” የሞሮኮ ሴራ በኦሊምፒክ ማጣርያ” ትውስታ በቢንያም አሰፋ

ለ2004 የአቴንስ ኦሊምፒክ ለማለፍ የመጨረሻው ምዕራፍ ደርሶ የነበረው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ብሔራዊ ቡድን ከታሪካዊው ውድድር የቀረበት ሁኔታ “የሞሮኮ ሴራ ነው” ሲል ቢንያም አሰፋ በትውስታ አምዳችን ይናገራል።

ጊዜው 1996 ነው። ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ማጣርያ ተሳትፎ ታሪኳ እንዲህ የመጨረሻ ምዕራፍ ደርሳ አታውቅም። በአሰልጣኝ ሥዩም አባተ የሚመራው ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ታዲዮስ ጌታቸው፣ ጌቱ ተሾመ፣ አንዷለም ንጉሴ (አቤጋ)፣ ኤልመዲን መሐመድ፣ ታፈሰ ተስፋዬ፣ ደብሮም ሐጎስ፣ ቢንያም አሰፋ እና ሌሎችም ነበሩ። ከሞሮኮ፣ አንጎላ እና ዩጋንዳ ጋር የተደለደለችው ኢትዮጵያ በሜዳዋ ያደረገቻቸውን ሦስቱንም የምድብ ጨዋታዎች በሙሉ በማሸነፍ ዘጠኝ ነጥብ ብትሰበስብም ከሜዳዋ ውጭ ያደረገቻቸውን ጨዋታዎች በአንፃሩ በሙሉ ተሸንፋለች።

የምድቡ የመጨረሻ ጨዋታዎች ወደ አቴንስ የሚወስደውን ትኬት የሚቆርጠውን ቡድን የሚወስኑ በመሆኑ ተጠባቂ አድርገውታል። ከመጨረሻው ጨዋታ በፊት አንጎላ በ10 ነጥብ ስትመራ፣ ኢትዮጵያ በ9 ትከተላለች፣ ሞሮኮ ደግሞ 8 ነጥቦች ይዛ ሦስተኛ ላይ ተቀምጣለች። ኢትዮጵያ ለማለፍ ካምፓላ ላይ ዩጋንዳን የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ስትገባ አንጎላ በሞሮኮ ነጥብ መጣል ይኖርባታል። አንጎላ በአንፃሩ ሞሮኮን ከሜዳዋ ውጪ ማሸነፍ በቀጥታ የማንንም ውጤት ሳትጠብቅ ወደ ኦሊምፒክ እንድታመራ ያደርጋታል። አጣብቂኝ ውስጥ የገባችው ሞሮኮ ደግሞ አንጎላን በሜዳዋ አሸንፋ የኢትዮጵያን ሽንፈት ትጠብቅ ነበር። ዩጋንዳ አነስተኛ ነጥብ ያላት በመሆኑ ከመርሐ ግብር ማሟያ ውጪ መሸነፍ ማሸነፍ ለእርሷ ምንም ፋይዳ የለውም።

በዚህ ስሌት መሠረት በአሰልጣኝ ሥዩም አባተ የሚመራው ቡድን የማለፍ ተስፋውን ይዞ ወደ ካምፓላ ቢያቀናም ምንም የማለፍ ዕድል በሌላት ዩጋንዳ ሽንፈት አስተናግዶ እና ወደ አቴንስ ሳያመራ ቀርቷል። የወቅቱ የቡድኑ ተጫዋች የነበረው ቢንያም አሰፋም ጋር ጊዜውን ሲያስታውስ “የሞሮኮ ሴራ ነበር” ይላል።

” በወቅቱ ጥሩ የሚባል ቡድን አሰልጣኝ ሥዩም አባተ ሰርቶ ነበር። የመጨረሻ ጨዋታውን ብናሸንፍ እናልፋለን። ዩጋንዳ ላይ እየተጫወትን እነርሱ ቀድመው ጎል ቢያስቆጥሩም እረፍት ከመውጣታችን በፊት አቻ ሆንን። የሚገርምህ ዩጋንዳዎች ቢያሸንፉ የማለፍ እድል የላቸውም፤ ሆኖም ጠንክረው ወጥረው ይዘውን ይጫወታሉ። በመሐል በመሐል እንጠይቃቸዋለን፤ ‘ምንድነው እንዲህ የምትሆኑት? አንድ የምስራቅ አፍሪካ ቡድን ቢያልፍ አይሻልም?’ እያልን እናወራቸው ነበር። ሆኖም ይባሱኑ በሁለተኛው አጋማሽ ጎል አግብተው ጨዋታው 2-1 ይጠናቀቅና ወደ አቴንስ የነበረን ጉዞ ይገታል። የማለፍ ዕድላችን ባለመሳካቱ አዝንን እኔ በግሌ በጣም ይቆጨኝ ነበር። ከጊዜ በኃላ የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች የነበረው አሳኒ ባጆፔ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲመጣ ስለሁኔታው ጠየቅኹት። ‘ለምድነው እንደዛ ኃይለኛ የሆናችሁብን? በጣም ስትከላከሉ ነበር።’ ብዬ ስጠይቀው የመለሰልኝ መልስ “የሞሮኮ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለዩጋንዳ ፌዴሬሽን ብር ከፍሏል” በማለት ለተጫዋቾቹ በነስ ወከፍ 500 ዶላር ተከፍሏቸው እንደነበር ነገረኝ። እኔም በጣም ገርሞኝ ለካ እንዲህ ያለ ነገርም አለ ብያለሁ። ”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ