በአካል በመገናኘት በበጎ ፍቃደኝነት የሚሰጡ ይሆናል። ሆኖም አሁን ካለው ሁኔታ አንፃር ስፖርተኞችንም ከወጪ ለመከላከል አብዛኛው እገዛ በኦንላይን እና በስልክ እንዲያቅ ለማድረግ እንደሚጥሩም ዶ/ር በረከት ገልፀውልናል። ከዚህ በተጨማሪ የዶክተሮቹ ስብስብ በቀጣይ ይህን ጉዳይ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋቾች ማህበር ጋር በቅርበት የመስራት ሀሳብ እንዳለው ተናግረዋል።

መሰል እገዛ ማግኘት የምትፈልጉ ስፖርተኞች ይህን ሊንክ በመጠቀም ወደ ቴሌግራም ግሩፑ መቀላቀል ትችላላችሁ።  👉 TELGRAM 


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ