አስተያየት | የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል…?

በኮሮና ምክንያት እግርኳስ ከአፍቃሪያኑ ከተለየ እነሆ በርካታ ቀናት የተቆጠሩ ሲሆን በሃገራችን ኢትዮጵያ ዛሬ ይፋዊ ጨዋታዎች ከመከወን ከተገደቡ 50ኛ ቀናቸውን ይዘዋል። ይህ ቢሆንም ግን በዓለም ላይ ያሉ የተጀመሩ ውድድሮች ዳግም እንዲመለሱ የተለያዩ ምክረ ሃሳቦች እየተሰጡ እና እየተጤኑ አለፍ ሲልም ደግሞ ውድድሮቹን እንዳይደረጉ ውሳኔ እየተላለፈ ሲሆን በሃገራችን ግን የሊጎቻችን ቀጣይ እጣ ፈንታ ምን እንደሆነ እስካሁን በውል አልታወቀም። በዛሬውም ፅሁፋችን ይህንን ጉዳይ በመመልከት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሊወሰኑ ስለሚችሉ ሚዛን ይደፋሉ ተብለው ስለሚታሰቡ ቀጣይ ውሳኔዎች ሃሳቦችን እናነሳለን።

ኮቪድ 19 በታህሳስ ወር በቻይና ግዛት ሁቤይ ከተማ መነሻነቱን ካደረገ በኋላ በመላው ዓለም በሚገኙ ሃገራት ላይ ተስፋፍቶ ከ200 ሺ በላይ የሆኑ የሰዎችን ህይወት ቀጥፏል። ይህ ወረርሽኝ በአህጉራችን አፍሪካም መዳረሻውን በማድረግ የብዙዎች ስጋት ከሆነ ሰነባብቷል። ሃገራችን ኢትዮጵያም በዚህ ወረርሽኝ ተፅዕኖ ቋሚ ክንውኖቿን ገድባ ቀዳሚ ኢላማዋን በሽታውን መከላከል ላይ በማድረግ እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች። በዚህ ምክንያት ደግሞ ቀዳሚ ተጎጂ የሆነው የሃገራችን እግርኳስም ከጉዞ ተገትቶ በቅርቡ ለመከወን አልያም ላለመከወን የአመራሮቹን ቀጣይ ወሳኔዎችን እየተጠባበቀ ይገኛል።
በዓለም ላይ ያሉ ፈርጣማ የሊግ አስተዳደሮች ሊጎቻቸውን ለማስቀጠል ከሚወስኑት ወሳኔ ጎን ለጎን የህዝባቸውን ጤና፣ ሊያገኙ ወይንም ሊያጡ ስለሚችሉት ገንዘብ እንዲሁም ስለ እግርኳሳቸው እድገት በማጤን ቀጣይ እርምጃቸውን እየቃኙ ይገኛሉ። በተለይ በአውሮፓ ያሉ ሃገራት ባላቸው የዳበረ ቴክኖሎጂ እና ታህታይ መወቃር (መሰረተ ልማት) እንዲሁም የገንዘብ አቅም ታግዘው ውድድሮቻቸውን ዳግም ለማስጀመር ደፋ ቀና እያሉ ይገኛሉ። ሌሎቹ ደግሞ “ጎመን በጤና” በማለት የዘንድሮ ውድድራቸውን በመሰረዝ ስለ ቀጣይ ዓመት ውድድሮች ለማሰብ ተዘጋጅተዋል። ነገር ግን የአውሮፓውያኑ የራስ ምታት የሆነው የቀጣይ ዓመት የአህጉራዊ ውድድር ተሳትፎ በተመለከተ የሚያስተላልፉት ውሳኔ ሆኗል። ከዚህ ጎን ለጎን ከታችኛው የሊግ እርከን ወደ ላይ የሚወጡ እና ከላይኛው ወደ ታች የሚወርዱ ክለቦችን የመለየት ስራ በተጨማሪም ተራራን የመግፋት ያክል ክብዷቸዋል ይታያል። እርግጥ የአውሮፓውያኑ ውሳኔ በቢሊዮኖች ከሚቆጠር ገንዘብ ጋር እየተደመረ እና እየተቀነሰ የሚሰላ ቢሆንም ግን እስካሁን የክርክሮች መድረክ ሆኖ ዘልቋል።

በዚህ ጉዳይ ግራ የተጋባችው አፍሪካም እንደ ተሞክሮ ያደጉትን ሃገራት መንገድ ለመከተል እስካሁን ዝምታን ብትመርጥም ከካፍ “የሊጎቻችሁን መገባደጃ መንገድ አሳውቁኝ” ጥያቄ በኋላ ድምፅ ማሰማት ጀምራለች። ለአብነት ጎረቤት ኬንያን ጨምሮ የጊኒ እና የአንጎላ ሊጎች ከዚህ በኋላ እንደማይደረጉ እና እንደተሰረዙ የተገለፁ ሲሆን ሌሎችም ተመሳሳይ ውሳኔዎችን ለመወሰን እየተቃረቡ እንደሆነ እየተሰማ ይገኛል። በተለይ በአህጉራችን አፍሪካ ያሉ ሃገራት ስለ ሃገራቸው ኢኮኖሚ እና ስለ ዜጎቻቸው በልቶ ማደር በሚያስቡበት በዚህ ሰዓት ስለ ሊጎቻቸው ቀጣይነት ማሰብን እንደ ሀጢያት በመቁጠር የዘንድሮን የውድድር ጊዜ እጃቸውን ተጠምዝዘው ቢሆን ያልተለመደ ወሳኔ እያሳለፉበት ይገኛሉ።

ታዲያ ሃገራችን ኢትዮጵያም በብሄራዊ ፌደሬሽኗ አማካኝነት እስካሁን የሊጎችን ቀጥይ እጣ ፈንታ ባታሳውቅም በቅርቡ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉ እየተገለፀ ይገኛል። በተለይ ከላይ የገለፅነው የካፍ ጥያቄ ነገሮች በቶሎ እንዲከወኑ እንደሚያደርግ ጠቁሟል። ለወትሮ ጭቅጭቅ እና ንትርክ ብሎም የሴራ ንድፈ ሃሳቦች በሚበዙበት የሃገራችን እግር ኳስ ሁሉን አግባቢ ውሳኔ ማሳለፍ ከባድ ቢሆንም ሚዛናዊነት እና ጊዜን ያገናዘበ መፍትሄ ማምጣት የማያሻማ ጉዳይ ነው። ከምንም በላይ ብሄራዊ ፌደሬሽናችን ይህንን ውሳኔ ለማሳለፍ ከሚመለከታቸው የእግር ኳሱ አካላት እና ከመንግስት ጋር ውይይቶችን (በተገቢው መንገድ) በማድረግ ነገሮችን መከወን ይጠበቅበታል። ከእነዚህ በተጨማሪ ከኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር እና ከኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመነጋገር ሚዛን ለሚደፉ ሃሳቦች ተገዢ መሆን የግድ ይሏል። ይህንን ታሳቢ በማድረግም በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ሊወሰኑ ስለሚችሉ 5 ውሳኔዎች ሃሳቦችን አንስተናል።

1. የሊጉ አሸናፊ እንዳይኖር ማድረግ እና ለአህጉራዊ ውድድሮች አሁን ያለውን ደረጃ ሰንጠረዥ ተጠቅሞ ተሳታፊዎቹን ማፅደቅ

ከምንም በላይ ውሳኔዎችን ለማሳለፍ የአህጉራዊ ውድድር ተሳትፎ የሚለይ መሆን እንደሚገባው የሚታመን ሲሆን ይህንን ግን በምን መልኩ ማድረግ ይኖርብናል የሚለው ለጭቅጭቆች በር የሚከፍት ነው። እርግጥ “ለተሳትፎ ብቻ” በእነዚህ የቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌደሬሽን ዋንጫ ውድድሮች ላይ የሚሳተፉት የሃገራችን ክለቦች በውድድሩ ላይ ጠብ ያለ ነገር ባያመጡም ለመርህ ሲባል ተሳታፊዎቹ አግባብ ባለው መልኩ ለይቶ እንዲሳተፉ ማድረግ ይገባል። በዚህም 17 ሳምንታት የተጓዘውን የሊጉን ደረጃ ሰንጠረዥ በመመልከት የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌደሬሽን ዋንጫ ውድድሮች ተሳታፊ ክለቦችን በመለየት የፕሪምየር ሊጉን ውድድር ማቆም ቀዳሚ አማራጭ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን እነዚህ የአህጉራዊ ውድድር ተሳታፊዎች በሚለዩበት ወቅት ሊጉን ሙሉ ለሙሉ እንዲሰረዝ አድርጎ መወሰን በዚህ ቀዳሚ አማራጭ ሊካተት የሚችል ሃሳብ ነው። ለዚህም ደግሞ ሊጉ ሙሉ ለሙሉ ሳይጠናቀቅ አሸናፊውን መለየት ተገቢ ሊሆን ስለማይችል የአህጉራዊ ውድድሮችን ኮታ ላለማጣት ብቻ አሁን ያለውን ደረጃ ሰንጠረዥ መጠቀም ሊመረጥ ይችላል። ከዚህ ጎን ለጎን በዚህ አማራጭ ውስጥ ከሊጉ የሚወርዱ እና ከታችኛው የሊግ እርከን (ከፍተኛ ሊግ) ወደ ፕሪምየር ሊጉ የሚወጡ ቡድኖች እንዳይኖሩ ማድረግ ምናልባት ሊመረጥ ይችላል። ምክንያቱም የሊጉ እጅግ የተቀራረበ የነጥብ ልዩነት እና የተደረጉ ጨዋታዎች ቁጥር ገና ግማሽ ያህል ብቻ መሆናቸው ያለ አሸናፊ ሊጉን ማቋረጥ መፍትሄ ሊሆን ይችላል። በዚህ አካሄድ ውሳኔ የሚሰጥ ከሆነ የ2012 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ ሳይኖር ሊጉን እየመራ የሚገኘውን ፋሲል ከነማ ወደ ቻምፒየንስ ሊግ መቐለ 70 እንደርታ ደግሞ ወደ ኮንፌደሬሽን ዋንጫ ያልፋሉ ማለት ነው።

2. የዘንድሮን የሊግ ውድድር ወደ ቀጣይ ዓመት ማሳለፍ

በእግርኳሳዊ ምክንያት የሚመጡ የገንዘብ ድጋፎች ብዙም በማይታይበትና ውድድር ከሚገኝ ደረጃ እና ዋንጫ ጋር ማዛመድ ልማድ ባለበት በእኛ ሃገር የዘንድሮን የሊግ አሸናፊ ወደ ቀጣይ ዓመት ማሳለፍ ብዙም አከራካሪ እንደማይሆን ይገመታል። ከምንም በላይ ለታሪክ እና ለንግርት ብቻ የሚሆነውን የሊጉን አሸናፊ እንዲሁ በ57% በሆነ የሊግ ጨዋታዎች ብቻ የመለየቱ ተገቢነት አጨቃጫቂ በመሆኑ ውድድሩን ወደ ቀጣይ ዓመት ማሳለፍ ካለው የሃገራችን የሴራ ንድፈ ሃሳቦች ጋር ተቀባይነት የሚሰጠው ይመስለናል። በዚህ አካሄድ ውስጥ ግን ሁለት አይነት መንገዶች ሊኖሩ ይችላሉ። አንደኛው የቀጣይ ዓመት ማለትም የ2013 መደበኛ ውድድርን እንደ አዲስ “ሀ” ብሎ መጀመር (ዘንድሮ ያመጡት ነጥብ ሳይቀነስ) ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከቆመው 17ኛ ሳምንት ውድድሩን አስቀጥሎ በፍጥነት በማጠናቀቅ የ2013 መደበኛ ውድድርን መጀመር የሚል ነው።

በመጀመርያው አማራጭ ቡድኖች የ2013 መደበኛ ውድድራቸውን ሲጀምሩ የዘንድሮው ወድድር ልፋታቸው መና እንዳይቀር ያላቸውን ነጥብ ይዘው ውድድር እንጂምሩ ማድረግ ላይፈፀም የማይችል ውሳኔ አይደለም። ክለቦች እጅጉን የተቀራረበ ነጥቦች መያዛቸው ውሳኔውን አስቸጋሪ ላያደርገውም ይችላል።

በሁለተኛው አማራጭ የውድድሩን ቀሪ 13 ሳምንታት በፍጥነት በማከናወን ማጠናቀቅ ሲሆን ምናልባትም ግን አማራጩ ከባድ የቤት ሥራ ግን ይዞ ሊመጣ ይችላል። ምክንያቱም ይህ አማራጭ ተግባራዊ ከተደረገ አንድ የፕሪምየር ሊግ ቡድን በ2013 የውድድር ዓመት ብቻ 43 ጨዋታዎች የማድረግ ግዴታ ውስጥ ሊገባ ይችላል። ይህም ክለቦቻችን ለከፍተኛ የፋይናንስ እጥረት፣ ተጫዋቾችን ለአካል ብቃት ችግር እንዲሁም አወዳዳሪውን አካል ለአስተዳደር በከባዱ ሊፈትነው ይችላል። ስለዚህ በዚህ አማራጭ ላይም ሁለት አማራጮች ሊኖሩ ይችላሉ፡-

ሀ) ቀሪውን የ2012 የውድድር ዓመት 13ኛ ሳምንት በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ያሉ ቡድኖችን በጥሎ ማለፍ (Playoff) በማጫወት አሸናፊውን መለየት፣ በወራጅ ቀጠናው ለሚገኙትም ተመሳሳዩን በማድረግ ወራጆችን በጥቂት ጨዋታዎች በመለየት በቶሎ የ2013 ውድድርን መጀመር

ለ) የ2012 ውድድርን ቀሪ 13 ሳምንታት በሙሉ አከናውኖ በማጠናቀቅ በመቀጠል የ2013 ውድድርን በምድብ ከፍሎ ማከናወን ሁለተኛ አማራጭ ሊሆን ይችላል። ይህ አማራጭ አንድን ቡድን በዓመቱ በአጠቃላይ (የ2012 ቀሪ ጨዋታ እና የ2013 መደበኛ ጨዋታ ድምር) ከ29 ያልበለጠ ጨዋታ የሚያደርግ በመሆኑ ምርጡ አማራጭ ሊሆን ይችላል።

ከዚህ ሀሳብ ጋር ሊነሳ የሚችለው ጉዳይ ውድድሩ ወደ ቀጣይ ዓመት በሚዘዋወርበት ጊዜ ምላሽ የማያገኘውን የቻምፒየንስ ሊግ እና የኮንፌደሬሽን ዋንጫ ተሳታፊዎቹ እጣ ፈተታ ውሳኔ ሰጪውን አካል ግራ መጋባት ውስጥ ሊጥለው የሚችለው መሆኑ ነው። ከምንም በላይ ግን እነዚህን የአህጉራዊ ውድድር ተሳታፊዎች ለመለየት ሚዛን የሚደፋው ወሳኔ የሊጉን ደረጃ ሰንጠረዥ መመልከት እንደሆነ ይታሰባል። በዚህም በብዙ አማራጭ ካፍ ለሚያዘጋጃቸው ውድድሮች የማለፍ የሰፋ እድል ያላቸው ፋሲል ከነማ እና መቐለ 70 እንደርታ በቅደም ተከተላቸው በቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌደሬሽን ዋንጫ ውድድር ላይ እንዲሳተፉ ሊደረግ ይችላል። በተጨማሪ ካፍ ሀገራት የተሳታፊዎችን ማንነት እንዲገልፁ በሚሰጠው ቀነ ገደብ መሰረት ውድድሮች ከታሰበው ጊዜ ቀደም ብለው ከተጀመሩ እስከ ቀነ ገደቡ መሪ የሚሆኑትን ክለቦች ለውድድሩ ማስመዝገብ አማራጭ ሊሆን ይችላል።

ከአህጉራዊ ተሳትፎ በተጨማሪ የመለያ ጨዋታዎች (Playoff) አማራጮች ተግባራዊ ከተደረገ እነማን ለቻምፒዮንነት፣ እነማን ላለመውረድ ይጫወቱ የሚለው ፈታኝ የቤት ሥራ ለአወዳዳሪው አካል የሚተው ይሆናል።

3. አሁን ያለውን ደረጃ ሰንጠረዥ ሙሉ ለሙሉ ማፅደቅ

የመጀመሪያ ዙሩን የሊግ ውድድር ያለፈው የሃገሪቱ የመጀመሪያ የሊግ እርከን ለመገባደድ 13 ቀሪ ጨዋታዎች ቢኖሩትም በሃገራችን እና በዓለም ካለው ከፍተኛ የወረርሽኙ ስጋት መነሻነት ሊጉ የመቀጠሉ ነገር ጥያቄ ምልክት ውስጥ ገብቷል። በተለይ በሃገራችን ያለው የክረምት ወቅት እየደረሰ መሆኑ እና የሃገራችን ሜዳዎች በክረምቱ ጨዋታን ለማከናወን ካላቸው አቅም ታሳቢነት ውድድሩ በያዝነው ዓመት እንደማይቀጥል ይገመታል። ውድድሩ ካልቀጠለ ደግሞ የሊጉ አሸናፊ ቡድን፣ የአህጉራዊ ውድድር ተሳታፊ ክለቦች እና ወራጅ ቡድኖች ላይለዩ ነው ማለት ነው። ይልቁኑም ግን እነዚህን በእንጥልጥል የቆሙትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሊጉ ያለበትን የደረጃ ሰንጠረዥ በመመልከት ውሳኔዎች በሰንጠረዥ አማካኝነት ሊፀኑ ይችላሉ። በዚህም የሊጉን መሪ ፋሲል ከነማን የሊጉ አሸናፊ በማድረግ የቀጣይ ዓመት የቻምፒየንስ ሊግ ተሳታፊ ማድረግ፣ ሁለተኛ ላይ የሚገኘው መቐለ 70 እንደርታን ደግሞ በደረጃው መሰረት ወደ ኮንፌደሬሽን ዋንጫ መላክ እና ሁለተኛነቱን ማፅደቅ እንዲሁም በሊጉ ወራጅ ቀጠና ላይ የሚገኙትን ጅማ አባጅፋር፣ ወልዋሎ ዓ.ዩ እና ሀዲያ ሆሳዕናን ከሊጉ ማሰናበት ሊጤንበት ይችላል። በወረዱት ምትክ ደግሞ በሦስቱ የከፍተኛ ሊግ ምድቦች ያሉትን የየምድቦቹ መሪዎች ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማሳደግ ሊመረጥ ይችላል። እግርጥ ይህንን ውሳኔ መወሰን ገና 17 ሳምንታት ብቻ ለተጓዘ ሊግ ርትዕ የጎደለው ቢያስመስለውም ካሉት ነባራዊ ሁኔታዎች አንፃር ነገሩን በዚህ ለመቋጨት ሊሞከር ይችላል። ቀሪ 13 ጨዋታዎች ይቅርና አንድ ጨዋታ ራሱ እጅግ በርካታ የደረጃ ለውጦች በሚያስከትሉበት ሊጋችን ይህ ውሳኔ በተለይ ወራጅ ሊሆኑ የሚችሉ ክለቦችን በእጅጉ ተጎጂ ሊያደርግ የሚትል መሆኑ ከሁሉም ውሳኔዎች አወዛጋቢው ሊሆን ይችላል።

4. የቀጣይ ዓመት ውድድር ተሳታፊዎችን መጨመር

በእኛ ሀገር ደረጃ የሊግ ተሳታፊ ክለቦችን ማብዛት መዘዙ ብዙ ቢሆንም ለወትሮውም ያለ በቂ ምክንያት የተሳታፊዎች ቁጥር ሲጨመር እና ሲቀነስ በሚስተዋልበት ሀገር ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ተንተርሶ ይህንን ውሳኔ ማሳለፍ ቀላል መፍትሄ ተደርጎ ሊወሰድ ይቸላል። በዚህ አማራጭ ውስጥ የዘንድሮው ውድድር ቻምፒዮን እንዳይኖረው ተደርጎ የሊጉን 1ኛ (ፋሲል ከነማ) እና 2ኛ (መቐለ 70 እንደርታ) ክለቦች ወደ አህጉራዊ ውድድር አሳልፎ ወራጆች ግን እንዳይኖሩ ማድረግ የሚል ውሳኔ ሊተላለፍ ይችላል። በተለይ ደግሞ የወራጅ ቀጠናው የነጥብ ልዩነት ጥቂት መሆኑ እና ቀሪዎቹ የሊጉ ጨዋታዎች በርካታ በመሆናቸው ለውጦች እንደሚኖሩ ታሳቢ ሲደረግ ወራጆችን እንዲህ ባለ ሁኔታ መለየቱ ተገቢ ስለማይሆን ነው። ከከፍተኛ ሊጉ ደግሞ ያሉትን 3 የምድቦቹን መሪዎች እና አንድ ቡድን በጥሩ 2ኛ በተመዘገበ ነጥብ በመለየት ወደ ቀጣይ ዓመት ለሚደረገው ፕሪምየር ሊግ ማብቃት ሊታሰብበት ይችላል። በዚህም በ20 ክለቦች መካከል የ2013 ውድድር (የቫይረሱ ስርጭት በፍጥነት ከተገታ) ማከናወን መፍትሄ ሊሆን ይችላል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ በዚህ አማራጭ ውስጥ የቀጣይ ዓመት የውድድሩ ቅርፅ እና ሌሎች ጉዳዮች ከወዲሁ በአፅንኦት መጤን ይገባዋል። ተሳታፊዎቹ ከ16 ወደ 20 በሚያድጉበት ጊዜ የቀጣይ ዓመቱን ውድድር ከወዲሁ በጥልቀት ማሰብ ያስፈልጋል። በተለይ ደግሞ በቀጣይ ዓመት ክለቦች ሊፈትናቸው ከሚችለው የፋይናንስ ችግር፣ ተዟዙሮ የመጫወት አቅም እና የሃገራችን የአየር ፀባይ ጋር ነገሮችን ከአሁኑ አስቦ እና አሰላስሎ መወሰን የግድ ይላል። በእነዚህ እና በሌሎች ወደ ፊት ሊከሰቱ ከሚችሉ ተለዋጭ ችግሮች ጋር ውሳኔን በመቃኘት የቀጣይ ዓመት ውድድሩን ወይ በምድብ ከፍሎ አልያም እንደቀድሞ በደርሶ መልስ የሚደረግበትን መንገድ መቀየስ አለበት። በተለይ በ2014 የሚደረገው ውድድር በተለመደው ቁጥር (16) እንዲካሄድ ቢያንስ 7 ቡድኖች ወደ ከፍተኛ ሊግ የሚወርዱ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ፍትሀዊ ውድድር ለማካሄድ ወገብ ጠበቅ ማድረግ ያስፈልጋል።

5. የዘንድሮውን ውድድር ሙሉ ለሙሉ ሰርዞ ለአፍሪካ ውድድር አላፊ ክለቦችን የዓምናዎቹን በድጋሚ ማድረግ

እርግጥ ይህ አማራጭ ከባዱ አማራጭ ቢሆንም ለሊጉ መገባደጃ ልጓም ለማበጀት ግን አንዱ መንገድ ሊሆን ይችላል። በተለይ ቀሪዎቹ የሊጉ ጨዋታዎች ብዛት እና የደረጃ ሰንጠረዡ የነጥብ ቅርርብ ይህንን አማራጭ ውሳኔ ሰጪው አካል ሊያሰላስለው እንደሚችሉ ይጠቁማል። ከዚህ ጎን ለጎን ግን በ17ቱ የሊጉ ጉዞ እየታተሩ ለመጡ ክለቦች ውሳኔው ልፋታቸውን መና የሚያስቀር ቢሆንም ከላይ የተጠቀሱት መንገዶች ካለተመረጡ ይህ “አከራካሪ” ውሳኔ ሊተላለፍ ይችላል። ከምንም በላይ ይህንን መንገድ አጨቃጫቂ የሚያደርገው የዘንድሮን ውድድር መሰረዝ ሳይሆን የዓምናዎቹን የአህጉራዊ ውድድር ተሳታፊ ክለቦች በድጋሚ ማሳለፍ የሚለው ነው። እርግጥ በዚህ አማራጭን ፋሲል እና መቐለ በውሳኔው በተመሳሳይ የሚጠቀሙ ቢመስሉም አሁን ያለው የሊጉ ሰንጠረዥ ከሚነግረው የመወዳደሪያ ቦታ አንፃር መለዋወጦችን ሊቀበሉ የግድ ይላል። ይህ ማለት አሁን ያለው የሊጉ መሪ እና ዓምና የኢትዮጵያ የጥሎ ማለፍ አሸናፊው የነበረው ፋሲል ከነማ በአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ዋንጫ እንዲሁም አሁን በሊጉ 2ኛ ደረጃን የያዘው እና የዓምና የሊጉ አሸናፊ መቐለ 70 እንደርታ በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ እንዲሳተፉ ሊሆን ይችላል። ከዚህ ጎን ለጎን በዚህ አማራጭ የዘንድሮ የውድድር ዘመን ሙሉ ለሙሉ ባዶ ሆኖ ስለሚቆጠር የሊጉ አሸናፊ፣ ከሊጉ የሚወርዱ እና ወደ ሊጉ የሚወጡ ክለቦች አይኖሩም ማለት ነው።

(ከአፍሪካ ውድድር አላፊዎች ውጪ ሀሳቦቹ ለሁሉም የሊግ እርከኖች እንደአማራጭ መቅረብ ይችላሉ)

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ