በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ ያለፉት 20 ዓመታት ስማቸው በጉልህ ከሚነሱ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው እና የበርካታ ድሎች ባለቤት ደጉ ደበበ የዛሬ “ትውስታ” አምዳችን ተረኛ ነው።
ጥቂት የማይባሉ ከእርሱ በተቃራኒው የሚጫወቱ አጥቂዎች እንደርሱ የሚያስቸግረን ተከላከይ የለም ይሉታል። በአርባምንጭ ከተማ መጫወት የጀመረው ደጉ በቅዱስ ጊዮርጊስ እና ብሔራዊ ቡድን ለ14 ዓመታት በመጫወት አይረሴ የሆኑ ዓመታትን አሳልፏል። በተለይ በፈረሰኞቹ ቤት ከ1996 – ከ2010 በቆየባቸው ዓመታት 10 የፕሪምየር ሊግ (አምስቱን በአምበልነት)፣ 5 የአሸናፊዎች አሸናፊ እና 3 የኢትዮጵያ ዋንጫ ሲያሳካ በብሔራዊ ቡድኔ ደረጃ ደግሞ 2 የሴካፋ ዋንጫዎችን በማንሳት በድምሩ 18 የዋንጫ ክብሮችን አሳክቷል። እነዚህ የዋንጫ ቁጥሮች የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫን እና ሌሎችንም ሳይጨምር ነው። በግሉም በ1997 እና በ2004 ሁለት ጊዜ የፕሪምየር ሊጉ ኮከብ ተጫዋችነት ክብርን አግኝቷል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ31 ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ሲመለስም የቡድኑ አምበል ነበር። ይህ ስኬቱን አስመልክቶ ወደ ኃላ በትውስታ አምንዳችን እንዲያጫውተን ጠይቀነው ይህን ብሎናል።
” ተጫዋች ስትሆን ሁልጊዜ ተጫዋች ብቻ ሳይሆን ራስህን የታሪክ አካል ማድረግ አለብህ። ከእኔ የተሻሉ አቅም ያላቸው ተጫዋቾች ይሄን ዕድል ያላገኙ ይኖራሉ። ጠንክሮ ከመስራት በተጨማሪ እኔ ዕድለኛ ስለሆንኩ ይሆናል ይህ ስኬት የተገኘው። ይህ በዋንጫ የታጀበ የስኬት ዓመታት ከእኔ በኃላ ባለ ትውልድ ይደገማል ብዬ አላስብም። ለአስራ አራት ዓመታት አንድ ቡድን መጫወት በዚህ ዘመን የማይታሰብና ከባድ ነው። በውስጥህ ጥንካሬ፣ በራስ መተማመን፣ ሥራን ማክበር፣ ሜዳ ውስጥ ስትገባ ሁሉ ነገርህን ለክለብህ መስጠት ይፈልጋል። ይህን ሳስብ የሚደገም አይመስለኝም። እኔ በጣም ደስተኛ ነኝ በዚህ ሙያ ውስጥ ሁሉም የሚያወራቸው ስኬቶች ባለቤት ስለሆንኩ”።
ደጉ ከፈረሰኞቹ ጋር ከተለያየ በኃላ ያለፉትን ዓመት ከመንፈቅ ከወላይታ ድቻ ጋር መልካም ቆይታ እያደረገ ይገኛል።
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ